ዋፋ ማርኬቲንግ እና ፕሮሞሽን ውስጥ ብልሹ አሠራሮች እንዳሉ ተጠቆመ

0
371

በዋልታ እና ፋና የቴሊቪዥን ጣቢያዎች በጋራ እና በአንድ ሰው ሽርክና የተቋቋመው ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ውስጥ ብልሹ አሠራሮች መኖራቸውን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደተናገሩት፣ በድርጅቱ ውስጥ ሕግን ያልተከተሉ ግዢዎች፣ የአሰራር ሂደትን ያልተከተሉ የውጭ አገራት ጉዞዎች እንዲሁም የውጭ ጉዞዎች ሲደረጉ ጉዞ ከሚደረግበት ዓላማ ጋር ተያያዥነት የሌላቸው እና ድርጅቱ የማያውቃቸው ግለሰቦች የውጭ አገራት ጉዞዎችን እንደሚያደርጉ፣ ከአሠራር ውጪ ሆኑ የውጭ አገር የሕክምና አገልግሎቶች ተከናውነዋል።

በድርጅቱ ውስጥ ተከሰቱ ከተባሉት እና ከአሠራር ውጪ ተደረጉ የተባሉት አንደኛው በቀን 01/07/2012 በተጻፈ ደብዳቤ የዋፋ ሥራ አስኪያጅ ፋንታየ ጌታነህ 284 ሺሕ ብር ከድርጅቱ በመበደር ወደ አገር ውስጥ ለሚያስገቡት እና በራሳቸው ሥም ለገዟቸው ቴሌቪዥኖች ቀረጥ ከፍለው ማውጫ እንዳደረጉ ተጠቁሟል። ምንጮች ጨምረው እንደገለጹት፣ በድርጅቱ የአሠራር ደንብ መሠረት አንድ ሠራተኛ መበደር የሚችለው በጣም ትልቁ እርከን የኹለት ወር ደሞዝ እንደሆነ እና በሥራ አስኪያጇ የተጠየቀው ገንዘብም ከሕጋዊነቱ የራቀ እንደሆነ ተያይዞ ተጠቅሷል።

ይህን በሚመለከት ዋና ሥራ አስኪያጇ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ምላሽ፣ የተባለው ነገር ሐሰት እንደሆነና መበደርም ቢያስፈልግ ካላቸው የባለቤትነት ድርሻ በመነሳት መበደር እንደሚችሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በድርጅቱ የአስተዳደር ኃላፊ በሆኑት እና ኃይሌ ትኩዕ በተባሉ ግለሰብ ስምንት ጥቅል እቃዎች ግዢ እንዲፈጸምባቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ለዋና ሥራ አስኪያጅ በመጋቢት 2/2012 ደብዳቤ ጽፈው ጥያቄ ያቀርባሉ። በዋና ሥራ አስኪያጅ በኩልም ግዢው እንዲካሄድ ፈቃድ የተሰጠበት ቢሆንም፣ እቃዎቹ በድብቅ ገብተው መጋዘን እንዲከማቹ እንደተደረጉ እና የግዢው ሂደት ግን አሁንም የዋጋ መጠይቅ ተይዞ እየተካሄደ እንደሆነ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የቀረበውን ክስ በተመለከተ ፋንታየ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ምላሽ፣ የተነሳው መሠረተ ቢስ ክስ እና ከግል ቂም የመነጨ ነው ሲሉ ተናግረዋል። በተለያዩ ጊዜያት ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎች በአካል እና በጽሑፍ እንደሚደርሷቸውም ጨምረው ገልጸዋል። አዲስ ማለዳ በአካል መታዘብ እንደቻለችው ዛቻ ያዘለ ባለ ኹለት ገጽ ጽሑፍ በሥራ አስኪያጇ ቢሮ ማየት ተችሏል።

በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ዱባይ ባቀኑበት ወቅት (የካቲት 2012) የባህል ቡድኑን ይዘው እንዲሄዱ ለዋፋ ጥያቄ በቀረበበት ወቅት፣ ከብሔራዊ ቴያትር ሠራተኞች ይዘው መሄዳቸው ተጠቅሶ፤ በባህል ቡድኑ እያንዳንዱ አባል በነፍስ ወከፍ 30 ኪሎ ግራም ቂቤ ወደ ዱባይ እንዲያጓጉዙ በማድረግ እና ዱባይ ላለ ተቀባይ መድረሳቸውን ጥቆማዎች አመላክተዋል።

ፋንታየ ለዚህም ምላሽ ሲሰጡ የተባለው ነገር ክብረ ነክ ጉዳይ እንደሆነና የተደረገውም ዱባይ የሚገኘው አል ሐበሻ ምግብ ቤት ከባህል ቡድኑ ኹለት ሰዎች ኹለት ወይም ሦስት ኪሎ ቂቤ እንዲያመጡላቸው በጠየቁት መሰረት እንደተወሰደላቸው ነው። እናም ይህ ዓይነት የሐሰት ውንጀላ የመጣው የባህል ቡድኑ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት አስበው ስለተከለከሉ ያቀረቡት ውንጀላ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በጥር 2012 ኹለት የአውሮፓ ከተሞች ጣሊያን እና ፈረንሳይ በተደረጉ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ፎረሞች ለአስጎብኚ፣ ለሆቴል ማስያዝ እና ለትራንስፖርት በሚል ሰበብ 12 ሺሕ ዩሮ ‹‹ጊዮን ኢንተርናሽናል ኤኬ›› ለተባለ ድርጅት እንዲተላለፍ መደረጉን ተገልጿል። ምንጮች ጨምረው እንደገለጹት፣ እንደ አገልግሎት የተጠቀሱት ነገሮች ጭራሽ ያልተከናወኑ እና ምንም ባልተሠራበት እንዲከፈለው እንደተደረገ ጠቁመዋል።

በዚህም ፋንታየ ምላሽ ሲሰጡ ድርጅቶችን የሚመረጡት በዋፋ ሳይሆን ዝግጅቱ በሚካሄድበት አገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እንደሆነና ተላለፈ የተባለው ገንዘብም እንዲያውም ትንሽ እንደሆነ፣ እስከ 30 ሺሕ ዮሮ ድረስ ተከፍሎት እንደሚያውቅ እና ለዚህም ደግሞ ዝግጅቱን ሙሉ በሙሉ ያዘጋጀውና ሆቴል እና ከአገር ወደ አገር ሲጓጓዝ የተካሄደውን ሙሉ ትራንስፖርት ያቀረበው ይኸው ድርጅት እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ዋልታ በ50 በመቶ ድርሻ ፣ ፋና በ49 በመቶ ድርሻ እንዲሁም በሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት ፋንታየ ጌታነህ ደግሞ ቀሪውን አንድ በመቶ ድርሻ በመያዝ የተመሠረተው ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን፣ ከ2001 ጀምሮ ወደ ሥራ የገባ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ትላልቅ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት ግንባር ቀደም መሆኑ የሚታወቅ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here