ነፃ የትምህርት እድል ያገኙ ተማሪዎች በፓስፖርት ክልከላ መስተጓጎላቸውን ገለጹ

0
632

ከውጭ አገራት ነፃ የትምህርት እድል ያገኙ ተማሪዎች ከፓስፖርት ማሳደስ እና ማውጣት ጋር ተያይዞ አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው ያገኙት እድል እያመለጣቸው መሆኑን ገለጹ።

በኒውዚላንድ አገር ነጻ የትምህርት እድል ገጥሟቸውና የማረጋገጫ ደብዳቤ ደረሷቸው የጉዞ ሰነዳቸውን (ፓስፖርታቸውን) ለማሳደስ ወደ ኢሚግሬሽን እና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ቢሄዱም፣ አገልግሎት ማግኘት እንደማይችሉ እንደተገለጸላቸው ሥማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንደሚናገሩት፣ በኤጀንሲው በአካል በተገኙበት ወቅት በተገቢው መንገድ የሚያናግራቸው እንዳላገኙ እና ያገኙት ምላሽ ኤጀንሲው ፓስፖርት ጋር ተያያዥ ጉዳዮችን ማስተናገድ ማቆሙን እንደሆነ ጠቁመዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ፓስፖርታቸውን ማሳደስ የማይችሉ ከሆነ ለረጅም ጊዜያት ሲጠብቁት የነበረው የውጭ አገር ነጻ የትምህርት እድል እንደሚያመልጣቸው እና ካሰቡት መስመር እንደሚያስወጣቸው ጨምረው ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ በበኩሉ፣ መንግሥት አጠቃላይ በአገሪቱ በወሰነው ውሳኔ መሰረት የተቀመጡ ክልከላዎች ቢኖሩም ኤጀንሲው አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሷል። ነፃ የትምህርት እድል አግኝተናል የሚሉ ሰዎችም የትምህርት እድሉን የሰጣቸው አገርና ነፃ የትምህርት እድል ማግኘታቸውን የሚገልጽ የድጋፍ ደብዳቤ ከትምህርት ሚኒስቴር እንዳላቀረቡ የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ደሳለኝ ተሬሳ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በአሁኑ ጊዜ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳይሰራጭ አገልግሎቱን በከፊል ማቋረጡን ተከትሎ በረራ የተከለከለባቸው አገሮች የሚሄዱ ከሆነ አገልግሎቱን መስጠት እንደማይቻል፣ ነገር ግን በረራ ወዳልተከለከለ አገሮች መጓዝ እንደሚችሉ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጨምረው ጠቅሰዋል።

ኃላፊው አክለውም ከዚህ ቀደም ነፃ የትምህርት እድል አግኝተናል በማለት እድሉን ከሰጣቸው አገር ወይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እውቅና የሌለውና ከትምህርት ሚኒስቴር እውቅና ያላገኙ ሰዎች በራሳቸው ፕሪንት በማድረግ ሕጋዊ ያልሆነ አካሄድ ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁንም በተመሳሳይ ድጋፍ እንዳላቀረቡ ገልጸዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ስርጭት ለመከላከል ሲባል ኤጀንሲው አገልግሎቶቹን በከፊል ማቋረጡን ተከትሎ፣የሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሕክምና ጉዞ፣ አስቸኳይ የመንግሥት ሥራና ተዛማጅነት ባላቸው ጉዳዮች መሆኑን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስረድተዋል። በዚሁም መሰረት ማንኛውም የመደበኛ አዲስ ፓስፖርትና የእድሳት አገልግሎቶች እንዲቋረጥ የተደረገ ሲሆን፣ የትውልደ ኢትዮጵያዊ እና የመኖሪያ ፍቃድ አገልግሎቶችም በተመሳሳይ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጠው ነበር።

ቢሆንም ጉዞ ወደ ተፈቀደባቸው አገር የመኖሪያ ፈቃድ ያለው ተገልጋይ አሁን ላይ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችለና ጉዞ ማድረግ እንደማይከለከል ደሳለኝ አንስተዋል።

በሌላ በኩል ኤጀንሲው ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባው ፓስፖርት ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ መግባቱን ኃላፊው የገለጹ ሲሆን፣ ኤጀንሲው በአሁኑ ሰዓት በቂ የሚባል ክምችት አለው ብለዋል። ቢሆንም ለወደፊቱ በቂ እንዳልሆነና ተጨማሪ እንደሚያስፈልግ ኃላፊው አክለው ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና በድንበር ቁጥጥር ሥራ በኩል ከጅቡቲ በጋላፊ ኬላ በኩል በሕገ ወጥ መልኩ የኢትዮጵያ መንግሥት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈፀሚያ ደንቡን በመተላለፍ 22 ኢትዮጵያን በጭነት መኪና ተጭነው በስውር ወደ አገር ሊገቡ ሲሉ በኤጀንሲው ሠራተኞችና ፀጥታ አካላት ትብብር በቁጥጥር መዋላቸውን እና በአሁኑ ስዓት በአፋር ክልል በለይቶ ማቆያ እንደሚገኙ የኤጀንሲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ዜጎችን ባልተፈቀዱ መንገዶች ከጎረቤት አገራት ጋር በውል ያልተከለሉ ኬላዎችን ሽፋን በማድረግ በዚህ ዓይነት ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ላይ በቀጣይ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here