የሕገ መንግሥታዊነት ጅማሮ ማሳያ. . .!?

0
499

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣን በአምስት ዓመት የሚገድብ በመሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው ሥራ አስፈጻሚም ሆነ ሕግ ተርጓሚው አብሮ ሥልጣናቸው ያበቃል። ሆኖም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለማቀፋዊ እና አገራዊ እውነታን ምክንያት ታክኮ የአስቸኳይ አዋጅ በመታወጁ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫ ማካሔድ እንደማይችል ለተወካዮች ምክር ቤት ማስታወቁ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ሊከሰት የሚችለውን ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ/ክፍተት የሚያስቀር በሕግ እና የሕገ መንግሥት ባለሙያዎች አስጠንቻቸዋለሁ ያለውን አራት አማራጭ ምክረ ሐሳቦችን በማቅረብ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት በማካሔድ የሚያስኬደው አማራጭ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ነው ሲል አስታውቋል።

አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወዲያውኑ የመንግሥትን ምክረ ሐሳብ መቀበላቸውን አስታውቀዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ መንግሥት ራሱን እንደብቸኛ አማራጭ አቅራቢ በመቁረጥ ሌላ አማራጭ ለመስማት ‘‘ጆሮ የለኝም፤ ሕገ መንግሥታዊም አይሆንም’’ ሲል አጣጥሎብናል ሲሉ ይከሳሉ። በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሽግግር መንግሥት የሚለውን አማራጭ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ እና አገሪቱንም ጭልጥ ወዳለ ስርዓት አልበኝነት የሚከት ነው ሲሉ እንደማይፈቅዱ አስረግጠው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የትግራይ ክልልን ከምታስተዳድረው ሕወሓት ደግሞ የፌደራል መንግሥቱ ያቀረባቸው አማራጮች ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን የብልጽግና ፓርቲ ብልጣብልጥ የሥልጣን ማራዘሚያ መንገድ ነው በማለት በትግራይ ክልል ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ይካሔዳል በማለት ጠንካራ የመልስ ምት ሰጥታለች።

እነዚህ እሰጣ ገባ በቀጠሉበት ሁኔታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግሥት ካቀረባቸው አማራጮች ውስጥ ምርጫው እስከሚካሔድ ድረስ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ‘ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ’ መስጠት ያስፈልጋል የሚለውን በመደገፍ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ እንዲመራ በማድረግ ጉባኤው ያሉት የውሳኔ ሐሳብ ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲያቀርብ አዝዟል።

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤም ኀላፊነቱን ለመወጣት ባለፈው ቅዳሜ፣ ሰኞ እና ሐሙስ ሦስት በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት የተላለፉ መድረኮችን በማዘጋጀት ይመለከታቸዋል ካላቸው የሕግ እና የሕገ መንግሥት ምሁራን፣ የኢትዮጵያ ጠበቃዎች ማኅበር፣ ሕገ መንግሥቱን በማርቀቅ ሒደት ሙያዊ እገዛ ያደረጉ ግለሰቦችን እንዲሁም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ከጤና ሚኒስትር አስተያየቶችን ሲሰማ ሰንብቷል።

ሰሞነኛ ትልቅ መነጋገሪያ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ጎልቶ የወጣው እነኚህ መድረኮች ነበሩ፤ ናቸውም። አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን ተዓማኒነት እንዲኖረውና የሥልጣን ቅብብሎሹ መልክ ባለው መንገድ በተገደበ ጊዜ በሚደረግ ምርጫ እንዲኖር የታሰበበት እንደሆነ፣ አሁን ባለው ሁኔታ የሥልጣን ክፍተት ይኖራል ብለው አስበው እንደማያውቁ የተናገሩ ሲሆን ሕገ መንግሥቱ የታለመለትን ግብ እንዲመታ መንፈሱን መረዳት ቀዳሚው ጉዳይ መሆኑን አለበት ሲሉ በአመክንዮ አስረድተዋል።

የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ያዘጋጀውን አስተያየቶችን የመስማት መድረኮችን በተመለከተ በርካቶች ሐሳባቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገፆችም ሆነ በመደበኛ መገናኛ ብዙኀን አውታሮች ያጋሩ ሲሆን ሒደቱ ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን በመግለጽ፣ አሳታፊና ለሕዝብ ግልጽ በሆነ አግባብ መታየቱን አድንቀዋል። በኢትዮጵያ ለዴሞክራሲያዊ ውይይቶች፣ ክርክሮችና ድርድሮች መሠረት ለመጣል እንደ መልካም ጅምር መወሰድ አለበት ሲሉም መድረኮቹን አሞካሽተዋቸዋል። በተጨማሪም ከፍተኛ የንቃተ ሕገ መንግሥት ሥራም ተሰርቷል በማለትም አድንቀዋል።

በሌላ በኩል ግን ለየት ያሉና በተቃራኒው የቆሙ ድምፆች አለመሰማታቸው ቅር እንደሚያሰኝና ሒደቱንም ጎደሎ እንደሚያደርገው አበክረው ድምፃቸውንም ያሰሙ ነበሩ።

የሆነው ሆኖ ችግሮችን ሕግን ብቻ መሰረት ባደረገ መልኩ ለመፍታት መታሰቡ ብሎም መሞከሩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሒደት ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ጅማሮ ማሳያ ተደርጎ በብዙዎች ተቆጥሯል።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here