ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ህፃናትና ታዳጊዎች እራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቁ ያስተላለፉት መልዕክት

0
634

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ህፃናትና ታዳጊዎች እራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቁ መልዕክት አስተላለፈዋል።

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ሕጻናትና አዳጊዎች

ዛሬ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል መንግሥታችሁ ምን እየሠራ እንደሆነ፣ ከእናንተም ምን እንደሚጠበቅ ለእናንተ ለመግለጥ እፈልጋለው። ይህ መንግሥት የእናንተ የልጆችም መንግሥት ነውና።

ልጆች

የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ የመጣ ወረርሽኝ ነው። ከቻይና ተነሥቶ ዓለምን እያዳረሰ ነው። ብዙ ሀገሮች ዜጎቻቸውን በሞት አጥተዋል። በኛም ሀገር 126 ያህል ኢትጵያውያን በቫይረሱ ተይዘውብናል።

አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አንዱ መከላከያ ነው። አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ማለት ከሌላ ሰው በአራት የልጆች ርምጃ ርቆ መቆምና መቀመጥ ነው።

እጅን ደጋግሞ በሳሙና መታጠብ ሁለተኛው መከላከያ ነው። ልጆች ጠዋት ስትነሡ፣ ስትጫወቱ ፣ ከተጫወታችሁ በኋላ፣ ከምግብ በፊትና በኋላ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በሳሙና ታጠቡ። ስትታጠቡ ጣታችሁን፣ መዳፋችሁን፣ በጣታችሁ መካከል ፣ የእጃችሁን መዳፍ ፈትጋችሁ በውኃና በሳሙና ታጠቡ።

ትምህርት ቤት ተዘግቶ ቤት ነው ያላችሁት። አደራ ከቤት አትውጡ። ትቤት የተዘጋው በንክኪ ምክንያት እንዳይተላለፍባችሁ ብለን ነው። እናንተ ለነገዋ ኢትዮጵያ በጣም ታስፈልጓታላችሁ። ስለዚህ ጤናችሁን ጠብቁ።

ቤት መዋል ሊሰለቻችሁ ይችላል። ግን እንዳትታመሙብን፣ እንዳትሞቱብን ብለን ነው። ቤት ስትሆኑ አጥኑ፣ መጽሐፍ አንብቡ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ሥሩ፣ የልጆችን ጨዋታ ተጫወቱ።

ተጠንቀቁ እንጂ አትጨነቁ። ዐዋቂዎች የተለያዩ መረጃዎችን ሲነጋገሩ እየሰማችሁ ልትጨነቁ ትችላላችሁ። ወላጆቻችሁ ሲወያዩ እናንተን እንዲያስቡ እንነግራቸዋለን። ነገሩን በእናንተ ቋንቋ እንዲያስረዷችሁ አደራ እላቸዋለሁ።

አይዟችሁ፤ ይሄን ከባድ ጊዜ እናልፈዋለን፤ ፈጣሪ እናንተን ይሰማልና ለኢትዮጵያ ጸልዩ።

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here