ኦነግ ዋነኛው ውጊያ ያለው ምዕራብ ወለጋ ነው አለ

0
526

በኦሮሚያ ክልል በተለይም ምዕራብ ወለጋ ዞን ግጭቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን ተከትሎ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የለየለት ውጥረት ውስጥ ገብተዋል።
ታኅሣሥ 11 በሠላም እና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገው የኦዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሠላማዊ መንገድ ትልግ ለማድረግ የተገባው ቃል እየፈረሰ መሆኑን አሳውቋል።
ኦዴፓ ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት እያሳየ ያለውን ትዕግስት እንደ ፍራቻ በመመልከት ሲዘርፉና ሲያሰቃዩ የነበሩ እንዲሁም ከሥልጣን የተባረሩ ወገኖች ‹‹ተላላኪዎችን በመግዛት ኦሮሚያን እና ኦሮሞን የጦርነት አውድማ ለማድረግ እየሠሩ መሆኑን›› ገልጿል።
ሕዝቡ በሠላም ወጥቶ እንዳይገባና ሥጋት እንዲሰማው፣ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ ገበያም እንዲቆም መደረጉንም ጠቅሷል።
በደቦ ፍርድ በሠላማዊ ሕዝብ ላይ ጭካኔ በተሞላበት ‹‹የሽብር ጥቃት በፈንጂ ሕይወታቸው እያለፈ፣ ሴቶች እየተደፈሩ፣ ንብረት እየወደመ እንዲሁም የሕዝቡ የመንቀሳቀስ መብት እየተገደበ ነው›› ያለው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የኦዴፓ አመራሮችና የኦሮሚያ ፖሊስ አባላትም በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው እያለፈ እንደሆነ አስታውቋል።
ጥፋቱ ከዚህ በላይ ከቀጠለ የሕዝብ እልቂትና የአገር መበተንን እንደሚያስከትል አፅንዖት የሰጠው ኦዴፓ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጡ የመንግሥት ግዴታ መሆኑን ጠቅሷል። በመሆኑም ወንጀል የሚፈፅሙና እንዲፈፀም የሚያመቻቹትን በማደን ለሕግ የማቅረቡ ሥራ በአስቸኳይ እንዲፈፀም አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልጿል። ጥፋተኞችን ለሕግ በማቅረብ ሒደትም የሕዝቡን ትብብር ጠይቋል።
የኦነግ ሊቀ መንበር ዳውድ ኢብሳ ትናንት አመሻሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኦነግ ላይ በኦዴፓ በኩል ጫና እየደረሰ ስለመሆኑ አንስተዋል። በኦዴፓ የወጣው መግለጫም ‹‹የውጊያ አዋጅ ይመስላል›› ብለዋል። ባለፉት ሁለት ቀናት በሰላሌ፣ ባሌ፣ ጉጂና ምሥራቅ ወለጋ ግጭቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል። ይሁንና ‹‹ዋነኛው ውጊያ ግን በሥፋት ያለው ምዕራብ ወለጋ ነው›› ያሉት ዳውድ ይህ የተከሰተውም መንግሥት በጣም ቸኩሎ በወሰዳቸው እርምጃዎች እንደሆነ ለመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።
‹‹ኦነግ ተኩስ አቁም ካወጀበት ቀን ጀምሮ የኦነግ ሠራዊት አንድም ቀን በራሱ ተነሳሽነት ተኩስ ከፍቶ እንደማያውቅ›› የገለጹት ዳውድ ሌሎች ተኩስ ሲከፍቱበት ግን ራሱን እየተከላከለ ስለመሆኑ ነው ያነሱት።
የመከላከያ ሠራዊት የኦነግ ታጣቂዎች ባሉበት አካባቢ በተለይም በምዕራብ ወለጋ መስፈሩ ግጭት እንዲከሰት ምክንያት እንደሆነም ዳውድ በመግለጫቸው አንስተዋል።
የሠላም ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ በመጥቀስ ኦነግ መንግሥት ዝግጁ ከሆነ ለመወያየት እንደሚፈልግም ሊቀ መንበሩ ተናግረዋል። ኅዳር 28/2011 ዐሥራ አራት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ተመካክረው ለክልሉ ሕዝብ የጋራ ሠላም ሲሉ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸው ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here