በኦሮሚያ ክልል ዱከም ከተማ የሚገነባው እና በኢትዮጵያ ትልቁ የነዳጅ ዴፖ ግንባታ በበጀት እጥረት ምክንያት በታቀደለት ጊዜ ለማስጀመርና በተቀመጠለት ቀነ ገደብ ለማጠናቀቅ እንደማይቻል የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ደረጃ ስራ ማለትም የፕሮጀክቱ የምህንድስና ዲዛይን ጥናት በታቀደለት ጊዜ የተከናወነና መዘግየት ያልገጠመው ቢሆነም ቀጣዩ ስራ የ30 ወራት( ሁለት ዓመት ከግማሽ) ሊወስድ ይችላል የተባለለት የፕሮጀክቱ ቀጣይ ስራ ማለትም ከጨረታ እስከ ግንባታ ማጠናቀቅ ያሉት ተግባራት ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያስፈልግ በቂ በጀት ያልተገኘ በመሆኑ ማካሔድ እንዳልተቻለ ለማወቅ ተችሏል። ጀክምሩ ግንባታው በታቀደለት መሰረት በህዳር 2012 ይጀመራል ተብሎ ቀን ቢቆረጥለትም የፕሮጀክቱ ግንባታ አልተጀመረም፡፡
ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በአለም አቀፍ ደረጃ እንቅስቃሴዎች ከመገታታቸው ባሻገር የዓለም ምጣኔ ሀብት በራሱ አደጋ ላይ ከመውደቁ ጋር ተያይዞ ፋይናንስ ማፈላለጉና በጋራ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ያሳዩ በውጭ ድርጅቶች ዘንድ ያለው ተነሳሽነት በእጅጉ በመቀነሱ የግንባታ ፕሮጀክቱን በታቀደው መሰረት ለማስቀጠል ሌላኛው ፈተና መሆኑን የድርጅቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ ሕግ አምላክ ተሰማ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል የፕሮጀክቱ የኢንጅነሪንግ ዲዛይን ለማከናወን ጨረታውን ያሽነፈው ስሜክ የተሰኘ የአውስትራሊያ ድርጅት የኢንጅነሪንግ ድዛይኑን ጥቅምት/2012 አቅርቦ የነበረ ሲሆን፣ በቀረበው የኢንጅነሪንግ ዲዛይን መሰረት ቀጣይ ስራ ጨረታ በማካሄድ የስራ ተቋራጮች መቅጠርና ግንባታውን ማከናወን ቢሆነም ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልግ በጀት ለማግኘት ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ፋይናንስ የማፈላለግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በ150 ሚሊዮን ዶላር ወጭ የሚስገነባው የዱከም ነዳጅ ድፖ እንዲጀመር በተያዘለት ጊዜ ካለመጀመሩ በተጨማሪ ድፖውን ለመገንባት እየተሰራ ያለው የስራ ሂደት መቆሙንም የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ታደሰ ኃይለማሪያም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ የግንባታ ፕሮጀክቱ የዘገየበት ምክንያት የኢኮኖሚ እጥረት መሆኑን የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አክለው ተናግረዋል ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የነዳጅ ፍጂታ የማስተናገድ አቅም ያለው ዘመናዊ ዴፖ ለመገንባት ድርጅቱ በኦሮሚያ ክልል በምትገኘው ዱከም ከተማ በአስር ሄክታር ስፋት ያለው መሬት ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ተረክቦ ግንባታውን ለማስጀመር አስፈላጊ ቅድመ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በሳለፍነው ዓመት የገለጸ ቢሆንም የግንባታ ስራውን ኢትዮጵያ በገጠማት የገንዘብ ችግር እንደዘገየ አዲሰ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡
የዱከም ዴፖ ፕሮጀክት 12 የማጠራቀሚያ ጋኖች የሚኖሩት ዘመናዊ ዴፖ ሲሆን 300 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ የመያዝ አቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ዴፖው ነዳጅ ከባቡር ፉርጎዎችና ከነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ማራገፍና መጫን እንደሚችል ተነግሮለታል፡፡
የዱከም ዴፖ ፕሮጀክትወደ ስራ ሲገባ የአገሪቱ አጠቃላይ ነዳጅ የማጠራቀም አቅም ከ367 ሺህ ሜትር ኩብ ወደ 667 ሺህ ሜትር ኩብ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 336‚000 ሜትር ኩብ የአገሪቱን የነዳጅ ፍጆታ ለ35 ቀናት የሚሸፍን ሲሆን፣ 667‚000 ሜትር ኩብ ደግሞ የ65 ቀናት የነዳጅ ፍጆታ እንደሚሸፍን ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል የአለም የነዳጅ ዋጋ በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ታይቶ በማይታወቅ የዋጋ ቅናሽአሳይቷል፡፡ ኢትዮጵያም ይሄንን አጋጣሚ ተጠቅማ ከጊዜያዊ ፍጆታ በዘለለ ለማከማቸት እየሰራች መሆኑን ነዳጅ አቅራቢ ድረጅት አስታውቋል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012



