በኢትዮጵያ በሚነሱ ግጭቶች ዋጋ የሚከፍሉት ቤተ እምነቶች ናቸው

0
1130

ጅማ በ1999 ሃይማኖትን ሽፋን ባደረገ ግጭት ብዙ ዋጋ ተከፍሎባታል። ለበርካታ ዘመናት በፍቅር በኖረው ማኅበረሰብ ውስጥ በተነሳ በዚህ ግጭት ሳቢያ ቤተ እምነቶች ተቃጥለዋል፣ ምዕመናን ተገድለዋል። በዚህ ጊዜ ግጭቱ መነሻና አጀንዳው ሌላ፣ ሃይማኖትን ግን ሽፋንና መጠቀሚያ እንዳደረገ ለማኅበረሰቡ በማስረዳት ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ሰላምን መመለስ ከቻሉ ሰዎች መካከል ይገኛሉ፤ ሊቀ ትጉሃን ቄስ ታጋይ ታደለ።

በዚህም ተግባራቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን «የሰላም አምባሳደር» ብሎ ያመሰገናቸው ቀሲስ ታጋይ፣ ይህንን ተከትሎ ነው በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሃይማኖት ተቋማት በጋራ ጉዳዮች ላይ የሚመክሩበትና አንድ ላይ የሚሠሩበት ተቋም በጅማ ከተማ የተመሠረተው። ከአራት ዓመት በኋላ፣ በ2003 ደግሞ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ተቋቋመ። ቀሲስ ታጋይ በዚህ ጉባኤ በሊቀመንበርነት የተሠየሙት ታድያ ባለፈው ዓመት 2011 ላይ ነው።

ጉባኤው ካለፈው ዓመት በኋላም ድምጾችን አጉልቶ በማሰማት ከፍ ያለ እውቅናን እያገኘ ያለ ሲሆን፣ አሁንም ከወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የዘለቀውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል በሚደረግ ጥረት ውስጥ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል። ከመጋቢት 28/2012 ጀምሮም እስከ ሚያዝያ 27 የዘለቀ አገራዊ ጸሎትና ምህላ በማወጅ በጋራ ጸሎት መርሃ ግብር ያካሄደ ሲሆን፣ ይህም ቤተ እምነቶች በተዘጉበት ጊዜ ሰዎች በየቤታቸው ሆነው ከጸሎት እንዳይቆጠቡ ለማድረግ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ የጉባኤውን ሥራና ኃላፊነት፣ በአባላት እምነት ተቋማቱ መካከል ስላለው ግንኙነት እንዲሁም ወቅታዊ ጉዳዮችን ለቀሲስ ታጋይ ታደለ በማንሳት ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

በኢትዮጵያ ለአንድ ወር የታወጀው ጸሎትና ምህላ መርሃ ግብር በተለያዩ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ሲተላለፍ ነበር፣ ምን ዓይነት ግብረ መልስ አገኛችሁ?
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በማስመልከት የእምነት ተቋማት በራሳችን አስተምህሮና ስርዓት፣ በጋራ በመነጋገር ከመጋቢት 27/2012 እሁድ ቀን፣ ለሁሉም ቤተ እምነቶች የጸሎት መርሃ ግብር ጥሪ አባቶች በጋራ አቅርበዋል። በተፈጠረው መግባባት መሠረት ለአንድ ወር (ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዝያ 27) ከምሽቱ 3 እስከ 4 ሰዓት በሁሉም ቤተ እምነቶች የጋራ ጸሎት ተጀመረ።

ከዛም በተናጥል አራት የመንግሥት ሚድያዎችን በመጨመርና፣ ወጣ ገባ ቢልም የግል ሚድያዎች በተሳተፉበት፣ በየሳምንቱ እንከታተላለን። ግምገማ ስናደርግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምዕመናን ተሳታፊ እንደነበር ከሚድያ ግብር ኃይሎች የምናገኘው አስተያየት ይጠቁማል። ሕዝቡ ከለቅሶና እንባ ጋር ጸሎቱን ሲያከናውን ከርሟል። በዛም ምክንያት ለአንድ ወር ያህል ጥሩ መልስ አግኝተናል።

ለምሳሌ በአንድ ወር ቆይታችን ውሰጥ ምንም ዓይነት ከኮቪድ ጋር በተያያዘ የሞተብን ሰው አልነበረም፣ መጨረሻ የማጠቃለያ ቀን ከወጣው መረጃ በቀር። የተያዙ ሰዎችም ቁጥርም በቀን ከፍተኛው ሦስት ነበር፣ አንድ ወሩ እንደዛ ነው ያለፈው። ጽኑ ሕሙማን ክፍል አንድም ሰው አልነበረም። የነበሩትም በከፍተኛ ቁጥር አገግመው ወጥተው ነበር። ይህ ከፈጣሪ ወደ እርሱ ስለተመለስን ለኢትዮጵያውን ምህረት ያደረገበት፣ አሳልፎ ያልሰጠበት ነው ብለን አይተናል።

ከዛ ግን ከጸሎት የመራቅና የመዘናጋት ሁኔታ ይስተዋላል። በዛም ምክንያት ደግሞ በነጋታው ጀምሮ በቫይረሱ የሚያዝ ሰው ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አይተናል፣ እስከ 35 ከፍተኛ ቁጥር ተመዝግቧል።

ከዚህ አኳያ በአንድ ወሩ ሁሉም ኅብረተሰብ ከብሔርተኝነት፣ ከመከፋፈል፣ ከጫጫታ ከመለያየት ወጥቶ አንድ ሆኖ ያሳለፈበት፣ ምንም ሥጋዊና ምድራዊ ነገርን ትቶ ወደ ፈጣሪ ያንጋጠጠበት፣ የለመነበት፣ የጮኸበት ወር ነበር ነው። በተለይ አንድ ወር ካጠናቀቅን በኋላና መጨረሻ አካባቢ፣ ከምርጫና የተለያየ ጥያቄ ጋር ተያይዞ ወረርሽኙ ተረስቶና ፈጣሪ ወደ ጎን ተደርጎ፣ ወደ ሌላ ጭቅጭቅ የገባንበት፣ ከዛም ጋር ተያይዞ ሰው እንባው ቆሞ ከገበያ ጋር ንትክር፣ ይከፈት አይከፈት፣ ምርጫ ይካሄድ አይካሄድ የሚል ሆነ። ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች አይተናል። ከአንድ ወሩ በኋላ (ባለፉት 15 ቀናት አካባቢ) ጥሩ ያልነበረ ጊዜ አሳልፈናል ብለን እናምናለን።

ብቸኛው ምርጫ ፈጣሪ እንደሆነ የሃይማኖት ተቃማትና የሃይማኖት አባቶች ያምናሉ። እንደምናየው ዓለም ከፈጣሪ እየራቀ፣ በተለይ ድኅረ ዘመናዊነት እየተከተለ ባለበት፣ ሉላዊነት ሁሉም ጋር የሚያደርስ ስለሆነ፣ ወደ ፈጣሪ መቅረብና አማኝ መሆን ቀርቶ፣ ከእግዚአብሔር መንገድ መውጣት እንደ ሥልጡንት፣ እግዚአብሔርን ማምለክና መጥራት ደግሞ እንዳለመሠልጠን የሚታይበት፣ ቤተ እምነቶችን መዝጋትና ወደ ዳንኪራና መዝናኛ መቀየር፣ ከእምነት ወጥቶ ወደ ግብረ ሰዶምናትና ፈጣሪን ወደሚያስቀይመው ሥራ ዓለም የተገባበት መሆኑን ያየንበት ነው።

በዚህም ዓለም በአንድ ጅራፍ ተቀጥቷል። ኢትዮጵያም የአማኝ አገር ብንሆንና ከፍተኛው አማኝ ነው ቢባልም፣ ሙሉ አማኞች እንዳልነበርን ማሳያዎች ነበሩ። በብሔርና በዘር፣ በጎሳ የተከፋፈልንበት፣ በኃጢአት መንገድ የተጓዝንበት ነው። በኹለትና ሦስት ዓመት ስናይ ሰው በማንነት ያፈናቀልንበት፣ በጠራራ ፀሐይ ሰው ቁልቁል የሰቀልንበትና የገደልንበት፣ እናት ልጇን ተመርቆ ዲግሪ ይዞ ይመጣል ስትል አስክሬን የተቀበለችበት የቀበረችበት አገር ሆነናል። ቤተ እምነቶች በድፍረት የተቃጠሉበት፣ አንዱ በአንዱ በሃይማኖት ምክንያት የተነሳበትና ፈጣሪን የተዳፈርንበት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።

ከዚህ አኳያ ይነስም ይብዛም የእጃችንን አግኝተናል። ፈጣሪ አሳልፎ ባይሰጠንም ጅራፉ ሁላችንንም እያገኘን ነው፣ ከዚህ ኢትዮጵያም አላመለጠችም። አሁንም እየጨመረ ነው። ንትርክና መለያት አሁንም አለ። አሁንም ጥንቃቄ የለም። ወደ ፈጣሪ ማንባትና ማልቀሱ መጀመሪያ አንድ ወር በሄድንበት ልክ አይደለም ያለው። ጸሎቱ መቆም የለበትም።

ግን እኛ ለሕዝብ አንድ ወር የሰጠነው ሰው በዚህ እንዲለምድና በየቤቱ እንዲያለቅስ ነው። እንጂ የግድ ጸሎት ሁሌም በቴሌቭዥን አይደለም። ወደየራሳችን አምጥተን እንድናለቅስ ሐሳብ ለሕዝቡ የማቀበል ያህል ነው እኛ የሠራነው
የአንድ ወሩ የጸሎት መርሃ ግብር ከተጠናቀቀ በኋላ አሁንም የመንግሥት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች የጸሎት መርሃ ግብሮችን እያስተላለፉ ይገኛሉ። ትብብሩ በምን መልክ ቀጠለ?
የረመዳን ወር በመሆኑና ቤተእምነቶች ዝግ ስለነበሩ፣ በቴሌቭዥን ጣብያዎች መርሃ ግብሩ እንዲቀጥል፣ ጸሎቱን እናደርጋለን ያሉና መቀጠል የሚፈልጉ ቤተ እምነቶች ደግሞ እያከናወኑ ነው። ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ የሰዓት አለመመጣጠን አለ። እንደ አዋጁ ሰሞን አይደለም። አሁን ሚድያዎች በተመቻቸው ሰዓት ነው እየተደረገ ያለው። በዚህም ከአንድንድ ቤተ እምነቶች ጋር አለመግባባት አለ።

ለምሳሌ ከ3 እስከ 4 ሰዓት በዛው መቀጠል አለበት የሚሉ ቤተ እምነቶች አሉ። ሚዲያዎች ደግሞ ይህ ወሳኝ ሰዓት ነውና፣ ገንዘብ የምናገኝበት ሰዓት ስለሆነ ለኪሳራ መዳረግ የለብንም ይላሉ። ዞሮ ዞሮ ያንን ለማጣጣም በመናበብ እንዲሠሩ ነው ፕሮግራም ያወጣነው። በዚህ ልክ እየሄዱ ነው።

ከዛም አልፎ በጥሩ ሁኔታ እየተጠቀሙ ያሉ አለ፣ ያልሄዱም እንደዛው። እናም እንደ አንድ ወሩ አይደለም። ሰውም በዛው ልክ በጉጉት እየጠበቀ አይደለም። አንዳንድ መጎሻሸሞችም እየታዩ ነበር።

ይህ ከተነሳ፣ እንዲህ መጎሻሸም እንዳይኖር ጉባኤው ክትትል ያደርጋል?
እንደ ጉባኤ ግብረ ኃይል አለ። ደረጃ አውጥተን ሰጥተናል። የትኛውም ቤተ እምነት የራሱን አስተምህሮ ሲያነሳ የሌላውን አስተምህሮ በማይነቅፍበት መንገድ ነው መሆን ያለበት። ምክንያቱም የሁሉም ቤተ እምነት አስተምህሮ የተለያየ ነው። ነገር ግን አንድ አድርጎ ወደዚህ ሚድያ ያመጣን ኮቪድ 19 ነው። የጋራ የሆነ ጠላት መጥቶብናል። በጋራ ካልሆነ ያንን መሻገር አንችልም።

ይህ መቅሰፍት የሚወገደው ‹እናንተ እንዲህ ናችሁ! እናንተ እንዲያ ናችሁ!› በሚል አይደለም። በመፈቃቀድና በመከባበር ላይ የተመሠረተ አገልግሎት ሰጥቶ ሕዝብን የማዳን፣ እንዲጠነቀቅ የማድረግ፣ በጸሎት የመደጋገፍ ሥራ ያስፈልጋል። አንዱ ለአንዱ እንዲጸልይለት፣ ሙስሊም ኅብረተሰብ ከተጎዳ ክርስትያኑ የሚጠቀመው ወይም ክርስትያኑ ከተጎዳ ሙስሊሙ የሚጠቀምበት አንዳች ነገር የለም። ስለዚህ ሁላችን በጋራ መደጋገፍ፣ መረዳዳት ስንችል ነው የምንሻገረው።

ስለዚህ የጋር የሆነው ነገር ላይ የተወሰኑ ነጥቦችን አውጥተን፣ ለሁሉም ቤተ እምነትና ሚድያ ሰጥተናል። ማንም ሰው ያን አይቶ መናገር ይቻላል። ተማምነንበት በዛ ሄደናል። አንዱን ወሩ በጥሩ ሁኔታ ነበር ያሳለፍነው።

ከሚዲያዎች ጋር በተገናኘ እንዲህ ያለ ነገር ሊያጋጥም ይችላል በማለት በፕሮዳክሽን የተቀረጸ ምስል እንዲተላለፍ ነበር አቅጣጫ የሰጠነው። ከዛ ውጪ ግን አንዳንድ ጣቢያዎች ቀጥታ እየገቡ ሲያስተላልፉ ነበር። ከዛ አንጻር መነቃቀፎች እየመጡ ነበር። እኛም ቆም ብለን ማንም የማንንም ቤተ እምነት፣ ሃይማኖት፣ አስተምህሮ መንቀፍ የለበትም፣ ይህ መነቃቀፊያ መድረክ አይደለም የሚል አቋም ይዘናል። ይህን ያደረጉ በይቅርታ እንዲያልፉና ከዚህ በኋላ እንዳይደገም አድርገናል።

ሌላ ምንም ዓይነት መካሻና አማራጭ ስለሌለ ማለት ነው። ይቅርታ ካላደረግንና ይቅረታም ካልተቀበልን፣ ይህን መሻገር ካልቻልን፣ ዞሮ ዘሮ ለዚህ መልስ ለመስጠት የሌላው አእምሮ ይጎዳል። እንዲህ ያሉ [መልስ መሰጣጠት] ነገሮች የሚመጡ ከሆነ ግን ወደ መጎሻሸም ነው የሚገባው። ስለዚህ አንድ ግለሰብ በሠራና አንድ ሰው ባጠፋ ብዙኀኑ ለምን ይቆስላል? ብዙኀኑ መቁሰል የለበትም። ይህን ለማለፍም ብቸኛው አማራጭ በይቅርታ ማለፍ ነው።

አጠቃላይ ግን የረመዳን ወር ሲጠናቀቅ፣ እንደ ጉባኤ ኃላፊነት አንወስድም። ግጭት እንዳይነሳ ለየቤተ እምነት መጠንቀቅ ስላለብን፣ ሚድያዎች በራሳቸው ኃላፊነት ወስደው ካሰራጩ እንጂ እኛ እዚህ ጉዳይ ላይ ማስተባበሩን ለጊዜው ገታ ማድረግ አለብን የሚል አቋም ላይ ደርሰናል።

ከወቅታዊ ሁኔታ ወጣ ስንል፣ ጉባኤው ከፖለቲካ ጫና ምን ያህል ነጻ ነው ማለት እንችላለን?
አንድ እውነት መናገር ያስፈልጋል። ከመንግሥት ጋር ተራርቀሽ አትሠሪም፣ ተቀራርቦ ተረዳድቶ ነው የሚሠራው፣ በትብብር እንሠራለን። እኛ ጥሩ ሐሳብ ላይ፣ በሰላምና ልማት ጉዳይ ላይ ከመንግሥት ጋር በትብብር እንሠራለን ነው። ነገር ግን መንግሥት የሚያመጣቸውን አጀንዳዎች ሁሉ ቤተ እምነቶች ላይ ቢጭን ይቀበላሉ ማለት አይቻልም። የሚቀበል ትከሻ ያለው ካለ እሱ የራሱ ፋንታ ነው። እኔ እንደምማራውና እንደማስተባብረው ተቋም ግን ስመጣም አቋሜን በግልጽ አስቀምጬ ነው።
ከመንግሥት ጥገኝነት ነጻ የሆነ ተቋም እንፈጥራለን። ይህ ማለት ማንኛውም የመንግሥት የፖለቲካ ማስፈጻሚያ እንዳንሆን፣ ገለልተኛ ሆነን፣ ለሕዝባችን፣ ተቸገሩና ለተጎዱ፣ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆን የሚችል ተቋም ለማድረግ ነው እኛ ለሕዝብ ቃል የገባነው።

እኔም አንድ ዓመት ሆኖኛል ኃላፊነት ላይ ከመጣሁ። በተለያዩ ሥራዎቼ ልገመገም እችላለሁ። ስንጀምር ግብረ ሰዶምን በማውገዝ ነው የጀመርነው፣ ይህ የሚደፈር ርዕስ አልነበረም። በድፍረት ቤተ እምነቶች ቃላቸውን አውጥተው እንዲናገሩ ያደረግነው የዛሬ ዓመት አካባቢ [ሰኔ 2011] ነው፣ በዛ ነው የጀመርነው።

በኋላ በተለያየ ቦታ እምነትን ሽፋን ባደረገ ቤተ እምነቶች ሲቃጠሉ፣ ሰዎች ሲገደሉ በግልጽ ነው መንግሥት ወንጀል የሠሩትን በአደባባይ ለፍርድ ሊያቀርብ ይገባል ብለን የሞገትነው። መግለጫ ቀድመን የሰጠነውም እኛ ነን።

ኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም የፖለቲካ ገዳይ ይነሳ፣ ማወራረጃው ቤተ እምነቶች ናቸው። ስለዚህ ፖለቲካ ከቤተ እምነት እጅህን አንሳ ነው ያልነው። ፖለቲከኞች ራሳችሁን ችላችሁ የፖለቲካ መደባደቢያ ቦታ አዘጋጅታችሁ ኳሱን እዛው ሜዳ ላይ ተጫወቱ፣ ወደ እኛ ወደ ቤተ እምነቶች፣ ወደ ሃይማኖቶች ኳሱን አትጠልዙት፣ ይህንን አቋማችንን በተደጋጋሚ ገልጸናል።

ስርዓት ትላንት ነበር፣ ዛሬ ያለው ትላንት የነበረው አይደለም፣ ዛሬ ያለውም ነገ አይኖርም። ሃይማኖትና እምነት ትላንት ነበር፣ ዛሬም አለ፣ ነገም ይኖራል። አማኝ እስካለ ድረስ እምነት ይኖራል። ስለዚህ የሀይማኖትና የፖለቲካ ስርዓት ይለያያሉ። እኛ ምድራዊ ስርዓት አይደለም የምናስቀጥለው፣ ሰማያዊ የእግዚአብሔርን መንግሥት፣ የፈጣሪን መንገድ ነው። የእነርሱ ሥጋዊ መንገድ፣ ሥጋዊ ሥራ ነው። ሥጋዊ አሠራርን ነው የሚከተሉት፣ ዓለማዊ ሥራን ነው የሚሠሩት። የእግዚአብሔርን የፈጣሪን ሥራ ይሠራሉ ብለን አናስብም።

ልዩነታችን ሰማይና ምድር ነው። እናም በጭራሽ ምድራዊ ሐሳብ በመንፈሳዊ ሐሳብ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ እፈተፍታለሁ፣ እወስናለሁ ቢሉ በእርግጠኝነት እኛ እድልም አንሰጥም። በጭራሽ ደግሞ የምንሸከምበት ትከሻም አይኖርም።

ይህን ያነሳሁት ከተሰሚነትን አንጻር ነው። ጉባኤው ገለልተኛ መሆኑን ሕዝብ ምን ያህል ተረድቷል ማለት ይቻላል?
ያው ሕዝብ የሚረዳሽ በሥራ እንጂ በንግግር አይደለም። ሕዝቡ ደስተኛ ላይሆን ይችላል። እንዳልኩት ጸሎት ስናውጅ የታሰሩ ሰዎች ይፈቱ፣ ይቅር እንባባል ብለን ነበር። በተለይ ከፖለቲካ ጋር ተያይዞ የታሰሩት። እነዚህ ሰዎች ከይቅርታው ተካፋይ መሆን አለብን ብለው እኛ ጋር መጡ። ትክክል ነው። እኛ የሃይማኖት ተቋማት ስንሆን የፖለቲካ ጉዳይ አይመለከተንም። እናም ለመንግሥት ይቅርታ ይደረግላቸው ብለን ደብዳቤ ጽፈናል።

ፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ብንሆን አናደረግውም። ነፍስ የገደለ ካልሆነ በቀር በምህረት በይቅርታ ሊታዩ ይገባል ብለናል። እናም ገለልተኛ መሆናችን ለማየት በምንሠራው ይለካን እንጂ በንግግራችን አይደለም። ነገም ቢሆን መንግሥት ያልሆነ መስመር ውሰጥ ቢገኝ፣ ለሕዝባችን ግልጽ ነው የምናደርገው። መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ መስመሩን ጥሶ ሃይማኖት ውስጥ ገብቶ እየፈተፈተ ነው ማለት እንችላለን። እስከ አሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ግን የገጠመን ነገር የለም። ከመንግሥት በጎ ሐሳብ ግን ይመጣል።

ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት (ግንቦት 7) ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃይማኖት አባቶችን ጠርተው ትልልቅ ሕዝብ፣ ትልቅ ሀብት አላችሁ፣ ግን ሕጻናትና ሴቶች ሲለምኑ እያየን ነው። እናም የሃይማኖት አገር ነን ማለት ይቻላል ወይ ብለው ትክክለኛ ጥያቄ አነሱ። እኛ እያለን እነ ቢንያም ሜቄዶንያን መሥርተው ችግረኞችን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማገዝ ከቻሉ፣ ሃይማኖት ተቋማት ግን ይህን መሥራት ካልቻልን፣ እውነት ተጽእኖ መፍጠር ችለናል ወይ ብለን ጥያቄ ውስጥ እንገባለን ማለት ነው።

በዛም ለምንድን እንደ ፋውንዴሽን ትልልቅ ሥራ አትሠሩም የሚል ጥያቄ መጥቷል። ሰው በዚህ መንግሥትና ሃይማኖት ተቀላቀለ ብሎ ማሰብ የለበትም። በትብብር እንሠራለን። መንግሥት እኔ አግዛለሁ፣ በአዋጅ እደግፋችኋለሁ፣ ተጽእኖ ፈጣሪ እንድትሆኑ እፈልጋለሁ ካለ፣ እንታገዛለን ማለት ነው።

ያ ማለት ግን የሚፈልገውን ሐሳብ ጫነብን ማለት አይደለም። እኛ ያስኬደናል አያስኬደንም ብለን አመዛዝነን፣ አውጥተን አውርደን ነው። አሁንም ምከሩበት ነው የተባለው። ጥሩ ዘመን ተሸጋሪ ሐሳብ ከሆነ፣ የሚጠቅም ከሆነ ማንም ያምጣው ማን፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤው መርህ የማያፈነግጥ ከሆነ፣ የተሻለ ሐሳብ ከሆነ እንወስደዋለን።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉት ከጉባኤው ጋር ይገናኛል ወይስ አዲስ ኅብረት ይመሥረት የሚል ነው?
ጉባኤው ራሱን የቻለ በሕግ የተመሠረተ ነው። ቀድሞም የነበረ ትብብር ነው። በሰላም፣ በአብሮነት፣ በመከባበር ብዙ ሥራ እየሠራ፣ አሁንም በሕዝብ ዘንድ እየተወደደ የመጣ ነው። ይህን ተሰሚነትና አብሮነትና መከባበር ይዛችሁ፣ ይህን ተጽእኖ መፍጠር ከቻላችሁ፣ ይህን በአንድ ወር ያሳያችሁትን አቅም በመጠቀም፣ እንደ ትልቅ ፋውንዴሽን ብትሠሩ ነው።

ሁሉም ሃይማኖቶች ከአብርሃም ይመነጫሉ የሚል ነገር አለ። እና ከአብርሃም የተገኛችሁ እንደመሆኑ፣ ዓለም ዐቀፍ መሆን የሚችል ፋውንዴሽን፣ ችግረኞች የምትረዱበት፣ ወጣቶችን የምታስተምሩበት፣ ሥራ እድል የምትፈጥሩበት መሆን የሚችል ማድረግ ትችላላችሁ የሚል ሐሳብ ነው የመጣው።

ሐሳቡ ጥሩ ነው፣ እናጥናው። ወደፊት እንምከርበት። የሚያስተባብረው ዞሮ ዞሮ ጉባኤው ነው። መሥራቾች ናቸው። ሌላ አዲስ የሃይማኖት ተቋማት አልመጡም። ይህንኑ ማጠናከር ነው። [የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር] ማፍረስ የመሰላቸው አሉ።

የተቋቋመ ኅብረት አለ፣ ግን ውስንነት አለው። ደርሶ እሳት የሚያጠፋና የሚያበርድ ዓይነት ሳይሆን፣ ጠንካራ የሆነ ዘመን መሻገር የሚችል ይሁን ነው። እንደውም ያን ዓይነት ሌሎችም ተቋማት ሊሳተፉ የሚችሉበት ነው የሚሆነው።

አንዳንዶች በጉባኤው እንዴት አራት ብቻ ሆኑ ይላሉ። ግን ትልልቆቹ ይጀምሩና ሌሎቹንም እየቀላቀሉ እያሳደጉ ይሄዳሉ ነው። እነዚህ አራቱ ግዘፍ ነስተው መውጣት አለባቸው የሚል ነው።

ለምሳሌ እያንዳንዳቸው ሃምሳ ሚሊዮን ብር ቢያዋጡ፣ ኹለት መቶ ሚሊዮን ብር የጋራ ሆስፒታል ወይም ዩኒቨርሲቲ፣ የችግረኞች መርጃ ማእከል ቢገነቡ፣ በቴሌቶን ምዕመናን አስተባብረው ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው ቢያስተባብሩ ይችላሉ። ሐሳቡ አእምሯችንን እንድናሰፋ ያደረገን አጀንዳ ነው። እንጂ አፍርሶ ስለመተካት አይደለም። ጉባኤው ዐስር ዓመት የቆየ የተመዘገበ ሕጋዊ ተቃም ነው።

እንደ እንግዳ ደራሽ ሳይሆን ተለፍቶበት ተደክሞበት ነው እዚህ የደረሰው። እኔ ባልኖርበትም የመሠረቱት ምስጋና የሚቸራቸው ናቸው። ሠሩ አልሠሩ ሌላ ጉዳይ ነው። ሁሉም በየጊዜው ነው የሚሠራው። ስለዚህ በጋራ የሚሠራ ነው የሚሆነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉባኤውን ለማፍረስ ሐሳቡም፣ ሕልሙም አላቸው ብዬ አላስብም። እንደዛ ዓይነት አስተሳሰብ ካለ፣ ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ነው የሚሆነው። እዛ ውስጥ ይገባሉ ብዬ አላስብም። ምክንያቱም መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ የተቀመጠ መስመር አለ። ገብተው እኛን ሃይማኖቶች እንዲህ ሁኑ፣ እናንተ እንዲህ ግቡ፣ በዚህ ውጡ ካሉ ነገ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት መንግሥትን ይህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አያስፈልግም፣ ይህ ወደዛ ይሂድ የሚል መጣረስ ይመጣል። ስለዚህ ሰው እንደዛ ቢመስለውም እንደዛ አይደለም።

የጉባኤው አባላት የሆኑ የሃይማኖት ተቋማት በጋር ሲመጡ የጋራ እሴትን መሠረት አድርገው ነው። ግን በየግላቸውስ የየራሳቸውን ቤት እንዲያጸዱና ችግራቸውን እንዲፈቱ በጉባኤው የሚደረግ ጫና አለ?
ይህን ገና ሐምሌ እና ነሐሴ (2011) የሠራው ሥራ ነው። አንደኛ ከሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ጋር አንድ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል። ቤተ እምነቶች ውስጣቸውን እንዲፈትሹ የሚያደርግ፣ ከሙስና፣ ከብልሹ አሠራርና ሥነ ምግባር ጋር የተየያዘ ሥራ እንዲሠራ ነው። አሁን የሃይማኖት ተቋማት ከመንግሥት ጋር ያላቸውን ችግሮች ነው ብዙ ጊዜ የሚያነሱት እንጂ የውስጣቸውን የራሳቸውን ችግር አያነሱም። በየቤተ እምነቱ ብዙ ችግርና ለቅሶዎች አሉ።

እናም ያንን በራሳችሁ መፍታት አለባችሁ ነው የምንላቸው። እኛ እንደ ጉባኤ የውስጥ አሠራር ውስጥ አንገባም። ግን እናማክራለን፣ ሥልጠና እንሰጣለን። ችግሩ እንዲቀረፍ የጋራ መስማሚያ ሰነድ አዘጋጅተን እንፈራረማለን። በዚህ መልክ ባለፈው ሥራዎች ጀምረናል፣ ጥሩ ውጤትም እየመጣ ነው።

ለምሳሌ ቦኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን አዲስ አበባ አገረ ስብከት አካባቢ ትልቅ ጩኸት ነበር። በሰዎች ዝውውር፣ ቅጥር ዙሪያ። እነዚህ ችግሮች ከሥልጠና በኋላ የተወሰነ ያህል ተቀርፈዋል። ጥሩ መስመር እየያዘ የመጣ ይመስለኛል። እንዲህ ያሉ ችግሮች በየቤተ እምነቱ አሉ። ያሉትን ችግሮች ራሳቸው እያጠሩ፣ እያስተካከሉ፣ መሄድ፣ አማኝ የሆነ ሰው በእምነት የሚሰጠውን ገንዘብ በእምነት ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል። እንዲጠራጠረው፣ አባትነቱን እንዲያሳጣው ሊያደርግ አይገባል። ከዚህ አኳያ በዚህ ላይ አስምረን እየሠራን ነው፣ ወደፊትም እንቀጥላለን።

እና የተነሳው ትክክል ነው። እንደዛ ዓይነት አሠራሮች አሁን መከተል እንደጀመርን ለማሳወቅ ነው። ሁሉም የራሱን ችግር እየቀረፈና ከራሱ ጋር ያለውን እያስተካከለ፣ ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር ያለውን ይመለከታል። አብዛኛው ችግር አስተዳደራዊ ናቸው። ከፋይናንስ አያያዝ፣ ግልጽነት፣ ቅጥርና ዝውውር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ናቸው አባል የሃይማኖት ተቋማት ጫና ደርሶብናል ብለው አቤቱታ የሚያሰሙበት ከጉባኤው መፍትሔ የሚያገኙበት መንገድስ አለ?
እንደዛ ዓይነት ጥያቄዎች አሉ። ቤተ እምነት ሆነው በተለይ ከካርታ ይዞታ ጋር በተያያዘ በካርታ ላይ ካርታ ወጣብን የሚሉ፣የተወረሰባቸው፣ መንግሥት አልመለሰልንም የሚሉና መሰል ብዙ ችግሮች ይነሳሉ። እነዛን እኛ የድጋፍ ደብዳቤ እንጽፋለን። እንደዛ ዓይነት ሥራ ውስጥ ዘልቀን ከገባን፣ ሌላ ሥራ ትተን ይህን ስናስተናግድ ልንውል ነው።

ግን እንዳልኩት የድጋፍ ደብዳቤ እንጽፋለን። አስፈላጊ ከሆነና በጉባኤው የተለየ ተብሎ ከተወሰነ፣ ጉዳዩን ይዘን ከሚመለከታቸው ጋር እንነጋገርበታለን። ከከተማ መስተዳደሮችና ክልል አስተዳደሮች ጋር በመገናኘት እየተወያየ እየፈታ ያለው ብዙ ጉዳይ አለ።

ባለፈው አንድ ወር በኢትዮጵያ አንጻራዊ መረጋጋት ነበር፣ ግጭቶችና ጭቅጭቆችም ጋብ ብለዋል። ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረግ ጥንቃቄም ጥሩ የሚባል ነበር። አሁንም በዛ መልክ እንዲቀጥል ምን ማድረግ ይገባል?
ትክክል ነው። ጸሎት ካወጅን በኋላ ወሩን ሙሉ አርፈናል፣ ኢትዮጵያም አርፋለች። የብሔር ንትርክና ከዚህም ከዚያም ከሚታይ ሃይማኖታዊ ትንኮሳ አርፈን ነበር። ሰዋዊ ነውና ግን በሰው ልጅ ሚሊዮን ፍላጎቶች ውስጥ፣ ሰው ይረሳል። ሰው ደግሞ የሠራውን ኃጢአትም፣ የተሰረገለትን በጎ ነገርም ይዘነጋል። መጽሐፋዊም ነው። በጎ ነገር በተደረገልህ ጊዜ አትርሳ ይላል።

ትላንት የነበረውን መከራ አይተናል፣ የአሁኑንም እያየን ነው። ወደ በጎ ነገር እንመለስ፣ ይቅር እንባባል ነው። ባልና ሚስት አልጋውን እየለየ ያለበት ሰዓት ነው። ይህን ያህል የሚለያይ በሽታና መቅሰፍት ነው የመጣው። ከአንድ ቤተሰብ አንድ ሰው ኮሮና ከያዘው፣ ያ ሰው ወደ ለይቶ ማቆያ ይገባል። ወንድሜ ነው ወይም ልጄ ነውና አብሬ እገባለሁ የሚል የለም። ይለያያል፣ ይከፍላል። ሰው ይህን እያየ እንኳ ንስሀ የማንገባበት፣ ወደ ፈጣሪ የማንመለስበት፣ በጎ ነገር የማናስብ፣ መልካም የማያሳየን ብዙዎች አለን።

አሁንም ሰው ወደ መዘናጋቱ፣ ወደ ጥሉ መጥቷል፣ ሰው ወደ ጥንታዊ ክፉ ባህሪው እየተመለሰ ይመስለኛል። አስቀድሞ እንዳልኩት በኮቪድ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር የጨመረውም በሥራችን ነው። ስንከፋበት በሽታውም ይከፋል። በትንፋሽ ይተላፍ እንጂ ራሱ መንፈስ ነው።

እናም ባለፈው ጾም ውስጥ የነበረው አንድነት አሁን እየተዘነጋና እየተሸረሸረ ነው። ሞት ቢጀምር ደግሞ ከተማው ጭር ይል ነበር። ዝጋ ባይባልና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባይታወጅም በሩን ቆልፎ ይቀመጣል። እኛ ውጪ የሆነው ዓይነት ደርሶብን ስላላየን ነው። የእኛ ሰው ደግሞ ካላየሁ አላምንም የሚል ዓይነት ነገር ነው። አሁንም መንግሥት ሞት አለ ይላል፣ ምንም የለም ነው የሚለው ሰዉ።

በራሱ ነው ሰው መማር እየፈለገ ያለው። ሞኝ ካልሆነ በቀር ሰው እንዴት በራሱ ይማራል? ብልጥ ሰው በጎረቤት ይማራል ይባላል። ኢትዮያውያን ብልጥ ነበረን፣ አሁን ሞኝ እየሆንን ይመስለኛል።

ከመንግሥት ጋር ግብ ግብ መፍጠር ተገቢነት አለው ብዬ አላምንም። አዋጁ የሕዝብን ደኅንነት ለማከበር የወጣ አዋጅ ነው ብዬ እንደግለሰብ አምናለሁ። ግብግብ ከገባን፣ ካልተሰበሰብኩኝ፣ ሰልፍ ካልወጣሁ ከተባለ ግን አስቸጋሪ ነው። የለም ተብሎ ሲከለከል ደግሞ መብቴ ተጣሰ ይላል። መጀመሪያ የተከለከለውም ለደኅንነቱ ነው። መንግሥት ለሥልጣኑ ለወንበሩ አይደለም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው፣ ለራሳችን ደኅንነት ነው።

ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት የፖለቲካ እና የብሔር ግጭቶች ይታዩ ነበር። አልፎም የሃይማኖት ግጭቶችን አይተን ነበር። ድኅረ ኮሮና ወደዛ እንዳንመለስም በጉባኤው በኩል እየተሠራ ያለ ነገር አለ?
እዚህ ላይ አማርኛው ሊታረም ይገባል። የሃይማኖት ግጭት የሚባል ነገር የለም። የሃይማኖት ግጭት ማለትኮ ሃይማኖቶች መሠረታዊ አስተምህሯቸው ሲጋጩ ነው። ግን ለዛ መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች መጽሐፍቶቻችን ላይ የሉም። ታድያ ከየት መጣ? ሰው በራሱ አስተሳሰብ በራሱ ጎዳና ስለሚነጉድ ነው። የራሱን ፍላጎት እያካተተ ሃይማኖትን ሽፋን ስለሚያደርግ ነው።

እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እስልምናን አጥፋ የሚል የለውም፣ እስልምናም ክርስትናያንን እንዳታይ፣ ብቻህን ካልሆነ ከሌላ ሃይማኖት ጋር አትኑር የሚል የለም። ግጭት የሚነሳው ሰው በራሱ በተፈጥሮው ራስ ወዳድና ከእኔ ውጪ ሌላ አልፈልግም ስለሚል ነው።

ከዚህ የተነሳ ስለሆነ የአስተሳሰብ ግጭቶች ይኖራል። ዞሮ ዞሮ ያ እንዳይሆን ሐሳብ ላይ መሥራት አለብን። ያልተሠራ ትውልድ ነው አፍራሽ የሚሆነው። ሰው ላይ መሠራት አለበት። የሥነ ምግባር ጉዳይ የምናነሳውና ቤተ እምነቶች በዚህ ላይ ጫና መፍረር አለባቸው የምንለው፣ ከዚህ አኳያ ነው። ያልተሠራ ትወልድ መንገድ እየዘጋ፣ ፋብሪካ እያቃጠና እያነደደ ይኖራል። ስላልተሠራ የተሠራ ነገርንም ያጠፋል።

ድርጅት ከመሥራት በፊት መጀመሪያ ሰውን ነው መሥራት የሚያስፈለግው የሚባለው ለዚህ ነው። በተለይ ቤተ እምነቶች ደግሞ ለዚህ ቅርብ ናቸው። ልጆችን በቤተ እምነት እያሳደጉ ከፍ እያደረጉ፣ ጥቅምና ጉዳቱን ማሳወቅ አለባቸው። ሰው እንዴት የራሱን ቤት አቃጥሎ እስፋልት ላይ ይተኛል? አገሩን እያፈረሰ እንዴት ነው ስደት የሚመጣው? በስደት ጥገኝት መጠየቅ፣ በረንዳ ማደር ነው የሚመጣው። ሰው ራሱ ቤቱን ማፍረስ የለበትም የሚለውን ቤተ እምነቶች መሠረታዊ አስተምህሮ አድርገው ሊያስተምሩ ይገባል የምንለው ለዛ ነው።

አሁን ወደ እርስዎ ልምጣ። በጉባኤው ወደ ኃላፊነት ከመጡ ገና አንድ ዓመት ነው። ሲመጡ ምን ጠብቀው ነበር? ባለፈው አንድ ዓመትስ ምን ተሠራ?
እሠራለሁ ብዬ ጠብቄ የመጣሁት የሠላምን ሥራ ነው። አሁንም እሱን እየሠራሁ ነው ብዬ አምናለሁ። እኔ የመጣሁበት ሰዓትና ጊዜ የሚሰጥ አይደለም። ዞሮ ዞሮ ግጭትና አፈታቱ ላይ ነው የምንሠራው። አብዛኛውንም ተወጥተነዋል። ያንን ባንሠራ ኖሮ ሊሆን የሚችለው ካባድ ይሆን ነበር።

እንደመጣሁ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ነው የግብረ ሰዶም ቡድን (ቶቶ አስጎብኚ) ለጉብኝት ኢትዮጵያ እንመጣለን ማለቱን ተከትሎ ሥራዬን በዛ ነው የጀመርኩት። ከዛ ቀጥሎ ግን 11/11/11 መጡ፣ የሲዳማ ጥያቄ ተነሳ። በዛም አንድ ወር ሄደን ከረምን። ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ ነበር። እሱም ጥያቄ የፖለቲካ ቢሆንም ያወራረዱትና ዋጋ የከፈሉት ቤተ እምነቶች ናቸው። ጥያቄው ግን ክልል እንሁን ነው። ውጤቱ በአንጻሩ የቤተ እምነቶች መቃጠል ነው።

በመስከረምና ጥቅምት አካባቢ የ86 ሰዎች ሕይወት አለፈ። በዛም ጉዳይ በጣም ዋጋ ከፍለናል። ብዙ ቤተ እምነቶች ተቃጥለዋል፣ ብዙ ሰዎች ተሰውተዋል። ይህም ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ ነበር፣ ጥያቄው ግን ሌላ ነበር። ስለዚህ ወደዚህ ሥራ ውስጥ ነው የገባነው። ታኅሳስ ውስጥ ደግሞ የሞጣ ጉዳይ መጣ። ይህም እረፍት የሚነሳ ጉደይ ነው። እሱን ሳንጨርስ ደግሞ ጥር ውስጥ በሐረር የጥምቀት በዓል ከሰንደቅ ዐላማ ጋር ተያይዞ እረፍት የነሳን ሥራ ነበር። መጋቢት መጀመሪያ ላይ ደግሞ ይህ ወረርሽኝ (ኮቪድ 19) መጣ።

እናም አቅደሽ ልትሠሪ ቀጥሎ የሚሆነውን የምታውቂበት አይደለም። አካሄዳችንን እየመሩ ያሉት ወቅታዊ አጀንዳዎች ናቸው። ወረርሽኙን ስንወጣ ምን እንደሚመጣ ደግሞ አናውቅም። እንሠራለን ብለን ያቀድነው በተለይ በሰላም ግንባታ ግን ብዙ አለ።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here