ለሕዝብ ቆጠራ የተገዙ ታብሌቶች ለፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ሊከፋፈሉ ነው

0
823

በአገር ዐቀፍ ደረጃ ለሦስተኛ ጊዜ ለማካሄድ ታቅዶ የነበረውን የቤትና ሕዝብ ቆጠራ በቴክኖሎጂ ለማገዝ በሚል በመንግሥት ተገዝተው የነበሩ 180 ሺሕ ታብሌቶች ያለሥራ ከመቀመጣቸው ጋር ተያይዞ ወደ ፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ሊከፋፈሉ መሆኑ ተገለፀ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በወሰነው ውሳኔ መሠረት በከፍተኛ ወጪ ተገዝተው በማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ውስጥ የሚገኙት ታብሌቶች ሕዝብ ቆጠራው ከመራዘሙ ጋር እንዲሁም ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ወደ ፌደራል መሥሪያ ቤቶች እንዲከፋፈሉ ከገንዘብ ሚንስትር ዲኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ደብዳቤ መጻፉን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ጉዳዮን በሚመለከት የገንዘብ ሚነስቴር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሐጂ ኢብሳ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ታብሌቶች ተገዝተው ረጅም ጊዜ በመቀመጣቸው እና ሕዝብ ቆጠራውም በመራዘሙ ለብልሽት እንዳይጋለጡ በሚል የሚኒስትሮች ምክር ቤት የወሰነ ሲሆን ይህንም ተከትሎ በኮቪድ ምክንያት ቤታቸው ሆነው ለሚሠሩ የፌዴራል መሥሪያ ቤት ሠራተኞች እገዛ እንዲያደርግ መታሰቡን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት ዕቃዎችን በዋናነት ማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሚያስተዳድራቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በመጀመሪያ ደረጃ የተሰረቁ ወይም ቁጥራቸው የጎደለ ከሆነ ይቆጠራል ብለዋል። አያይዘውም በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኩል ደግሞ የታብሌቶች መሥራት እና አለመሥራት ተረጋግጦ ለ187 የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች እንደሚከፋፈል አስታውቀዋል።

ከታብሌቶች ቁጥር ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ እና ቦረና ዞን ሥልጠና ሰጪዎች ከኤጀንሲው የተሰራጩትን 120 ታብሌቶች ለመመለስ ፈቃደኞች ሳይሆኑ መቅረታቸውን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የማእከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ለሦስተኛው የሕዝብ ቆጠራ በሚል የቅድመ ዝግጅት 180 ሺሕ ታብሌቶችን እና 126 ሺሕ ተንቀሳቃሽ የኃይል መሙያዎችን (ፓወር ባንኮችን) መግዛቱ ይታወሳል። በዚህም ረገድ 665 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገባቸውም ታውቋል። በጊዜው በተካሄደው የግዢ ጨረታም ኹለት ዓለም ዐቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ማለትም ሊኖቮ እና ሁዋዊ የተባሉ ኩባንያዎች መመረጣቸው ታውቋል።

በዚህም ምክንያት ለሊኖቮ ድርጅት 141 ነጥብ 7 ዶላር በአንድ ታብሌት የተከፈለው ሲሆን፣ ፓወር ባንክ ለሚያቀርበው የቻይናው ሁዋዊ ኩባንያ ደግሞ 25 ዶላር በአንድ ፓወር ባንክ ተከፍሎታል። ከዚህም በተጨማሪ ወደ አገር ውስጥ በሚያጓጉዙበት እና እቃውን እስኪያስረክቡ ድረስ ያለው የትራንስፖርት ወጪ 15 ነጥብ 75 እና 14 ነጥብ 63 ብር፣ ለእያንዳንዱ እቃ እና ለኩባንያዎች በቅደም ተከተል ተከፍሏቸዋል።

ለሕዝብ እና ቤት ቆጠራ በአጠቃላይ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ተመድቦ የነበረ ሲሆን፣ የተመደበው ገንዘብም ከአገር፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ከውጪ ለጋሽ አገራት እንደተገኘ ተገልጿል።

ይሁን እንጂ በመጋቢት 2011 በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን የተጠራው አስቸኳይ ስበሰባ፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ሊካሄድ የታሰበውን የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ዕጣ ፋንታ የወሰነ ነበር። እንደመነሻ ሆነው ደግሞ በክልሎች ለሕዝብ እና ቤት ቆጠራ የሚሆኑ ግብዓቶችን አሰራጭቶ መጨረስ ካለመቻሉም ባለፈ፣ በተለይም ደግሞ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት የቀረበውን ከሰላም እና ጸጥታ ጋር የተያያዘ ችግር ቆጠራውን ለማካሄድ እንደማይቻል አንደኛ ማሳያ እንደነበር ይታወሳል።

በኅዳር ወር 2009 ይካሄዳል ተብሎ በትክክለኛው ጊዜ ገደብ ተጠብቆ የነበረው የሕዝብና ቤት ቆጠራ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ሲተላለፍ ቆይቷል። በሕገ መንግሥቱ መሠረት አገር ዐቀፍ ሕዝብና ቤት ቆጠራ አስገዳጅ ሁኔታዎች ካላጋጠሙ በየዐስር ዓመቱ የሚካሄድ አገራዊ ኹነት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here