በኢትየጵያ የተከሰተውን የፖለቲካ ለውጥ የሚመለከቱ በርካታ መጽሐፎች ገበያ ላይ ውለዋል። ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) ከነዚህ መካከል አንዱን መርጠው በአጭሩ ይዘቱን ያስዳስሱናል።
የመጽሐፉ ርዕስ፦ የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት በኢትዮጵያ፡ የለውጥ ማዕበል ዐቢይን የወለደውና ዐቢይ ጉዳይ እና ቀጣይ ስጋት
ደራሲ፦ ኤፍሬም ግዛው እና ውብነህ እምሩ
የታተመበት ጊዜ፦ 2011
አሳታሚ፦ ኤክስትሪም አታሚ
‘ታሪክ ሁልጊዜ በአሸናፊዎች ይጻፋል’ የሚለው ብሒል በእኛ አገር ቦታ ሳይገኝ የሥልጣን መንበር ላይ የወጡም ከመንበሩ ተፈንግለው የወደቁም ታሪክን ይጽፋሉ። በጦር ሜዳ የድል ፅዋ የጠጡም፣ በሽንፈት የተመለሱም ታሪክን ይጽፋሉ። ድርሳን ይደርሳሉ፤ ዜና መዋዕል ያዘጋጃሉ። በኢትዮጵያ ታሪክ የአሸናፊዎች እና የተሸናፊዎች ንግግር ይመስላል።
ያለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ ትዕይንታዊ ባሕርይ እየተላበሰ የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ ብዙ መጽሐፎች እየተጻፉ ነው። አብዛኞቹ መጽሐፍት የለውጥ አራማጅ የተባሉትን ባለሥልጣናት ምስል ከአጓጊ ርዕሶች ጋር አያይዘው ወደ መጽሐፍት ገበያ እየተቀላቀሉ ነው። የመጽሐፍቱ ይዘት እና ጥራት በእጅጉ አጠያያቂ እንደሚሆን የተወሰኑ መጽሐፍቶችን ተመልክቶ ማረጋገጥ ይቻላል። ብዙዎቹ ጠዋት ተጽፈው ማታ ለገበያ የሚቀርቡ ይመስላሉ። ስንዴውን ከእንክርዳዱ ሳንለይ ሁሉንም መኮነን ባይቻልም።
ከነዚህ የወቅቱን የፖለቲካ ለውጥ የመተንተን ዓላማ ይዘው ከተዘጋጁ መጽሐፍት መካከል “የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት በኢትዮጵያ” አንዱ ነው። መጽሐፉ ላለፉት ሦስት ዓመታት በአገራችን እየተከሰተ ያለውን ትግል እና ተውኔት መሰል አጓጊ የፖለቲካ ለውጥ በታሪክ ሰንሰለት እና ዐውድ ውስጥ እያስቀመጠ ይተርካል። የፖለቲካ ለውጡን ከአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ አንፃር ይገመግማል፤ ልዩነቱን ነቅሶ ያወጣል። የፖለቲካ ለውጡን አዲስ ባሕርያት የፖለቲካ ንድፈ ሐሳቦችን ከኹነቶች እያሰናሰነ ያስረዳል። የአገራችን የፖለቲካ ተስፋዎች እና ስጋቶች ከዝርዝር ምክረ ሐሳብ ጋር ያስቀምጣል።
የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት ከማውጫው ከተቀነሰው መግቢያ ጨምሮ ከመቅድሙ ጋር በዐሥራ ሦስት ምዕራፎች፣ በ380 ገጽ፣ ለአንባብያን ቀርቧል። የደራሲዎቹ ዋና አትኩሮት ያለፉት ሦስት ዓመታት ሲሆን፣ ዓላማቸው በመቅድም ውስጥ እንዳሰፈሩት “…እነዚህን የጭንቅ፣ የምጥና የመከራ ሦስት ዓመታትን ተከትሎ በአገራችን አዲስ ለውጥ እና አዲስ ምዕራፍ ሲመጣ፣ እንዲሁም ለውጡን ተከትሎ የተከሰቱና የታዩ ኩነቶችን ተደምረው፣ አንድም እውነታውን ለማስቀመጥ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቀጣዩ ጊዜያት ለሚመጣው ትውልድ ትንሽ መረጃ አኑሮ…” ለማለፍ ነው። ምን አልባት በዚህ መልክ መረጃ የማኖራቸው እና የፖለቲካ ለውጡን ዝርዝር ሒደት መዝግቦ ማስቀመጥን እንደመነሻ ግብ አድርገው ቢነሱ ከላይ የጠቀስናቸው ገበያውን የሞሉት መጽሐፍት ሚዛን ይደፉ ነበር።
የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት አብዛኛው የመጽሐፉ ክፍል ሥልጣን እና የሥልጣን ሽግግር፣ እርካብ፣ ኮርቻ እና መንበር በሚሉ ፈሊጣዊ ፅንሰ ሐሳቦች በመጠቀም፣ ሥልጣን ማዕከል አድርጎ ረጅሙን የኢትዮጵያ ታሪክ ይዳሰሳል። ሥልጣን ላይ አወጣጥን፣ አጠቃቀምን እና ቆይታን ከአክሱም እስከ አሁኑ የኛ ዘመን የፖለቲካ ሒደት ይዳሰሳል። ሥውር መንግሥት በአንድ ምዕራፍ የቀረበ ሲሆን የሥውር መንግሥት እና የሕዝባዊ መንግሥት ትግል አዲሱ በሥልጣን ዙርያ የሚደረግ ትግል ብቻ ሳይሆን ሥውር መንግሥት ወቅታዊ የአገሪቱ ፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ ፈተና መሆኑ ያስረዳል። ለዚህም ይመስላል በርዕሱ ውስጥ የተካተተው።
የመጽሐፉ አንዱ ጥሩ ጎን በዐሥራ ሦስት ምዕራፍ የተነተኑትን ጉዳዮች በመጽሐፉ ሽፋን ላይ ለመወከል የተሠራው ሥራ ነው። የመጽሐፉ ሽፋን ገጽ ስዕል አስተውሎ ለተመለከተ የስዕሉ ውክልና አንድ ምስል ሺሕ ቃላት ያስከነዳል የሚለው ብሒል ሐሳብ ያጠናክራል። በሽፋኑ ስዕል ማዕከል በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የተቀመጠ የሥልጣን መንበር ተቀምጧል። ወደ መንበሩ የሚወስደው ባለአምስት ደረጃ በቀይ ቀለም ደምቋል። በከባዱ ጨለማ ውስጥ በመጠኑ የተከፈተ በር ይታያል።
ሥልጣን እና የጨለማው መንበር
ጨለማው እና በጨለማው ውስጥ የተቀመጠው መንበር የመጽሐፉ ዋና ትኩረት የሆነውን የሥልጣን እና የሥልጣን ሽግግር ታሪክ እስከ ሥውር መንግሥት በኢትዮጵያ የሚወክል ይመስላል። የመጽሐፉ ባለብዙ ገጽ ምዕራፍ፣ ምዕራፍ ሁለት ከገጽ 35 እስከ 106 የሚወስደው ሲሆን የሥልጣን ሽግግር በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ የሥልጣንን ትርጉም ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕል እና የትርጉም ማግ እየመዘዘ ይተርካል። ከጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ተነስቶ የዘመናዊቷ እና የአሁኗን ኢትዮጵያ የሥልጣን ሽኩቻን፣ ትግልን እና ፉክክር ይተነትናል። ይህ የሥልጣን ሹኩቻ ሽግግሩን በደም የተቀባ፣ የሥልጣን ቆይታን ትርጉምና ፅድቅ አልባ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን የፖለቲካ ነቀርሣ እንዳደረገው ያስረዳል። ምናልባትም በዶ/ር መረራ ጉዲና አገላለጽ የአገሪቱ “የፖለቲካ ቡዳ ” በሥልጣን ዙሪያ ያሉ ሹክቻዎች እና ጦርነቶች እንደሆነ መጽሐፉ ይሞግታል።
የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት የአገሪቱን ረጅም ታሪክ የሥልጣን ጉዳይ ሲረብሸው እና ሲያሻክረው፣ መንገዱን አስቶ ቁልቁል ሲያወርደው እንደ ነበረ ታሪክ እያጣቀሰ ይተነትናል፤ ይሞግታል። የመጽሐፉ ዋና ንድፈ ሐሳባዊ እና ፅንሰ ሐሳባዊ መዋቅር መነሻ ደራሲው በግልጽ ያልተገለጸው ወይም ዲራዓዝ በሚል ብዕር ሥም የዶ/ር ዐቢይ ነው የሚባለው “እርካብና መንበር” በሚል ርዕስ በሰፊው እየተሰራጨ ያለ መጽሐፍ ነው። ሥልጣን የመጽሐፉ የመመልከቻ መነፅር እና የትረካው ዋና መቅዘፊያ ነው። ከተጠቀሰው መጽሐፍ መንበር፣ ኮርቻ እና እርካብ ዓይነት ፈሊጣዊ ፅንሰ ሐሳቦችን ይዋሳል። የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት ሥልጣን ላይ አትኩሮ የታሪክን ሒደት በመተንተኑ የዚህን መጽሐፍ የፍልስፍናውን መንፈስ ወርሷል። ከዚሁ መጽሐፍ ተውሶ የኢትዮጵያ ሥልጣን ባሕርያት ማለትም “ቅርፁ በወታደራዊ አቅሙ የተመካ፣ በሃይማኖት የተደገፈ፣ ከጀብዳዊ ቅንነት ይልቅ በጀብዳዊ ጭካኔ የሞላበት” እንደሆነ ገልጾ ይህን በረጅሙ የታሪክ ንፅረ ዕይታ ውስጥ ያሳየናል። ይህ የሥልጣን ባሕርይ የአገሪቱን የታሪክ፣ የሥልጣኔ፣ የነጻነት እና የድህነት ዛቢያ ነው ይለናል። ምንም እንኳን የተለየ የሥልጣን ፍልስፍና እንደ ገዳ ዓይነት ቢኖርም ገዢው የሥልጣን አያያዝ ይኸው ጅብደኛው የሥልጣን ፍልስፍና ነው ይለናል። ለዚህም ይመስላል ይህ ጀብዳዊ በደም የተሞላ የሥልጣን ኮርቻ በመጽሐፉ ሽፋን ስዕል ላይ ወደ ሥልጣን በሚወስደው ቀይ ደረጃ የተመሰለው።
የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት የዚህን ጀብዳዊ ሥልጣን “ወገንተኝነቱን፣ ግለኝነቱን፣ ቡድንተኝነቱን እና ሚዛናዊነት የጎደለው እንደነበር” እያሳየ ኢትዮጵያን ችግር ከዚህ እየቀዳ የሚተነትንልን። የኢትዮጵያ ታሪክ ከአክሱም እስከ ዛጉዌ፣ ከዛጉዌ እስከ ጎንደር፣ ከጎንደር እስከ ዘመነ መሳፍንት፣ ከዚያም ከቴዎድሮስ እስከ ኃይለስላሴ፣ ብሎም ከደርግ እስከ አሕአዴግ መለያ ባሕሪው “የመጨፍለቅና የመግደል ሽግግሮች፣ የሴራ ፖለቲካ የተሞላበት፣ በሥልጣን ኮርቻ ለመውጣት የሚያደርግ ፍፃሜ እንደሆነ ያትታል። በዚህ ፍልሚያ ደም እና ሞት የማይለየው፣ ክብር የጎደለው ብቻ ሳይሆን “ሠላምን፣ ፍትሕን፣ ልማትን፣ ብልፅግናን፣ እኩልነት እና ነፃነትን” ያላመጣ የሥልጣን ፍልስፍና ነው ይለናል። ለዛም የሽፋኑ ገጽ ላይ ያለው የጨለማው መንበር ሁነኛ ኢትዮጵያ ሥልጣን ፍልስፍና ተምሳሌት ሆኖ የቀረበው።
በመጠኑ የተከፈተው በር
በከፊል የተከፈተው በር የሚገባው ብርሃን አንድ ቁጥር በሽፋኑ ላይ አኑሯል። አንድ ቁጥር የጀማሪ ምልክት ናት። ብርሃን የተስፋ ተምሳሌት ነው። በቅርቡ በምንሰማቸው ትርክቶች እንደ መዝጊያ በር በሰምና ወርቅ ደምቆ የወጣ ቁስ የለም። የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት በምዕራፍ ዐሥር “የተዘጉ በሮች” በሚል ብዙ በሮች እየተከፈቱ እንደሆነ ይተርካል። የዲሞክራሲ በር፣ የኢሕአዲግ የውስጥ በር፣ የተፎካካሪ ድርጅቶች በር፣ የዲያስፖራ በር፣ የተስፋና የሕዝብ በሮች ሲከፈቱ በሚል ሰፋ ባለ አቀራረብ አዲሱን የፖለቲካ ለውጥ ይተርካል። በር፣ ብርሃን እና አንድ ቁጥር የተስፋውና የጀማሪው የለውጥ ተምሳሌቶች ሆነው ቀርበዋል። ይህ ለውጥ ጀብዳዊ የሥልጣን ሽግግር ታሪክ የቀየረ፣ ሠላማዊ ሽግግር እንደሆነ እና በዚህ የታሪክ ሒደት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ያመሰግናል። በዚህ በተከፈተ መልካም ዕድል ላይ በመሥራት የአገሪቱን የታሪክ ሸክም ማቅለል ይቻላል ይለናል። ከምዕራፍ 4 እስከ ምዕራፍ 10 ከሕዝባዊ እምቢተኝነት እስከ አዲሱ “የለውጥ አመራር” መምጣት የተደረጉ ኹነቶች በተለያዩ ርዕሶች ሥር ይዳስሳል። በነዚህ ምዕራፎች ከሕዝባዊ ተጋድሎ እስከ ኢሕአዲግ ውስጣዊ ትግሎች በመዘርዘር የአዲሱን ዘመን መወለድ ያካትታል። ይህን አዲስ ዘመን የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት የፍቅር፣ የአንድነት፣ የእርቅ እና የተስፋ ዘመን ይለዋል።
ሥውር መንግስት ወቅታዊው የጨለማ መንበር
የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት ለውጡን በመተንተን አይቆምም። በምዕራፍ 11 እና 12 የሥጋት ምንጭ ሆነው “የሥውር መንግሥት” በኢትዮጵያ ከሰኔ 16 የቦንብ ጥቃት ምንነት፣ ተምሳሌትነትና ፖለቲካዊ አንድምታ ጋር በማያያዝ አቅርቧል። የሰኔው የቦምብ ጥቃት ጀብዳዊ የሥልጣን ሹኩቻ ታሪክ ማሳያ እንደሆነ ይሞግታል። ጥቃቱ ለውጡን ወደ ጀብዳዊ የሥልጣን አዙሪት ለመመለስ የሞከረ እንደነበረ ያስረዳል።
በተለይም ጥቃቱ ለፖሊስ እና ደኅንነት ኃይሎች የሰጠውን ትርጉምና ተሞክሮ ይተነትናል።
በመጽሐፉ ሽፋን ላይ የተቀመጠው የጨለማው መንበር በምዕራፍ 12 የቀረበው የሥውር መንግሥት ባሕሪ ተምሳሌትም ይመስላል። የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት “ሥውር መንግሥት” የጀብዳዊ የሥልጣን ፍልስፍና ወቅታዊ የበኩር ልጅ እንደሆነ ያስረዳል። በዚህ አካራካሪ ምዕራፍ ጀብዳዊ የሥልጣን ተዋኒያን ሕቡዕ ገብተው የፖለቲካውን ሒደት በጨለማ ፖለቲካ ሊመሩት ይፈልጋሉ ይለናል። ዓለም ዐቀፋዊ ተሞክሮች በተለይም ከቱርክ ታሪክ እስከ ግብፅ ወቅታዊ ሁኔታ አቅርቦ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ስጋቶች ያትታል። የብዙ አገሮች ተሞክሮ በወፍ በረር እየቃኘ የሥውር መንግሥት እርሾ የሆነውን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሁኔታ ብሎም የሥውር መንግሥት የማምከኛ መንገዶች ይዳስሳል።
የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት በምዕራፍ 13 ተስፋና ስጋቶች በሚል ርዕስ የዘመናችን ፈተናዎች እና የፖለቲካ መልካም ዕድሎች ዘርዝሯል።
ይህ መጽሐፍ የዛሬ ታሪክ ነው፣ የዛሬ ችግርና ስጋት ላይ ቆሞ በትናንት ድሮነቱ ውስጥ ይዞን ይሄዳል። ይዞን ሄዶ መልሶ ዛሬ ላይ ያመጣናል። በተስፋ እና በስጋት መካከል አቁሞ መልካም የሚለውን መንገድ ይጠቁመናል። የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት የኢትዮጵያን ታሪክ በካርል ማርክስ የታሪክ ንድፈ ሐሳብ ከጋርዮሽ እስከ ፊውዳል ስርዐተ ማኅበር ያደረገውን ሽግግር ይተነትን እና ያሁኗን በተለይም ድኅረ 1983 ኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመተንተን ማርክስን መጋበዝ አልፈለጉም። ረጅሙም የኢትዮጵያ ታሪክ በመደቦች መካከል ሳይሆን በሥልጣን ፈላጊዎች ትግል የተሞላ ታሪክ እንደሆነ ያስረዳል። በምርት ኃይል ሳይሆን የሥልጣን መንበርን ኮርቻ እና እርካቡን ለመቆጣጠር የሚደረግ ትግል ረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ችግር እንደሆነ ያስረዳል። ይህን ችግር ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር በማካሔድ የጀብዳዊ የሥልጣን አያያዝ አጠቃቀም ፍልስፍና ማቆም እንደሚቻል ሊያሳምነን ይሞክራል። ትግሉ ሠላማዊ በማድረግ ዲሞክራሲን ሀ ብሎ መጀመር ይቻላል ይለናል ። ለዚህም የገዳ ዓይነት ተሞክሮች ከቡራቡሬው ታሪካችን መቅዳት ይቻላል ይላል።
የሥልጣን ሽግግር እና ሥውር መንግሥት የኢትዮጵያን ችግር በከፊል በማርክሳዊ ትንታኔ አሳይቶ መፍትሔው በሊብራል ሐሳብ ያቀርባል። ዋናው ጥያቄ የሥልጣን ሽግግሩ ሠላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ማድረጉ እና ከሥውር መንግሥት እጅ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን እንዴት መንበሩን በሊብራል የምርጫ ዲሞክራሲ ብቻ ሕዝባዊ ማድረግ ይቻላል የሚለው ነው። እርካብ እና ኮርቻውን በምርጫ ማስያዝ ብቻ ሳይሆን ፈረሱ በሕዝባዊ መንገድ፣ ወዴት፣ እንዴት ይጋልብ የሚለው ጥያቄ ወቅታዊ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።
መጽሐፉ ያነሳው ቀልብ ሳቢ፣ ስሜት ኮርኳሪ አገራዊ ጉዳይ በውስጥ ያሉ ፅንሰ ሐሳባዊ ሕፀፆች፣ ንድፈ ሐሳባዊ ተቃርኖውች እና የአርትኦት ችግሮች በዚች ጽሑፍ ላይ ብዙም ላለማተኮር መርጫለሁ።
ሕዝባዊ ፖለቲካና ዴሞክራሲ ይለምልም!
ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስ እና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህር ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው yonniashine2010@gmail.com ማግኘት ይቻላል።
ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011