በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን በመስቃንና ማረቆ መካከል በተፈጠረ ግጭት የሦስት ሰዎች ሕይወት አለፈ

0
259

በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን በሚገኙት የመስቃንና ማረቆ ወረዳዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል።
በዞኑ በሚገኙ ኹለቱ ወረዳዎች በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱት ግጭቶች ለሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት መሆናቸው እንደቀጠለ መሆኑ ታውቋል።
ከሰሞኑን በዞኑ ኹለት ወረዳዎች መካከል በተነሳ የግለሰቦች ፀብ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ መመመድ ጀማል አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው ያለው የፀጥታ ኃይል ግጭቱን በጊዜ ማስቆም መቻሉንና በአሁኑ ሰዓትም ዞኑ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ጨምረው ገልጸዋል።
የስርቆትና የእርስ በእርስ ትንኮሳዎች እንዲሁም የተለያዩ ምክንያቶች ለማረቆና መስቃን ወረዳዎች የግጭት መነሻ መሆናቸውን የተናገሩት መሐመድ፣ በወረዳዎቹ መካከል በተደጋጋሚ የሚፈጠረውን ግጭት ለማስቆም ጥረቶች ቢደረጉም ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ያለመቻሉንም አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም በወረዳዎቹ መካከል ሰላምን ለመፍጠር ተደጋጋሚ ወይይቶች ተደርገዋል። ለችግሩም ተጠያቂ ናቸው የተባሉ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ ተደርጓል ያሉት መሐመድ፣ ችግሩን የሚፈጥሩ ግለሰቦች የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ በሆደ ሰፊነት ለማለፍ አለመቻላቸው ግጭቱ ዛሬም ድረስ እንዲቀጥል አድርጎታል ሲሉ ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓትም በአካባቢው የሚገኘው የፀጥታ ኃይል ሁኔታውን በመቆጣጠር ሰላምን የማስቀጠል ግዴታውን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ መሐመድ መናገራቸውን ኢትዮ ኤፍ ኤም ዘግቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 80 ግንቦት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here