የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከ16 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለሚያስገነባቸው 10 የመንገድ ፕሮጀክቶች ከተቋራጮች ጋር ሥምምነት ተፈራመ።
ታኅሣሥ 4/2011 በነበረው የሥምምነት ፊርማ ሥነ ስርዓት ላይ እንደተገለጸው በተለያዩ አካባቢዎች ይገነባሉ የተባሉት 10 የመንገድ ፕሮጀክቶች ጠቅላላ ርዝመት 724 ኪሎ ሜትር ነው።
መንገዶቹን ለመገንባት በአምስት አገር በቀልና አምስት የውጪ ሥራ ተቋራጮች ጨረታውን አሸንፈው ከባለሥልጣኑ ጋር ሥምምነት ፈርመዋል። መንገዶቹን ገንብቶ ለማጠናቀቅ እንደየግንባታዎቹ ስፋት የኮንትራት ጊዜው የሚለያይ ቢሆንም ረጅሙ የጊዜ ገደብ ሆኖ የተቀመጠው አራት ዓመት ከአምስት ወር መሆኑ ታውቋል። ትንሹ የጊዜ ገደብም ሁለት ዓመት ሆኗል።
መንገዶቹ ካላቸው ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳና ማኅበራዊ ጠቀሜታ አንፃር ታይቶ ከዚህ ቀደም ከነበሩበት የአስፋልት እና የጠጠር መንገድ ደረጃ አሁን ወደ ተሻለ የአስፋልት ደረጃ ከፍ ተደርገው የሚገነቡ ናቸው። ከጎሬ ማሻ ቴፒ መንገድ ፕሮጀክት በስተቀር ሌሎቹ ዘጠኝ የመንገድ ፕሮጀክቶች ወጪ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን እንደሆነ ባለሥልጣኑ አስታውቋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011