በተለምዶ ሜቴክ ተብሎ የሚጠራው የብረታ ብረት ኢንጅነሪነግ ኮርፖሬሽን (ብኢኮ) አካል የሆነው ኅብረት ማምረቻ ኢንዱስትሪ የቀድሞ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና የኮርፖሬሽኑ የሥራ ዘርፍ ኃላፊ ሻለቃ መስፍን ስዩም በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ትናንት ዓርብ፣ ታኅሣሥ 5/ 2011 ፍርድ ቤት የቀረቡት ሻለቃው፤ ሰባት ነጥብ ዘጠኝ ሚልየን የሚጠጋ ገንዘብ በማባከን ተጠርጥረዋል፤ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት የተያዙበትን ምክንያት እንደማያውቁ ገልጸዋል። ይህንን የተረዳው ፍርድ ቤቱ ለሰኞ ታኅሣሥ 8/ 2011 እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
የሜቴክ የቀድሞ ኃላፊዎች ላይ ይህ አይነቱ ክስ ሲቀርብ የመጀመሪያው አይደለም።
የብረታ ብረት ኢንጅነሪነግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ክንፈ ዳኘው ከወር በፊት መታሰራቸውና ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወቃል። ከሁለት ሳምንት በፊት በነበረ የፍርድ ቤት ውሎ ዳይሬክተሩ የተጠረጠሩባቸው ግዥዎች ተለይተው ለፍርድ ቤት መቅረቡ ይታወሳል፡፡
በቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የኢንዱስትሪን ዘርፍ ለማሳደግ በ10 ቢሊየን ብር የተቋቋመው ሜቴክ ኢትዮጵያ ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ጎን እንድተሰለፍ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተበሎ ተገምቶ ነበር። ይሁን እንጂ የተሰጠውን ሚና ችላ በማለት ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ስድስት ዓመታት 37 ቢሊየን ብር የውጪ አገር ግዢ መፈጸሙንና ሁሉም ግዢዎቹ ያለ ምንም ዓይነት ጨረታ እንደተከናወኑ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መገለጹ አይዘነጋም።
የውጪ አገር ግዢ ሲደረግ፤ ከኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች ጋር የሥጋ ዝምድና ወይም የጥቅም ትስስር ያላቸው በግዢዎቹ ላይ እስከ 400 በመቶ ድረስ የተጋነነ ወጪ ያደርጉ ነበር በማለት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለአብነትም በአንድ ድርጅት የ205 ቢሊዮን ብር ግዢ ያለ ጨረታ መፈጸሙን ተናግሮ እንደነበር አይዘነጋም።
ከሙስና ክስ ባሻገር፤ ባሳለፍነው ሳምንት፤ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሰብኣዊ መብት ጥሰት ወንጀል በተጠረጠሩ በእነ ጎሃ አጽብሃ መዝገብ ውስጥ 33 ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀን ታኅሣሥ 4 የተሰየመው ችሎት ፈቅዷል።
ፖሊስ እስካሁን ያከናወነውን የምርመራ ውጤት ለፍርድ ቤቱ ያቀረበ ሲሆን፥ ተጠርጣሪዎች ሰብኣዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ በመገናኛ ብዙኃን የተላለፈው ዘገባ እንደመቃወሚያ አቅርበዋል። ይሁን እንጂ ፍርድ ቤቱ ዘገባው የቀረበበት ሚዲያ በግልጽ ባለመገለጹ ምክንያት ትዕዛዝ ለመስጠት እቸገራለሁ ብሏል። ነገር ግን ተጠርጣሪዎች ማስረጃ በማንኛውም ሰዓት ማቅረብ እንደሚችሉም አስታውቀዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011