እንቅስቃሴን በፈረቃ

0
478

ኮቪድ 19 ወረርሽኝ የዓለምን መልክና ቁመና ከቀየረ ዋል አደር ብሏል። በተለይ ደግሞ ከመዘናጋትም ይሁን ከሌሎች ካላወቅናቸው ተግባራት አንጻር ብቻ ባደጉት እና ምጣኔ ኃብታቸው በጎለመሰው አገራት ላይ ነው አነጣጥሮ ዕልቂቱን ያከናወነው። ወረርሽኙ ከተከሰተ እና ውስጥ ለውስጥ ስሩን ከሰደደ በኋላ ታዲያ የነቁት ሊመልሱት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰው ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ እንደሆነ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እየዘገቡት እኛም እየተሳቀቅን እንገኛለን። የከፈሉትን ዋጋ ለተመለከተ ነግ በእኔ በሚል ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ቅድመ ዝግጅት ባላቸው የአገራት የምጣኔ ኃብት እና የመንግስት የጤና ፖሊሲ በመመርኮዝ ሲንቀሳቀሱም እየተስተዋለ ነው።
ይህ ታዲያ በየትኛውም የዓለም አቅጣጫ ቢኬድ መሸሸጊያ ወይም ነጻ መሬት የማይገኝለት ወረርሽኝ እኛንም ስጋት ውስጥ የከተተን ይመስላል። መንግስት የሚቻለውን በማድረግ ከለጋሽ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ከፍ ሲልም ከዓለም አአቀፍ ድርጅቶች ደጅ እየጠና አስፈላጊውን ግብዓት እያሰባሰበ እና ችግሩ ለሚጠናባቸው ዜጎች የሚደርስበትን ሃብት እያሰባሰበ ይገኛል። ከሃብት ማሰባሰቡ ባለፈም በደህናው ጊዜ ኢትዮጵያ ስትተዳደርበት የነበረውን መደበኛ ሕግ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመተካት ወረርሽኙን እንቅስቃሴ ለመግታት ላይ ታች ሲል እየተስተዋለ ይገኛል።
በዚህ ወቅት ታዲያ ከዚህ ቀደም መብራት እና ውሃ በፈረቃ ሲያገኝ ነበረው ሕዝብ እንቅስቃሴውም በፈረቃ እንዲሆን ታውጇል። በፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ባሳለፍነው ሳምንት የወጣው እና በተገባደደው ሳምንት መጀመሪያ ተግባራዊ የሆነው የተሸከርካሪዎች በሙሉ ቁጥር እና ጎዶሎ ቁጥር የሰሌዳ ቁጥር እቅስቃሴ ታዲያ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስር በትራንስፖርት ዘርፉ በርካታ መዘርዝሮች የወጡ ሲሆን በአዲስ አበባ በኮድ 2 ተሸከርካሪዎች ላይ የወጣው እና ሰሌዳ ቁጥራቸው የመጨረሻ ቁጥር ሙሉ እና ጎዶሎ የሆኑ ተሸከርካሪዎች በሳምንቱ ሦስት ሦስት ቀናት ተወስኖላቸው እንዲንቀሳቀሱ ተደርገዋል።
ይሁን አንጂ አዋጁ ለሕክምና ባለሙያዎች እና ለሚዲያ ሰዎች የልዩ ፈቃድ በማግኘት ኹሉንም ቀናት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ አስቀምጦ ነበር። ይሁን እንጂ የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የልዩ ፈቃድ ተጠቃሚ ይሆናሉ ያላቸው አካላት ለማስተናገድ ረጅም መንገድ በመፍጠሩ እና ብዙ ቀናትን በማስቆጠሩ ከፍተኛ ትችትና ቅሬታ በተለያዩ ሰዎች ሲቀርብበት ሰንብቷል።
ከዚህም ባለፈ ፈቃድ ለመጠየቅ በሚኬድበት ስፍራ ያለው መጨናነቅም እቅስቃሴውን ለመግታት ከታሰበበት የወረርሽኙን የመቆጣጠር አላማ እጅግ የተራራቀ እንደሆነ አዲስ ማለዳ በስፍራው ተገኝታ ለመታዘብ የቻለችው ጉዳይ ነው። ይህ ብቻ ሳይበቃ ፈቃድ ለመስጠት በኃላፊነት ስፍራ ላይ የተቀመጡ ሰዎች ከአሰራር ውጪ በዕጅ መንሻ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ግለሰቦች ሳይሆን በየትኛው መስፈርት ፈቃዱ ለማይገባቸው ግለሰቦች እየተሰጠ ነው የሚሉ ቅሬታዎች በመኅበራዊ ትስስር ገጾች ሲስተጋቡ ሰንብተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here