ምርምርና ፈጠራን ያነሳሳው ኮቪድ 19

0
716

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ (AASTU) የቴክኖሎጂ ለውጦችና ሽግግሮችን የማድረግ እቅዱን ይፋ ያደረገው ከወራት በፊት የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ወር ላይ ነበር። እነዚህም ለውጦች የማኅበረሰቡን ሕይወት በበጎ ጎን የሚቀይሩ እንደሚሆኑ አጽንኦት መስጠቱንም የተለያዩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

በዛው ጊዜ ታድያ ዩኒቨርስቲው የምርምርና የፈጠራ ማእከል እንደሚከፍት ይፋ አድርጎ ነበር። ማእከሉንም አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ለማሟላት የደረሰበትን ደረጃም አስረድተዋል። አምስት ኮሌጆችን አቅፎ በያዘው ዩኒቨርስቲው (አርክቴክትና የሲቪል ምህንድስና፣ የባዮሎጂና ኬሚካል ምህንድስና፣ ኤሌክትሪካልና ሚካኒካ ምህንድስና፣ የተፈጥሮና ማኅበራዊ ሳይንስ እንዲሁም አፕላይድ ሳይንስ ኮሌጆቹ)፣ የምርምርና ቴክኒክ ሽግግር ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዝዳንት ግርማ ጎንፋ (ፒኤችዲ) ከአዲስ ማለዳ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል።

አስቀድሞ ዩኒቨርስቲውንና ምርምርን በሚመለከት ሊሠራው ያለውን ማእከል በሚመለከት ከተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ዩኒቨርስቲው ለምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች 42 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለዩኒቨርስቲና ኢንዱስትሪ ትስስር 2.6 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀው ነበር። ለማኅበራዊ አገልግሎት ሥራዎችም በተመሳሳይ 1.7 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቁመዋል።

ታድያ በእነዚህ ሥራዎች ተማሪዎች እንዲሁም የትምህርት ቤቱ አባላት የሆኑ ሠርተኞች ሁሉ ሱታፌ አላቸው። ይህም በተለይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ተግባር ሥራ ሲገቡ የራሳቸው የፈጠራ ሐሳብ ጭምር ያላቸውና ባለ ብሩኅ አእምሮ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። በዩኒቨርስቲው የሚሠሩ የረጅም ጊዜ የእቅድ ሥራዎችም ለማኅበረሰቡ ጭምር ተጨባጭ ለውጥ ያመጣሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ደጋግመው ያነሳሉ።

ከፍተኛ የምትህርት ተቋማት አንዱ ግባቸው ይህ መሆኑ ግልጽ ነው። ምንአልባት ከኮሮና በፊት በነበረችው ኢትዮጵያ፣ እነዚህ የምርምር ተቋማት የሚያደንቅ እንጂ የሚደግፋቸው አልነበረም። አሁን በኮቪድ 19 ኮሮና ወረርሽ ምክንያት ግን ብዙዎቹ በተግባር የተፈተኑና በተግባርም አቅማቸውን ያሳዩ በመሆናቸው የመፍትሐየ ሐሳቦቻቸውም በዛው ልክ ተፈላጊ ሆነዋል።

በተለይም ለጊዜው አስፈላጊ የሆነውን ቬንትሌተር በመሥራት፣ የንጽህና መጠቢያ ሳኒታይዘሮችንም በማምረት በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጥናትና ምርምር ማእከላት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፣ አቅማቸውንም አሳይተዋል።

ሳኒታይዘር ሲነሳ፣ ይህ በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ይሁን እንጂ በግለሰብ ደረጃም በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ወጣት የኢንጂነሪንግ እና የተለያዩ ሙያተኞች የመሠረቱት የኒው ኢራ ሪሰርች ኤንድ ዴቨሎፕመንት ማእከል የፈጠራ ሥራ የሚዘነጋ አይደለም። ማእከሉ በኢትዮጵያ የኮረና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በባለሙያዎች የአገልግሎት ብቃቱ የተረጋገጠ ሜካኒካል የኦክስጅን ቬንትሌተር ሞዴል አዘጋጅቶ ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ማቅረቡ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ይህንኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዓለማችንን ሕዝብ ያጠቃና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ሕይወት የነጠቀ ወረርሽኝ ለመከላከል፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ኮሚቴ በማዋቀር ልዩ ልዩ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው ሙያተኞች የፈጠራ ሥራቸውን እንዲያቀርቡ ባወጣው የውድድር መስፈርት 446 ያህል ግለሰቦች እና ድርጅቶች ልዩ ልዩ ሞዴሎችን ሰርተው ማቅረባቸውን መገልጹ ይታወሳል። ከችግሩ አጣዳፊነት አኳያ ጥራት ላላቸውና ለኢንዱስትሪ ምርት ዝግጁ ለሆኑት ቅድሚያ በመስጠት እስከ መጪው ግንቦት ወር ውጤቱ በግልፅ ይፋ ይደረጋል ሲልም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

እነዚህ በአገር ልጅ በአገር ቤት የሚመረቱ ምርቶች ጥቅማቸው ቀላል አይደለም። በአንድ ጎን በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽ ምክንያት፣ በአስቸኳይ የሚያስፈልግ መሣሪያ በመሆኑ ቬንትሌተሮቹ በጊዜው ለሕክምና ማእከላት እንዲዳረሱ ለማድረግ የሚያስችል ነው። ከዛም ባሻገር መንግሥትን ከከፍተኛ ወጪ የሚያተርፉ ሲሆን፣ ከውጪ ከሚገባውና ወጪ ከሚደረገው ገንዘብ 90 በመቶ ያተርፋል የሚሉ መረጃዎችም ይፋ ተደርገዋል። ከዛም በተጓዳኝ መሣሪያዎቹ ሞዴል አድርገው ከወሰዷቸው በተሻለ፣ ለአጠቃቀም ምቹና ከባድ ያልሆኑ ሆነው የተመረቱ ናቸው።

አፍሪካ በዓለም ዐቀፉ የጤና ድርጅትም ሆነ የተለያዩ የጤና ተመራማሪዎች ቀጣይዋ የኮሮና ወረርሽኝ ማእከል ልትሆን ትችላለች እያሉ ነው። እንደሚባለው የሚሆን ከሆነና የቫይረሱ ስርጭት እየተስፋፋ ብሎም እየከፋ ከሄደ፣ ወባና ኮሌራን ያላጠፋች አፍሪካ፣ በቂ ቬንትለተሮች ከወዲሁ ካላዘጋጀች በቀር የሚጠፋው የሰው ሕይወትና የሚደርሰው ኪሳራ ለማሰብም የሚሲጋ ነው። ይህም እነዚህን የፈጠራና የምርምር ሥራዎች ሚናቸው በቀላል የሚታይ እንዳይሆን ያደርጋል።

እንደሚታወቀው ቬንትሌተር አሁን ከማንምና ከምንም በላይ ተፈላጊው መሣሪያ ሆኗል። መሣሪያው ለመተንፈስ የሚረዳ ሲሆን፣ ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ መተንፈሻ አካላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ቫይረስ እንደመሆኑ፣ አገልግሎቱም በዚህ የሚገለጥ ነው።

ታድያ እንኳን አፍሪካና የአውሮፓ አገራት አሜሪካ ሳይቀሩ በቂ ቁጥር ያለው ቬንትሌተር አላቸው ማለት አይቻልም። ይህም ችግር ሆኖ ተመልክተናል። በአፍሪካ ደግሞ እንደሚጠበቀው ነገሩ ይብሳል። ለምሳሌ ብንጠቅስ ዐስር የአፍሪካ አገራት አንድም እንኳ ቬንትሌተር የሌላቸው ሲሆን፣ አንድ ቬንትሌተርን በአንድ አገር ስንት ሰዎች ይጠቀማሉ የሚለው ንጽጽር በአፍሪካ ቢሠራ፣ አንዱን መሣሪያ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያገለግል ሆኖ ይገኛል። አሜሪካና ጣልያን ባላቸው ከፍተኛ የቬንትሌተር አቅም ሊቋቋሙት ያልቻሉትን ታድያ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራትስ እንዴት ይገፉታል የሚለው ጉዳይ ከስጋት የሚመነጭ ትክክለኛ ጥያቄ ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው በኮቪድ-19 ከተያዙት መካከል 80 ከመቶው ተጠቂዎች የሆስፒታል ውስብስብ ክትትል ሳያሻቸው ሊድኑ ይችላሉ። ነገር ግን ከ6ቱ በሽተኞች ቢያንስ አንዱ የመተንፈስ ችግር ሊያጋጥማት ወይም ሊያጋጥመው ይችላል። ይህም የሚሆነው ቫይረሱ ሳምባን የሚያጠቃ ስለሆነ ነው። በዚህ ወቅት ቬንትሌተር ከሌለ ግለሰቡን ማዳን የማይሆንና የማይታሰብ ነው።

የቬንትሌተር ነገር ከተነሳ ታድያ፣ ኹለት ዓይነት ቬንትሌተር ወይም እንደተባለው የቫይረሱ ተጠቂ እንዲተነፍስ የሚረዳ መሣሪያ አለ። አንዱ መካኒካል ቬንትሌተር ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ቱቦ-አልባ የሚባለው ቬንትሌተር ነው።

ይህንን የተለያዩ ጽሑፎች ሲስረዱና ሲያብራሩ እንዲህ አስቀምጠውታል፣ ‹‹መካኒካል ቬንትሌተር የአየር ቱቦ በአፍ በኩል እንዲገባ ተደርጎ ታማሚው ካርቦንዳይኦክሳይድ እንዲያስወጣና ኦክስጅን እንዲያስገባ የሚያደርግ ነው። ቱቦ-አልባው ቬንትሌተር ወይም በእንግሊዝኛው (Non Invasive Ventilator) ግን ወደ ሳምባ የሚወርድ ቧንቧ ሳይኖረው አፍና አፍንጫ ላይ በሚደረግ ጭምብል ብቻ የሚሠራ ነው።››

ታድያ ቫይረሱና ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዐቀፍ ደረጃም የፈጠራ ሥራን ቀስቅሷል ማለት ይቻላል። ለምሳሌም ቢቢሲ አማርኛ የዘገበውን ስናነሳ፣ የለንደን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ መሐንዲሶች ልምድ ይነሳል። እነዚህ መሀንዲሶች ‹ከመርሴዲስ ፎርሙላ-1› አቻዎቻቸው ጋር በመሆን አዲስ ዓይነት አጋዥ የመተንፈሻ መሣሪያ ለመሥራት ሙከራ ላይ ናቸው።

አፍሪካ በብዙ ነገር የታደለች አይመስልም። በድህነቷ ላይ ወረርሽኝ ሲታከል የሕዝቧን ኑሮ ምን ያህል ከባድ እንደሚዲርግና ቀና ለማለት የምታደርገውን ጥረትን መልሶ የሚያዳፍን ግልጽ ነው። በአንጻሩ ግን የቀሰቀሰው የፈጠራ ሥራ ቀላል አይደለም። ምንም እንኳ ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉት የአፍሪካ አገራት ቫይረሱን ለመከላከል ከውጪ ያገኙት ድጋፍ በእጅጉ ያገዛቸው ቢሆንም፣ የአገር ውስጥ እንቅስቃሴዎችም ሚናቸው የሚናቅ አይደለም።

ከላይ ለመጠቃቀስ እንደተሞከረው በኢትዮጵያም በግለሰብ እንዲሁም በማእከል ደረጃ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ እየተደረጉ ነው። ከእለት ወደ እለት የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችን ለመለየት የመመርመር አቅሟን እያሳደገች ያለችው ኢትዮጵያ፣ በየጊዜው የቫይረሱ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በሄደ ቁጥር የሕክምና መስጫ ግብዓቱም በዛው ልክ ያስፈልጋታል። ለዛም ነው እንደ እንግዳ ደራሽ የሆነውን ወረርሽኝ ለመግታት፣ በጥድፊያ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎችን ወደ ተግባ እንዲገቡ መፋጠን ያለባት።

ታድያ እንዳልነው በቫይረሱ ለተጠቂ ሰዎች የመተንፈሻ ችግር ሲገጥማቸው የሚያገለግለውን ቬንትሌተር በግለሰብ እንዲሁም በማእከል ደረጃ የሠሩ አሉ። ከእነዚህም መካከል አንዱ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ነው። አዲስ ማለዳ ከላይ የተነሱትን ነጥቦች መነሻ በማድረግና በማውሳት የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሳች ሲሆን፣ የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ከዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኒክ ሽግግር ተጠባባቂ ምክትል ፕሬዝዳንት ግርማ ጎንፋ (ፒኤችዱ) ጋር ተከታዩን አጭር ቆይታ አድርጋለች።

በዩኒቨርስቲው የጥናትና ምርምር ማእከል ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ቬንትሌተሮችን እየሠራችሁ እንደሆነ ይታወቃል። አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ማንስ ነው የተሳተፈበት?

በጊቢው የሚሠሩ መደበኛ ሥራዎች አሉ። ከዛ ውጪ በየሆስፒታሉ ያሉትን የሜካኒካል ቬንትሌተር ጥገና የሚሠራ ቡድን አቋቁመን ወደ ሥራ አሠማርተናል። እነርሱ ያንን እየሠሩ ነበር። ስለዚህ በውስጥ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ። ከዛ ውጪ ከአገር ዐቀፍ ቡድን ጋር በመጣመር የሚሠሩ/የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ። አሁን ሰዓት ተማሪዎች በጊቢ ስለሌሉ [በዚህ የቬንትሌተር ሥራ] መምህራንና ሠራተኞች ናቸው ያሉትና የተሳተፉት።

እንደ ጥናት ማእከል ከዚህ ቀደም የተሠሩና ችግር ፈቺ ሆነው የወጡ ሥራዎች ነበሩ?
በዩኒቨርስቲው የተሠሩ ብዙ ሥራዎች ነበሩ። ከኮቪድ 19 ጋር ያልተያያዙትም ብዙ ናቸው። ከወረርሽኙ ጋር የተገናኘ የሠራነውን ለመጥቀስ ግን የእኛ ዩኒቨርሲቲ ሳኒታይዘር ማምረት የጀመረው መጀመሪያ ነው። ለዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ፣ ለአካባቢው ሰዎችም ያንን ቅርበዋል። ዩኒቨርስቲው በወረርሽ ምክንያት እንደማቆያ ሆኖ ስለሚያገለግልም፣ በዛዛ ለሚቆዩና ለሕክምና ቡድን እንዲሁም በተመሳሳይ አከፋፍለናል። ከዛ ውጪ ጊቢ ውስጥ የእጅ መታጠቢያ ቁሳቁሶችን ሠርተናል፣ እነዚህም የእጅ ንክኪ የሚቀንሱ ሆነው የተሠሩ ናቸው።

ከዛ ውጪ የቬንትሌተር እጥረት ነበር። እሱን ማምረት እንችላለን የሚለውን ካሰብን በኋላ የተለያየ አማራጭ ይዘን በዛ ላይ እየሠራን ነው።
እዚህ ላይ ግን መታየት ያለበት ዩኒቨርሲቲ እስከ ተወሰነ ደረጃ ነው ሥራዎችን የሚያደርሰው። ከዛ ወስዶ አሳድጎ መፍትሔ እንዲሰጡ ለማድረግ ወደ ምርት የሚያስገባና አምርቶ የሚያወጣ ሌላ አካል ያስፈልጋል። በእኛ አቅምና ስፋት የመጀሪያውን ደረጃ እንሠራለን። ያንንም ለሚመለከተው አካል ነው የምናስረክበው፣ በስፋት ተመርቶ እንዲያገለግል። በዚህ ላይ ብዙ ሥራዎች አሉ። ወደፊትም ያንን ከሚያመርት አካል ጋር በመነጋገር ነው ወደ ምርት ደረጃ ነው የሚደርሰው።

ብዙ ጊዜ የምርምር ሥራዎችን መሥራቱ ሳይሆን ለተጠቃሚና ለሚያስፈልገው ማኅበረሰብ ማድረሱ ነው ፈተና የሚሆነው። ይህም በገንዘብ አቅም ምክንያት እንደሆነ ደጋግሞ ይነሳል። አሁን ላይ የፋይናንስ አቅም ምን ያህል ይፈትናል?

እርግጥ የፋይናንስ እጥረት በተወሰነ መልክ አለ። ከዛም በላይ ግን የእቃ አለመገኘት ነው ችግሩ። የእኛ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ነው። የሚስፈልግ ቁሳቁስ ብዙ ነው። ግን ገንዘብ ይዘን ብንወጣም እንኳ በቀላሉ ገበያ ላይ የምንፈልገውን አናገኝም። እንደሚታወቀው ደግሞ የመንግሥት ግዢ ስርዓት ረጅም ነው። በዛም መንገድ ረጅም ጊዜ ይሄዳል። ከገንዘቡ በላይ የእቃ አለመገኘትን የመንግሥት የግዢ ሂደት ረጅም መሆኑ ነው እየቸገረን ያለው።

አሁንስ ከዚህ ወረርሽኝ ጋር በተገናኘ የጥሬ እቃ ግብዓት ምን ያህል አግኝታችኋል?
ከኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ፣ ቬንትሌተሩን ለመሥራት የሞከርነው ገበያ ላይ ባሉና በሚገኙ ግብዓቶች ወይም እቃዎች ነው። ምክንያቱም ከውጪ እቃ ለማምጣት አሁን ዓለም ያለችበት ሁኔታ የተነሳ ጊዜ ስለሚፈጅ ነው። እናም ባለው ነገር እየሠራን ነው።

ግን እንደ አጠቃላይ ሲታይ ዩኒቨርስቲዎችም መንግሥትም ትኩረት ሰጥተው ግብዓቶችን በቀላል ማግኘት እንድንችል ማመቻቸት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
በተያያዘም አሁን ላይ ያለው የመንግሥት ትኩረት ጥሩ የሚባል ነው። በፊት ከነበረው አሁን ይሻላል። አንዳንድ ነገሮች ላይ ግዢ ስንፈጽምም በተሻለ እየተንቀሳቀስን ነው። ወደፊትም ይህ መቀጠል አለበት ብዬ ነው የማስበው። መንግሥትም ይህን ሊያስብበት ይገባል። ምክንያቱም ችግር ሲመጣ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ሠርተን ነው አገር መቀየር ያለብን።

አሁን ታድያ አንዳንድ ነገሮች ላይ፣ የፈጠራ ሥራዎችን ጨምሮ፣ በተሻለ እየተንቀሳቀስን ነው። ወደፊትም ይህ መቀጠል አለበት ብዬ አምናለሁ።
አሁን በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት የፈጠራ ሥራዎችን የመሥራት ሁኔታዎች ተነቃቅተዋል። ወደፊትስ በምን መንገድ መሄድ ያስፈልጋል ይላሉ?
ይህ [አሁን ያለው የመነቃቃት እንቅስቃሴ] መቀጠል አለበት። በሽታው እንኳ ቢሄድ፣ እንደ አገር ብዙ ችግሮች አሉብን። ለበሽታ ብቻ ሳይሆን ለአገር እድገትም ሥራ ያስፈልጋል። ሁሉም ተቋም በየፊናው መሥራት አለበት፣ ሁላችንም መሥራት አለብን። አንድ ችግር ሲሄድ ሌላ ችግር ይተካል።

አሁን እየሠራችሁ ያላችሁት መሣሪያ ሂደቱን አጠናቅቆ ለምርት ሲደርስ፣ አቅምና ደረጃው በምን መስፈርት ይለካል? ወደ አገልግሎት ለመግባት ብቃቱስ እንዴት ይረጋገጣል?

ምርቱ ካለቀ እኛ ለሚመለከተው አካል እንሰጣለን። ለሕክምና ተቋም ሊሆን ይችላል ወይም ለመንግሥት መሥሪያ ቤት። ስለዚህ ጥራቱን አረጋግጠው ነው ወደ ሥራ የሚገባው። ቀጥታ ወደ ሥራ የሚገባ ሳይሆን ጥራቱ በሚመለከተው አካል የሚረጋገጥ ይሆናል።

እንዳየነውና እንደሰማው በግል እንዲሁም በተለያየ ሁኔታ ቬንትሌተሮችን እየሠሩ ያሉ ባለሞያዎች አሉ። ከእነዚህ ሰዎችና ተቋማት ጋር የምትገናኙበትና የምትነጋገሩበት ወይም የምትመካከሩበት አውድ አለ?

እንደሚታወቀው የእኛ ምሩቃን የተለዩ ናቸው። ተማሪዎችን ስንወስድም ፈትነን ነው የምንወስደው፣ ትምህርት አጠናቅቀው ሲወጡም የእኛ ተማሪዎቻችን ጥሩ ናቸው። የራሳቸውን ሥራ የፈጠሩ ልጆች አሉ። ከእነርሱም ጋር እየተነጋገርን ነበር፣ አብረንም እየሠራን ነው።

ከእነርሱም ጋር ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ሐሳብ ያለው ሰው ካለ፣ ወደ እኛ ሊመጣ ይችላል። እኛም የምንችለውን ድጋፍ እናደርጋለን። እኛ ለብቻችን መሥራት ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ማበረታታትና ከሌሎችም ጋር የመሥራት ፍላጎቱ አለን።

ኢትዮጵያ ብዙ የተማረ እንዲሁም ወጣት የሰው ኃይል አላት። ያለውን አቅም እንዲህ ባለ መልክ ለማውጣትና ጥቅም እንዲሰጥ ለማድረግ ምን መደረግ አለበት?
እውነት ነው! የሰው ኃይል አቅም አለን። አስቀድሞ እንደጠቀስኩት ግን የአሠራር ችግሮች አሉ፤ ሰው እንዳይሠራ የሚያደርጉ። ከዛ ውጪ የግብዓት እጥረቶችም አሉ፣ ያንን መፍታት አለብን። እንዲሁም ደግሞ ማቀናጀት ያስፈልጋል። ድርጅቶችና ተቋማት መቀናጀት አለባቸው። ምክንያቱም ብቻችንን ሠርተን የምናመጣው ነገር የለም። ስለዚህ ቅንጅቱ ላይ የሚያስፈልጉ ነገሮች ከተሟሉ ብዙ ችግር እንፈታለን ብዬ አስባለሁ።

አሁን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲህ ለአገር የሚሆኑና አስፈላጊ ምርቶች እንደሚመረቱ መታየቱ መነሳሳት ይፈጥራል ብለው ያምናሉ?
አዎን! ይህ ለወጡት ብቻ ሳይሆን በጊቢው እየተማሩ ላሉትም ትልቅ ተስፋ ነው። ምክንያቱም ዩኒቨርሲቲው የሆነ ነገር ከሠራ፣ ዩኒቨርሲቲው የእነርሱም አካል ነውና ነው። አሁንም ስለወጡ እንጂ [በቬንትሌተር ሥራው] እነሱን [ተማሪዎችንም] ማሳተፍ እንችል ነበር። እናም እንዳልኩት ለእነርሱ ለወደፊትም ተስፋ ነው የሚሆነው። ዩኒቨርስቲ ደኅና ነገር ሠርቶ፣ አገር ከጠቀመ፣ ለነገ ተመራቂዎች እንዲሁም ለተቀመረቁትና ሥራ ላይ ላሉትም፣ ጥሩ የማስተዋወቅ ሥራና የአቅም ግንባታ ይሆናል።
በፊት የነበሩና አሁን ያሉ እድሎችን አነጻጽረን ማየት ከቻልን፣ ምን አዲስ ነገር አለ?

አሁን እንደሚታወቅ ተማሪዎቸ ጊቢ ውስጥ የሉም። የእኛም በዛ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። አሁን ትምህርቶችን በኦንላይን ለመስጠት እየሞከርን ነው። ይህም በተለይ ኹለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ነው። ይህ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ አልተለመደም። ይህ ልምድ በዚህ ከቀጠለ የመማር ማስተማር ሂደቱን ቀላል ያደርገዋል።
ከዛ ውጪ ብዙ ቴክኖሎጂዎች እየወጡ ነው፣ በዚህ የመማር ማስተማር ሂደት ደጋፊ የሚሆኑ። ስለዚህ ወደፊት የትምህርት አሰጣጥ ሂሰቱን ለማሻሻል ይረዳ ይሆናል።
ይህ አሁን ያነሱት ነጥብ ላይ፣ የትምህርት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ መደገፉ ጥሩ ሆኖ የትምህርት ጥራት ጉዳይንስ አሳሳቢ አያደርገውም?

አንድ ነገር ሲሠራ ጥሩም መጥፎም ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል። ይህን ማጤና ያስፈልጋል። አሁን ካለው ችግር አንጻር ግን ያለን አማራጭ ይህ ነው። በኋላ ላይ አመጣጡን አይቶ የትኛው ጥሩ ጎን አለው፣ የትኛው፣ መጥፎ ጎን አለው የሚለውን ማጥናት ይቻላል። አሁን ያለው አማራጭ ግን ይህ ብቻ ስለሆነ ይህንን ነው የምንጠቀመው።

በዩኒቨርሲቲ እንደ ጥናትና ምርምር ማእከል የፈጠራና የምርምር ሥራዎች በሞዴል ይቀርባሉ። ዩኒቨርስቲ ወደ ምርት የሚገባበት አጋጣሚ ወይም መንገድ የለም?
አሁን እኛ መሥረት የምንችለው የተወሰነ ለማሳያ በሚሆን መጠን ነው። ያንን ካመረትንና በትክክል ሥራ ላይ መዋሉን ካረጋገጥን፣ ለሚመለከተው አካል እናስተላልፋለን። ይህም ጤና ሚኒስቴር ሊሆን ይችላል ወይም ሳይንስና ቴክኖሊጂ ሚኒስቴር ይሆናል። እናም ለእነርሱ ሰጥተን እነርሱ የሚመረትበትን አግባብ የሚፈልጉ ይሆናል። ዩኒቨርስቲ እዛ ድረስ ነው መሄድ የሚችለው።

ዩኒቨርሲቲ መሥራት የሚችላቸው ሥራዎች አሉ። ይህም ማስተማር፣ ምርምርና የፈጠራ ሥራ ነው። ዩኒቨርስቲ ወደ ምርት መግባት አይችልም። ስለዚህ እኛም ማድረግ የምንችለው ለምርቶቹን ማሳያ አምርተን፣ መሥራቱን አረጋግጠን ያንን ማቅረብ ነው። እንዳልኩት የሚመለከተውን አካል አነጋግረን የሚመረትበትን አግባብ መፈለግ አለብን።

በአጠቃላይ ግን ይህ ወረርሽኝ ብዙ እድልም ይዞ መጥቷል፣ ችግር ብቻ አይደለም። ይህ ለብዙ ሰዎችን ለሥራ አነሳስቷል።ስለዞህ ሁሉም አካል ተባብሮ ያንን ማስቀጠል አለበት። ይም ከተቻለ አገር የሚጠቅም ሥራ መሥራት ይቻላል።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here