‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ሰው የሚባለውን አይሰማም የሚል ትንታኔ ትክክል አይመስለኝም››

0
513

የሰብአዊነት ድጋፍ ጥምረት ቅድሚያ ለሰብአዊነት ብሎ የሚንቀሳቀስ ኅብረት ነው። ወጣቶቹ እንዲህ ሰውና መገናኛ ብዙኀን ሁሉ ስለመረዳዳትና ድጋፍ ስለማሰባሰብ መናገር ባልጀመሩ ጊዜ፣ በሚደርሱ ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋዎች ወቅት በፍጥነት ድጋፎችን ከበጎ አድራጊዎች በመሰብሰብ ለተቸገሩት የሚያደርሱ ናቸው። ይህም ‹የት ሄጄ…በማን በኩል…ለማን ልርዳ?› ለሚሉ ግለሰቦችና ባለሀብቶች ምላሽ የሰጠ ነበር።
አሁን የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለም ላይ ካደረሰው ማኅበራዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አንጻር፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድሃ ነገር ግን አዳጊ የሚባሉ አገራት ጫናው ቀላል አይሆንም። ይህንንም ክብደት ‹ሃምሳ ሎሚ…› ብለው፣ ሸክሙን ለማቅለል ከወዲሁ የበጎ አድራጎት ልገሳና ድጋፎች እየተደረጉ ይገኛሉ። ይህንን በሚመለከትም፣ የበጎ አድራጎት ሥራንና ከዚህ ቀደም የነበረውን እንቅስቃሴ በማንሳት ከሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት መሥራቾች መካከል ያሬድ ሹመቴ፣ ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

ከዚህ ቀደም በተለያዩ ተፈጥሮአዊ እንዲሁም ሰው ሠራሽ አደጋዎችና ችግሮች ምክንያት የተለያዩ ድጋፎችን ስታሰባስቡ ነበር። አሁን ወረርሽኙን በተመለከተ የሚደረገው የድጋፍ ማሰባሰብ ከቀደሙት በምን ይለያል?

ከዚህ ቀደም ከነበረው እርዳታ የማሰባሰብ ሥራ ይህን ለየት የሚያደርገው፣ አብዛኞቹ ከዚህ በፊት ያደረግናቸው አዲስ አበባን የለጋሽ ማእከል አድርገን፣ ከአዲስ አበባ ውጪ ላሉ ነው እርዳታ እናደርግ የነበረው። ይህ ችግር ከመጣና ጥሪውን ካቀረብንበት ጊዜ አንስቶ ግን፣ ለጋሾችም ራሱ ልገሳ የሚፈልጉበት ደረጃ ላይ ስለደረሱ/ስለሚደርሱ ይህ ለየት ይላል።

ሌላው ከዚህ ቀደም የነበረው አደባባይ የሚወጣ ችግር ነው። ማለትም አንድ ሰው ተፈናቅሎ ሌላ ቦታ ቢሰፍር፣ የሰፈረበትን ቦታና የደረሰበትን ችግር በገሃድ ማየት ይቻላል። ስለዚህ ለመርዳት ወይም እገዛ ለማድረግ ብዙ አይቸግርም። ይህ ግን ማን ምን ዓይነት ችግር እንደደረሰበት ለማወቅ ያስቸግራል። ‹ቤት ይቁጠረው› የሚባል ዓይነት ባህሪ ያለው ስለሆነ ነው።

አንዳንድ ምልክቶች ግን እናያለን። ለምሳሌ ሰዉ ለምንድን ነው አሁን ወደ ሥራ ገበታው የተመለሰው፣ ወይ አንድ ሰሞን ቀርቶ የነበረው እንቅስቃሴው አሁን ደምቆ የታየው ስንል፣ ይህ ለእኔ ማኅበራዊ ቀውስ ለመፈጠሩ አንዱ ማሳያ ነው። ቤቱ መቀመጥ ስላልቻለ ብሞትም ልሙት ብሎ ሰው ወደሥራ እየገባ ነው። ይህን መታዘብ የምንችልበት ግን እውናዊ የሆነ ማረጋገጫ የለም። መንገድ ላይ የምታገኚውን ሰው እያንዳንዱን ካላናገርሽ በቀር።

ተዘግተውና ቆመው የነበሩ፣ ከቤት መውጣትን የሚጠይቁ የሥራ ዘርፎች፣ በተለይ የእለት ገቢ የሚገኝባቸው ሥራዎች ተመልሰው ወደመከፈት የሄዱት፣ ቤት ውስጥ በመቀመጥ ምክንያት እየደረሰ ባለው የምግብ ዋስትና ችግር ምክንያት ሊሆን ይችላል። እንዲህ አድርጎ የሚተነትንና የሚያጠናም ያስፈልገናል።

አሁን ባለው ሁኔታ ሰው አይሰማም የሚል ትንታኔ ትክክል አይመስለኝም። በሌላው ዓለም ሰዎች በፖሊስ በግድና በዱላ እየተደበደቡ አትውጡ ሲባል እናያለን፤ እንደዛ በሕግ ግዳጅ ከመጣ እኛም አገር ግርፊያው አይቀርም። ምክንያቱም አትውጣ ቢባል ቤት ለመቀመጥ የሚያስችል የተረጋጋ የገቢ ምንጭ የሌለው ሰው ያንን ማድረግ አይችልም።

ስለዚህ የማኅበራዊ ሳይንስ ምሁራን፣ ተቋማት በአሁን ሰዓት ያለውን ነገር አጥንተው መግለጥ አለባቸው። በስታትስቲክ ኤጀንሲ 2007 የተደረገው የቤትና ሕዝብ ቆጠራ መሠረት፣ አዲስ አበባ 30 በመቶ ሕዝብ በእለት ገቢ የሚተደዳርና ዝቅተኛ ገቢ ያለው ወይም ምንም ገቢ የሌለው ነው። ይህም በቁጥር 2.1 ሚሊዮን ይሆናል። ሌሎች በምገዝባ ያልተካተቱ ሲጨመሩ 40 ሺሕ አካባቢ፣ በአጠቃላይ 2 ሚሊዮን 140 ሺሕ አካባቢ ሰዎች እርዳታ ይፈልጋሉ የሚል ጥናት አለ፣ በምገባ ኤጀንሲ በኩል የቀረበ።

ነገር ግን ሰዉ ለምን ምክሩን ለመስማት ቸል የሚል ጥናት ቢጠና፣ በትክክል ከቤት ለመውጣት የሚያስገድድ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ መኖሩን የሚያሳይ ነው የሚል መነሻ ግምት (Premise) አለኝ። ያ ስላልተደረገ ግን ተጽእኖውን ማወቅ አንችልም።

ከጤናው ባሻገር ደግሞ ኢኮኖሚው ላይ ለሚመጣ ጫና አሁናዊ ማሳያ ማግኘት አይቻልም። ማለትም አንድን ውሃ የምታጠጪውን ዛፍ ወይም ችግኝ አንድ ቀን ውሃ ብትነፍጊው አረንጓዴነቱን በኹለተኛ ቀን አያጣም። ‹ይኸው ዛሬ ውሃ አላጠጣሁትም፣ ነገር ግን አሁንም አረንጓዴ ነው› ብትይ ትልቅ ስህተት ነው። ከምጣኔ ሀብት ጋር የሚገናኙ ነገሮች በኋላ ነው የሚጎዱት።

ወደነጥቦቹ ስመለስ፣ በቀይ መስቀል ማኅበር በኩል የምግብ ዋስትና የሚል ሐሳብ አለ። እሱን ማሳከት ከቻልን ቀጥሎ የምንሠራው የተመጣጠነ ምግብ ዋስትና የመስጠት እቅድ አለ። መብላት ብቻ ሳይሆን ጤናውን በጠበቀ መንገድ አስፈላውን ንጥረ ነገር ያሟላ ምግብ ሰው ማግኘት አለበት የሚል ነው። ወደዛ ደረጃ መድረስ አለብን በሚል በጋራ እየሠራን እንገኛለን። አሁን ትልቁ የገጠመን ውጥርት የምግብ ዋስትናን በሁሉም መልክ ለማረጋገጥ፣ የቁጥሩ ነገር ነው። አዲስ አበባ ላይ ብቻ 2.1 ሚሊዮን ሰው ማገዝ ያስፈልጋል ከተባለ፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ምን ያህል እንደሚሆን ቁጥሩ አዳጋች ነው።

በተጨማሪ አካል ለአካል ግንኙነቶች በመቀነሳቸው ወይም ባለመበረታታቸው ምክንያት፣ በርካታ እርዳታ ማድረግ ልቡ የሚሻ ሰው እርዳታውን ለመለገስ የሚያስችለው የቴክኖሎጂ ተደራሽነት እጅግ አናሳ ነው። ይህም መሆኑ አሁን ያለውን እርዳታ የማስተባበር ሥራ ከባድ አድርጎታል ብዬ አስባለሁ። ከዚህ በፊት አገር ፍቅር ቴአትር ቤት ውስጥ በዐስር ዲቂቃ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይመጡ ነበር። አልፎም መጋዘኖች ሞልተው የቀይ መስቀል ማኅበርን ትልልቅ መጋዘን እየተጠቀምን ከስር ከስር እየላክን፣ የአገር ፍቅር ቴአትር ጊቢን ሳይቀር የእህል ማከማቻ አድርገን ሰፊ አንቅስቃሴ እናደርግ ነበር። ለዚህ ያገዘን ሕዝቡ እዛ ለመምጣት ምንም ስለማይቸገር ነው።

አሁን ግን ቤት ተቀመጥ የተባለን ሰው እንደገና እርዳታ ለመስጠት ውጣ ማለት ከባድ ነበር። ይህ አንዱ መከራ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ከዚህ ቀደሙ የተለየ ያደርገዋል።

ሌላ አዲስ አበባ ውስጥ ግዙፍ እርዳታ ማሰባሰብ ሥራን የምንሠራው እኛ ብቻ ነበርን። አሁን መንግሥም ገብቷል፣ በየመንደሩም እርዳታ ለማስተባበር የተነሱ ብዙ ወጣቶች አሉ። በአንድ መልኩ አሁን እየተሰበሰበ ያለው በእኛ ብቻ ስላልሆነና በሌሎችም አካላት ጭምር ስለሆነ፣ የበርካታ ሰዎች እጅ የሚያርፍበት የበርካታ ተቋማትም ተሳትፎ ያለበት ነው። በሌላ መልኩ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተሻለ ነው ልንል እንችላለን። የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እንኳ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ማሰባሰብ ችሏል። ይህ ከዚህ በፊት አልነበረምና ጥሩ ጎን ነው።

እነርሱም [መንግሥት] መዋቅራቸውን ነው የተጠቀሙት። እናም አንዳንድ ሰዎች ሳይወዱም፣ በአገራችን መንግሥት ጠይቆ እንቢ ማለት ስጋት ስላለው፣ በዛ ልክ እርዳታ ለማድረግ የተንቀሳቀሱ ሰዎች እንደሚኖሩ እገምታለሁ፣ እንሰማለንም። ይህም የራሱ የጎንዮሽ ጉዳት ቢኖረውም፣ በዛ ልክ አቅም መሰብሰብ መቻል መልካም ነገር ነው።

በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በተፈጥሮአዊ አደጋ ዙሪያ በመከላከልና አደጋም ሲደርስ ተጎጂዎችንና ሰለባዎችን ለማገዝ መንግሥት በጀት መድቦ ይሠራል። ሌሎች የእርዳታ ተቋማትም ይህን ይሠራሉ። ሰው ሠራሽ በሆነ ችግር ምክንያት የሚፈጠሩ አደጋዎችን ግን መንግሥት ራሱ ባላየ ነበር የሚያልፋቸው፤ ለመንግሥት መጥፎ ገጽታ ነበር። ይህን ያህል ተፈናቃይ አለ ሲባል፣ አንቺ የምትይውና መንግሥት የሚያቀርበው ቁጥር ራሱ ይለያያል። እውነታዎችን የመደበቅ ነገር ነበር።

ይህኛው ግን አፍጥጦ የመጣና የዓለም ክፈተት በመሆኑ፣ መንግሥትም በተለየ መንገድ ይህን ችግር አመጣ ተብሎ ስለማይወቀስበት፣ በዚህ መሳተፉ እንደ በጎ ጎን ማየት ይቻላል።

በኢትዮያ በበጎ አድራጎት ሥራ የመሳተፍና የመለገስ ባህላችን ድሮም የነበረ ነው ወይስ ይህ ወረርሽን እንደ አዲስ ቀስቅሶታል?
ሦስት ምክንያቶችን እዚህ ላይ መጥቀስ ይቻላል። ኢትዮጵያውያን ሃይማኖተኛ ሕዝብ ይባላል። ጥንትም የቆየ የመስጠት ባህል አለ። ሰው ከሚባለው ከሚጠጣው፣ ከገቢውም በየሃይማኖቱ አስራት በኩራት ያወጣል። አቅመ ደካሞችን ለመርዳትም እንደዛው። የሚለምኑ ሰዎች በየቤቱ ዞረው የሚበላ ወይም ሳንቲም ይዞ ለመሄድ አይቸገሩም። ይህ በኢትዮጵያ የቆየ ባህል ነውና ቀድሞ ነበረን ብሎ ማሰብ ይቻላል።

ኹለተኛ እኛ አገር እርዳታ ለሚሰጥ ምንም ማበረታቻ አይደረግም ነበር። በሌሎች የሠለጠኑ አገራት በጎ አድራጎት ስትሠሪ መንግሥት ‹ሥራዬን ስለሠራችሁልኝ ይህን ያህል የግብር ቅናሽ አድረጌአለሁ› የሚልበት አሠራር አለ። እኛ አገር ያ የለም። እናም ብዙ ተቋማት ወደ እርዳታ ለመግባት የሚያበረታታቸው ነገር አልነበረም። በተቃራኒው ወደ እርዳታ እንዲገቡ የሚያደርጋቸው የሕዝብ ግንኙነት ወይም የማስተዋወቅ እድል የሚፈጥርላቸው አጋጣሚ ነው። ስለዚህ በዚህ መልክም ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ለድርጅቶች እንደ አንድ የገበያ ሥራ እቅድ ያዩት ስለነበር እሱም ባህል ሆኖ ቆይቷል።

ሦስተኛው በጎ ፈቃደኝነት የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ድሮም ይታወቃል። ከሆነ ጊዜ በኋላም ብዙ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመታየታቸውና የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ በመኖሩ ምክንያት፣ የብዙ ሰዎችን ስሜት ለመኮርኮርና ለማንሳሳት እድል ሰጥቷል። የበጎ ፈቃድ ላይ ለራስ እርካታ የሚሰማሩ ሰዎችም፣ ኹለቱን ቀስቅሰው ወደ ተግባር ለማዋል አስችለዋል።

ስለዚህ እነዚህ ባህል ነበረን ወይ የሚለውን ይመልሱልናል። አሁን ያለው የመስጠት አንቅስቃሴ ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው በታች ነው ብዬ ነው የማስበው። ገቢው ሳይሆን እንቅስቃሴውን ነው። እርግጠኛ ሆኜ የምንገረውና እኛ ጋር ያለው መረጃ ሲታይ፣ 10 ሺሕ የሚሆኑ ቡድኖች ባለፈው ጥቅምት አካባቢ ባደረግነው የእርዳታ ማሰባሰብ ሥራ ተሳትፈዋል።

ይህ ማለት አንድ ቦታ የሚሠሩ የሥራ ባልደረቦች፣ አንድ ኮንዶሚንየም የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ አንድ ሰፈር ያሉ ጓደኛሞች ተሰብስበው ተሳትፈዋል፣ መጠኑን ማሰብ ነው። ዓይነቶቹ ትንሽ ሊሆኑ ይችላሉ። ግን አሁን ባለው ስናይ በቡድን የማሰባሰብ ነገር የለም ማለት ይቻላል። ድርጅቶችን ግን እንሰማለን፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይሰጣሉ። አሁን የተደረገውን ድጋፍ መጠን ድምሩን ስታይ ከዚህ ቀደም ሲሰበሰብ ከነበረው ትልቅ ነው። በተሳትፎ ግን አነስተኛ ነው። ለዚህም አብዛኛው ሰው ለራሱ የሰጋበት ስለሆነ ነው የሚል ግምት ማስቀመጥ ይችላል።

አካላዊ መራራቁም አንድ አስተዋጽአ ይኖረዋል?
አሁን የምንናገረው ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ ነው። ግን መታዘብ እንደምንችለው አካላዊ መራራቅ በመኖሩ የሚፈጥረው ነገር አለ። ሆኖም ነገሮችን የምናሳይበት መንገድ ችግር ገሃድ አውጥቶ የሚያሳይ አይደለም። አንድ ቦታ ቦንብ ፈነዳ ቢባል በቦታው ቢያንስ ጥላሸት ይታያል። አሁን ግን አይታይም። የሚታያቸው በጣም ትጉህ የሆኑና አርቀው ማሰብ የሚችሉ፣ የከፋ ችግር ያመጣብናል የሚል ግንዛቤ የደረሳቸው ሰዎች ናቸው፣ የሚሳተፉትም። እንጂ በዐይን የሚታይ ችግር አይደለም። ዋናው እሱ ይመስለኛል። እንጂ በአካል መምጣት አለመቻል ትልቁ ችግር አይመስለኝም።

ይህ ድጋፍ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ እስከመቼ ይቀጥላል?
የፊታችን ሰኞ (ሚያዝያ 19/2012) ኹለተኛ ዙር እንጀምራለን። የምንቀጥለው እስከመቼ ነው የሚለውን መወሰን አንችልም። የመጀመሪያ ዙሩን ባሳፈልነው ሳምንት ነበር ጨርሰን ቅስቀሳ ያቆምነው። ቅስቀሳ አቁመንም ሰዎች ይመጣሉ። ዛሬም (ሚያዝያ 14/2012) ጭምር እርዳታ ስንቀበል ነበር።

ኹለተኛው ከመጀመሪያው በምን ይለያል የሚለውንና አንድ ኹለት ማለቱ ለምን እንዳስፈለገ በዚሁ ላንሳ። ሁሌም እርዳታ እንሰበስብና ከስር ከስር የምናደርስበትን ሪፖርት እናደርጋለን፣ ለሕዝቡ። ስለዚህ አንዴ ዘመቻውን ስናቆም ሙሉ ለሙሉ ነው የምናቆመው። አሁን ባለው ሁኔታ እርዳታ አድርጉ እንላለን፣ ግን የተቸገረ ካልነው ውስጥ ምን ያህል ረዳን፣ ምን ያህሉን አገዝን፣ የስንቱን ችግር መቅረፍ ቻልን የሚለውን እያሳየን አይደለም።

ስለዚህ ከአንድ ሳምንት ወዲህ ያሉትን ስንሠራ የቆየነው እንዴት እናግዝ፣ እናሰራጭ የሚለውን ነው። የመጀመሪያ ቤት ለቤት የሚኖሩ የምግብ እርዳታዎች አሉ፣ በየቤቱና መንደሩ የሚደረግ ነው። ለሱ የመንግሥትን ተሳትፎ እንጠብቃለን። የምግብ ባንኮች ተቋቁመዋል። በዛ እኛም ተሳትፎ አለንና፣ ድግግሞሽ እንዳይፈጠር፣ በየቤቱ ለሕዝቡ የሚሰጠውን ማቀናጀት ላይ ከመንግሥት ጋር የምንሠራ ስለሆነ በእኛ በኩል ሪፖርት አይኖርም።

ነገር ግን ማእከላት አሉ፣ የአረጋውያን፣ የሕጻነት፣ የአእምሮ ሕሙማን፣ የአካል ጉዳተኞች የመሳሰሉት። ለእነዚህ እርዳታ አድርሰናል። እነዚህን እርዳታዎች ሪፖርት እናደርጋለን። ይህን ያህል ምግብ ለዚህ ለዚህ ሰጥተናል እንላለን። አንደኛ ድግግሞሽ እንዳይፈጠርና ወደሌላ ቦታ ፊታችንን እንድናዞር ነው። ኹለተኛ የሰጠ፣ የለገሰ ሰው ድጋፉ ወደዚህ ቦታ መሄዱን እንዲያስብና የቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ግምት ውስጥ እንዲከት ነው።

ኹለተኛ ዙር ቅስቀሳ ስናደርግ ያልሰጡትን ብቻ ሳይሆን የሰጡት ድጋሚ እንዲያስቡበት በሚያደርግ መንገድ ለማምጣት ነው።
ዛሬ መቶ ኩንታል እህል በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በኩል ወጪ አድርገን የምግብ ዝግጅት እየተደረገ ነው፣ ምገባ እጀምራለን። ማእከል መርጠናል። የሙከራ ሥራ የምንጀምርባቸው ኹለት ማእከላት ላይ ምግብ ማብላት ነው። ይህም ማለት በቀን ሥራ ይተዳደሩ የነበሩ ሰዎች ከቤታቸው ወጥተው ምግብ ይዘው ተመልሰው ቤት የሚገቡበት ወይም ቤት የሌላቸው፣ መንገድ ላይ ያሉት የሚበሉት እንዳያጡ በየቦታው ምግብ አዘጋጅተን የሚቀርብበትን መንገድ እናስተዋውቃለን።

ስለዚህ ኹለተኛ ዙር ስንጀምር ሕዝብ የሰጠንን የት እንዳደረስን አሳይተን ለቀጣይ እንቅስቃሴ ሥራ የምንጀምርበት ነው። መች ያቆማል የሚለውን ለመናገር፣ መቼ ነው ይህ ችግር የሚወገደው የሚለውን ነው ማየት የምንችለው፣ እንጂ መገመት አንችልም። ግን ወደ እደላ ስንገባ እናቆማለን። ጎነ ለጎን የሚመጣም ካለ ማእከሉ ሥራ ላይ ስላለ እንቀበላን። አጠናክረን ወደ ኹለተኛው ዙር እርዳታ ማሰባሰብ ተግባር እንገባለን።

በነገራችን ላይ የእህል ክምችት ላይ ብዙ አስበን ስናከማች ቆይተናል። ግን በሚያሳዝን ሁኔታ የእህል ማቆያ ስለሌለ፣ ወደ ነቀዝት የተቀየሩ እህሎች አሉ። እኛ ጋር [አገር ፍቅር] ባይገጥመንም ሌሎች ማከማቻዎች እንዲህ ያለ ችግር ገጥሟል። ስለዚህ ምግቦችን በቶሎ ማውጣት አስፈላጊ ነው።

ግን የከፋ ችግር እስኪደርስ ብሎ መጠየቅም አያስፈልግም። እናም አሁን ነው ሳይስፋፋ መቆጣጠር ያለብን። ስለዚህ ቶሎ ወደ ተግባር ለመግባት ግፊት እየፈጠርን ነው።

ወረርሽኙን ባለበት መቆጣጠር ተችሎና ይህ ነገር በፍጥነት ካለፈ/ሲያልፍ የተሰበሰበው እርዳታ ምን እንዲደረግ ታስቧል?
በሽታው ጠፍቷል፣ ሙሉ ለሙሉ ቆሟል፣ ስጋት የለም የሚል ሪፖርት ቢደርሰን፣ ለአንድ ዓመት መቀጠል አለብን የሚል እምነት አለን። እኔም ብቻ ሳልሆን የሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት አገር ፍቅር የምናምነው በዛ ነው። ምክንያቱም ጫናው ቶሎ የሚፈታ አይደለም። የኢኮኖሚ ጫናውም ቶሎ መፍትሔ የሚገኝለት አይሆንም።
ቀድሞ እንዳልኩት ችግሩ ቆሟል ቢባል እንኳ ጉዳቱ ቆይቶ ስለሚመጣ፣ እርዳታ ከማሰራጨት የሚቆምበት ምክንያት የለም። መልሶ ማቋቋም ሥራ በምንም ተአምር ቫይረሱ ቀርቷና እናቁመው የሚባል አይደል። ማኅበራዊ ዋስትናን አጠናክሮ ወደፊት መግፋት ግዴታ ነው። ይህን ችግር ብንወጣው፣ እናም በኋላ የሚመጣውን የኢኮኖሚ ችግር መቆጣጠር ብንችል እንኳ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ከ30 በመቶ የማያንሱ ዜጎች በአዲስ አበባ ብቻ እንኳ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ናቸው።

ይህ ችግር ስለመጣ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ጊዜ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ የሚኖሩ ብዙ ዜጎች ያሉበት አገር ስለሆነ፣ ነገሩ ቢቆም እንኳ እርዳታ የማይፈልግ ሰው ደራጃ ላይ ነን ብሎ ማሰብ ቅንጦት ነው የሚሆነው። ጸሎታችን ወረርሽኙ እንዲቆም ነው። ከቆመም በኋላ ግን ድጋፍ ማሰባሰቡን ቶሎ እናቆማን የሚል ነገር ላይ ከደረስን ሕዝባችን ረዳን ማለት አይቻልም።

በጎ አድራጎት በተለያየ መንገድ ይገለጣል። ሰው ምን መለገስ፣ ምንስ መስጠት ይችላል?
መጀመሪያው ነገር በግለሰብ ደረጃ አንድ ሰው ቁርስ፣ ምሳ፣ ራት የሚበላ ከሆነ፣ ከዚሀ ውጪ ምንም ከሌለው ቢያንስ ቁርሱን መተው ይችላል። ማንም ሰው መስጠት አይችልም የሚል ድምዳሜ የለንም። አንድ እናት ለምሳሌ ሥራቸው ልብስ ማጠብ ነው። ልብስ ደግሞ አሁን ቫይረሱን ሊያጋባ ስለሚችል፣ እኛ ጋር ይመጡና ጉልበት ሥራ አግዘው ውለው ይሄዳሉ።

እና ጉልበትንም እንዲህ ላለ አገልግሎት ማዋል ይቻላል። በእርግጥ ብዙ የበጎ ፈቃደኝነት እጥረት የለብንም። ግን በየአካባቢው በጉልበት አገልግሎት መስጠት ይቻላል። በዋናነት ግን ከራስ አልፎ ለሌላ ሰው ማሰብና መጨነቅ የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን ከተማመንን፣ በምን መንገድ ላግዝ የሚለው አይቸግርም። ስኳር ሦስት ማንኪያ የሚያደርግ ከሆነ፣ አንዷን ሲተው ለራሱም ጤንነት ነው ለሌላውም ያቀምሳል። ማንም ሰው መስጠት አልችልም ሊል አይችልም፣ ይህን ለማድረግ አቅም አነሰኝ ማንም እንደማይል ነው።

የመቄዶንያው ቢንያም ‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው› ይላል። ስለዚህ ሁሉም ሰው መሳተፍ የሚችልበት እድል ነው ብዬ አስባለሁ። በነገራችን ላይ የእኛ የእርዳታ አሰባሰብ ለየት የሚለው በነጠላ አንድ ሳሙና ጭምር ስለምንቀበል ነው። በወር ውስጥ አንድ ሳሙና ብቻ አንድ ሰው ቢሰጥ ትልቅ ነገር ነው። ማንም ሰው ላለመስጠት የለኝም የሚል ምክንያት የሚሰጥት አይደለም። ዋናው የሚያስፈልገው የልብ ቅንነት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here