በሜቴክ ይገነባ የነበረውና በ2010 ውሉ በመቋረጡ ግንባታው የቆመውን የመልካ ሰዲ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ግንባታን ለማስጀመር ፕሮጀክቱ የደረሰበትን ደረጃ እያጠና እንደሆነ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የመልካ ሰዲ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአራት ነጥብ 16 ቢሊየን ብር ወጪ የእንፋሎት ኃይልን በመጠቀም 137 ነጥብ አምስት ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ ታቅዶ የተጀመረ ነው። የኃይል ማመንጫ ግንባታውንም የብረታብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሊሰራ ውል ገብቶ ነበር። ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቱን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ሊያስረክብ ውል ፈርሞ ሰኔ 9/2006 ሥራውን ቢጀመርም ፕሮጀክቱ በታቀደለት የጊዜ ገደብ ውስጥ መጠናቀቅ እንዳልቻለ የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ ሞገስ መኮንን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በአንጻሩ ኮርፖሬሽኑ የግንባታውን ወጪ አንድ አራተኛ ወይም 25 በመቶ አካባቢ ክፍያ ወስዷል ተብሏል።
ኮርፖሬሽኑ ግንባታውን በተባለው ጊዜ ባለማጠናቀቁ ተጨማሪ ሰባት ወራት ቢሰጠውም ፕሮጀክቱን ከተረከበበት ሰኔ 2006 ጀምሮ ውሉ እስከተቋረጠበት 2010 የሠራው 27 ነጥብ አምስት በመቶ ብቻ መሆኑ ታውቋል። በዚህም የኃይል ማመንጫው ባለቤት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ከሜቴክ ጋር የገባውን ውል ለማቋረጥ መገደዱን አሳውቋል።
ሜቴክ ከአማካሪው መኃንዲስ የሚሰጡትን አስተያየቶች አለመቀበልን ጨምሮ ከአማካሪ መኃንዲሱ እና ከንዑስ ሥራ ተቋራጮቹ የሚወጡ የተጨማሪና የሥራ ለውጥ ትእዛዞችን ለፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ እንዲያቀርብና ዝርዝር ዲዛይኖችን ሳያቀርብ ሥራዎችን እንዳያከናውን በተደጋጋሚ ቢነገረውም ምላሽ ሳይሰጥ ሥራውን ያከናውን እንደነበር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገልጿል።
ተቋራጩ ጋር ከነበሩ ችግሮች በተጨማሪ በዲዛይኑ መሠረት የስቲም ተርባይን ጀነሬትሩን ለመትከል በ20 ሜትር ጥልቀት ላይ መገኘት የነበረበት አለት እስከ 28 ሜትር ድረስ ባለመገኘቱ ግንባታው ለአንድ ዓመት ያህል ተቋርጦ ነበር ተብሏል።
የመልካ ሰዲ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ በአፋር ክልል የእርሻና የግጦሽ መሬትን በስፋት በመውረር ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ያለውን፣ ‹‹ፕሮስፒስ ደሊን ፕሎራ›› የሚሰኝ መጤ አረም መንጥሮ በማቃጠል ወደ እንፋሎት ኃይል በመለወጥ አገሪቷ ከሚኖሯት ታዳሽ ኃይል ማመንጫዎች መካከል አንዱ ይሆናል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር።
ሜቴክ ከዚህም ውጪ ከኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተገናኘ የኤሌክትሮ መካኒካልና የኃይድሮሊክ ሥራዎችን ለመሥራት ውል መግባቱ ይታወሳል። ይሁንና በሥራው ከፍተኛ መጓተትና የጥራት ጉድለት አሳይቷል በሚል መነጠቁ አይዘነጋም።
በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ አገራዊ የሆኑ እንደ ስኳር ፋብሪካና የማዳበርያ ማምረቻ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ጋር ውል ቢገባም በውሉ ላይ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ሥራዎችን ማከናወን ባለመቻሉ ሲወቀስና ፕሮጀክቶቹ ሲቀማ እንደነበርም ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ከመልካ ሰዲ ውጪ ሁለት መቶ 54 ሜጋ ዋት ያመነጫል የተባለውን የገናሌ ዳዋ ሦስት የውኃ ኃይል ማመጫ እና ሁለት ሺህ 160 ሜጋ ዋት እንደሚያመኘጭ የሚጠበቀው የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች በታቀደላቸው የግንባታ ጊዜ እየተከናወኑ ስለመሆናቸው አሳውቋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011