ከመንግሥት ተቋማት በመቀነስ ተጨማሪ 20 ሺሕ ሊትር ውሃ ለነዋሪዎች እንዲደርስ ተደረገ

0
600

ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በየቀኑ ሲደርስ ከነበረው የውሃ ፍጆታ በተጨማሪ ከመንግሥት ተቋማት በመቀነስ 20 ሺሕ ሊትር መጨሩን የአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ባለሥልጣን አስታወቀ። ባለሥልጣኑ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው፣ ከትላልቅ እና ከፍተኛ ውሃ ፍጆታ ካላቸው የመንግሥት ተቋማት ተቀናሽ የተደረገውን 20 ሺሕ ሊትር ውሃ ወደ ኅብረተሰቡ እንዲከፋፍል እየተደረገ ነው።

በዋናነት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ይፋ ከተደረገ በኋላ አንዱ ወረርሺኙን ለመቆጣጠር እንደ መፍትሄ ከተቀመጡት ንፅህናን መጠበቅ እንደመሆኑ፣ የውሃ ስርጭት ተደራሽነቱን ለማስፋት በሙሉ ሰዓት እየተሠራ ሲሆን፣ ባለሙያዎች እና የውሃ ስርጭት ክፍል ሠራተኞች 24 ሰዓት እንዲሠሩ መደረጉን የባለሥልጣኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሰርካለም ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የሥራ ሰዓት የተጨመረበት ምክንያት በዋናነት በአዲስ አበባ ከተማ የኮቪድ 19 ቫይረስን ለመመርመር እና ለለይቶ ማቆያ ተመርጠው የተለዩ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ ውሃ ፍጆታ ይኖራል ተብሎ በመታሰቡ እና ይህንንም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ታስቦ ነው። ለዚህም 28 በሚሆኑ በቦቴ ተሽከርካሪዎች ሞልቶ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ እንደሆነም ታውቋል። ከዚህም ባሻገር ወረርሽኙን ለመግታት ሕዝብ በሚበዛባቸው በአምስት አውቶብስ ተራዎች ማለትም መርካቶ፣ አስኮ፣ ዘነበወርቅ፣ ቃሊቲ እና ላም በረት አካባቢ የውሃ መስመር መዘርጋቱንም ጨምረው ገልጸዋል።

እንደ ሰርካለም ገለፃ የውሃ ፍጆታ ከተለያዩ መንግሥት ተቋማት መቀነሱ ለውሃ አቅርቦቱ መስተካከል አስተዋጽኦ አለው። ይህ መደረጉ የነበረው የውሃ ስርጭት ላይ ለውጥ ቢኖረውም፣ የፈረቃ አሰራሩ እንደማይቀየር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ፈረቃው እንዳይቀር ያደርገው ዋናው ምክንያት ደግሞ ባለሥልጣኑ ውሃ የማምረት አቅሙ ውስን ስለሆነ ነው ብለዋል። እንደ ሰርካለም ገለጻ ከሆነ፣ የኮሮና ቫይረስ ኮቪድ 19 ከመጣ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የውሃ ፍላጎት ቢሠራ ከዚህ በላይ እንደሚሆን ነው። ስለዚህም ፍላጎት እና አቅርቦት ላይ ከፍተኛ አለመመጣጠን ስላለ ፈረቃው እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከትላልቅ ተቋማትም የውሃ አቅርቦት ቅነሳ ሲደረግ በአንጻራዊነት የፈረቃውን ሂደት እንዳያዛባ በጥንቃቄ እየተሠራ ሲሆን፤ በዋነኛነት የውሃ አቅርቦት ቅነሳ በመደረጉ እያስተካከልን ያለነው በፈረቃም ሆኖ በተገቢው መንገድ ኅብረተሰቡ እንዲደርሰው የማድረግ ሥራ ነው ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ረጅም ጊዜ የውሀ አቅርቦት የተስተጓጎለ ነበር ያሉት ሰርካለም፣ ለቡ ላይ የተሰበረ የውሃ መስመር በመኖሩ ምክንያት አየር ጤና አካባቢ፤ ዓለም ባንክ፣ ቆሬ እንዲሁም ዘነበ ወርቅ አካባቢ ፈረቃ መስተጓጎል አጋጥሞ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ አስታውሰዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ የውሃ ማምረት እና የማቅረብ አቅሙ አለመጣጣም እንዳለ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ከተማን የቀን ፍጆታ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ሲሆን፣ ነገር ግን ወደ ነዋሪው እየቀረበ የሚገኘው 570 ሺሕ ሜትር ኩብ ውሃ ብቻ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከአዲስ አበባ ውሃ እና ፍሳሽ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here