“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
ታክሲ ጥበቃ ረጅም ሰዓት ካቆየን በኋላ፤ አንዲት እናት በመኪናቸው ሊሸኙን ፈቃደኛ ሆኑ። በባዶ ያልፉን የነበሩ የቤት መኪናዎችን በየልባችን ሳንራገም አልቀረንም፤ እርሳቸው ፈቅደው ሲያሳፍሩን «አንዳንዴ መቼም ጥሩ ሰው ያጋጥማል! እግዚአብሔር ይስጥልን» ብለን መረቅናቸው፤ ለመመረቅ እርጅና ይጠየቃል እንዴ?! ጥቂት እንደሔድን፤ እኚሁ ሴት ጋቢና አብራቸው ከቆየች ሴት ጋር በሠፈራቸው ስለደረሰ አደጋ ያወጉ ቀጠሉ። ወጋቸውን ከጀመሩት እንደቆዩ ያስታውቃል። «ለራሷ በረሮ ትንሽዬ ናት፤ ምን አገኝባት ብሎ ነው? እንደው ከሆነስ እዛ ገላቸውን የሚሸጡ ምስኪኖች ጋር መሔድ ሲችል ምንም የማታውቅ ትንሽ ልጅን እንዲህ ማድረግ…አሳዛኝ ጊዜ ላይ ደረስን!» አሉ። አብራቸው የተቀመጠች ወጣት ሴትም ቀበል አድርጋ ተናገረች፤ ከኋላ እኛም አዳማጭ ሆነን ቆየን። በመካከል ከተሳፈርነው ውስጥ አንዷ በጨዋታቸው ጣልቃ ገባች። «ጊዜውማ ክፉ ነው! ብጠቅመው ብዬ፤ ለሴቷ ልጄም ታላቅ ወንድም ይሆናታል ብዬ የዘመድ ልጅ ከክፍለ ሀገር አምጥቼ ነበር። ስንለማመድ ልጄን እየተውኩለት ሥራ እወጣለሁ፤ ባለቤቴም የከባድ መኪና አሽከርካሪ ስለሆነ እምብዛም ቤት አይኖርም» ንግግሯን ቀጠለች። መኪናው ውስጥ የተሳፈርነው ሁላችንም በጥሞና ሴቲቱን እያዳመጥናት ነው። ‹‹መች አውቄ? ለካ እኔ አምኜ ስወጣ ልጄን ይነካካት ነበር›› . . . ብቻ አመመኝ ማለት ስታበዛ ጤና ጣቢያ ወሰድኳት። ከዛ ነው የሆነው ሁሉ የገባኝ። ቢቸግረኝ ለራሱ ቤት ተከራይቼለት በየወሩ የቤት ኪራይ እየከፈልኩና ቀለብ እየሰፈርኩለት እንዲኖር ነግሬው ከቤቴ አስወጣሁት። አይ! ተዉኝ እስቲ!» ለአፍታ በመኪናው ዝምታ ሆነ። «እና ለባለቤትሽ ወይም ለፖሊስ አልተናገርሽም? ልጅሽ’ኮ አካሏ ብቻ ተጎድቶ አይቀርም። ስሜቷም ይጎዳል» አለች፤ ጋቢና የተቀመጠችው ወጣት። «ሆሆይ! ይሄ ምን ተብሎ ይነገራል? …ይቅርታ! ካላስቸገርኩ እዚህች ጋር አውርዱኝ። . . . አመሰግናለሁ» ብላ ወረደች። እሷ ብትወርድም ሐሳቡ ግን ከሁላችንም ጋር ቀርቷል። መኪናው ውስጥ የቀረነውም ከዛ በኋላ «እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ?» ዓይነት ሐሳብ ስንቀባበል ነበር። በዚህ ዓይነት ግን በየቤቱ፣ በየሴቱ ልብና ሐሳብ ስንት ነገር ይኖር ይሆን? ለምን አልተነገረም ሲባል፤ መልሱ « ይሄ ምን ተብሎ ይነገራል?» ይሆናል። ‹‹ምን ተብሎ ይነገራል?›› ከተባለ የበደለ እንዲያፍር፣ ተበዳይ ቀና እንዲል ሲባል ይነገራል! ያጠፋ ሰው ቅጣቱን እንዲያገኝ ይነገራል! ‹‹አዎን ይነገራል!›› አንዱ ከሌላው እንዲማር ሲባል ይነገራል! ‹‹እኔንም ስሙኝ›› ስንል ዝም ብለን አይደለም። . . . አሳዘኙን የልጇን ታሪክ ያጋራችን እናት ይህን መልዕክት ቢደርሳት ምንኛ በወደድኩ!
መቅደስ /ቹቹ/
liduabe21@gmail.com
ቅጽ 1 ቁጥር 5 ታኅሣሥ 6 ቀን 2011