የሱማሌ ክልል ምክር ቤት አባላት በፖሊስ ተደበደቡ

0
1025

ምክር ቤቱ በ12 አባላት ላይ ያለመከሰስ መብታቸውን አንስቷል

የሱማሌ ክልል ምክር ቤት አባላት በምክር ቤቱ አሰራር ደንብ መሰረት የተጣሰ ሕግ አለ በማለት ስብሰባ ረግጠው በመውጣታቸው እና ቅሬታቸውን ለሚዲያ አካላት ለመናገር በመሞከራቸው በጸጥታ አካላት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ተገለጸ።

ድብደባ የደረሰባቸው የምክር ቤት አባላት ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ አንገብጋቢ ጉዳዮች መኖራቸውን እና ኮቪድን ጨምሮ አሁን ክልሉን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው መንግሥት በብልሹ አሰራሮች እየተዘፈቀ በመሆኑ ውይይት እና ማስተማመኛ ድምጽ ሊሰጥበት ይገባል የሚል ጉዳይ በመነሳቱ ነው። እንዲሁም እነዚህን ጉዳዮች በማንሳት ውይይት የማይደረግ ከሆነ ግን በመንግሥት በኩል የቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ውይይት የማያደርጉ መሆኑን መናገራቸውን ይጠቅሳሉ።

የምክር ቤት አባል የሆኑት ኒያም ሐማሬ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ የተፈጠረውን ጉዳይ ሲያስረዱ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ መሐመድ በውስጣቸው የያዟቸው አመራሮች ከፍተኛ የሆነ ሙስና ውስጥ በመግባታቸው እና ሙስጠፌም አንድ ብቻቸውን ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ምንም አይነት ችግሩን የመቅረፍ አቅም እንደሌላቸው በምክር ቤት አባላት ዘንድ በመታመኑ አባላት ግምገማ ማካሄድ ፍላጎት እንዳላቸው መታመኑን አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ በወቅቱ 180 አባላት የተገኙበት ስብሰባ ውስጥ 58 የሚሆኑት በቀረቡት አጀንዳዎች ላይ እንወያይ የሚለውን ሲደግፉ፣ ቀሪዎቹ ግን መጀመሪያ ደረጃ አንገብጋቢ የሆኑ አጀንዳዎች ላይ መወያየት ይገባናል በሚል ሳይደግፉ ቀርተዋል። ይሁን እንጂ ቆጠራ በተካሄደበት ወቅት ከአፈ ጉባዔዋ በኩል 154 ድጋፍ ስለተገኘ መደበኛ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ይደረግ የሚል ውሳኔ ላይ በመደረሱ ስብሰባውን ረግጠው ለመውጣት እንደተገደዱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ኒያም አክለው ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከአዳራሹ በወጡበት ቅጽበት ከስምንት እስከ ዘጠኝ የሚደርሱ የልዩ ኃይል መኪናዎች ፖሊሶችን ጭነው በመምጣት መንገድ እንደዘጉባቸው እና ከፍተኛ የሆነ ድብደባ እንደፈጸሙባቸው ጠቁመዋል። በዚህም ሳቢያ በከፍተኛ ደረጃ የተጎዱ የምክር ቤት አባላት መኖራቸውን ጨምረው ጠቅሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለሚዲያ አካላት መግለጫ እና መረጃ ለመስጠት የሞከሩ የምክር ቤት አባላት ክፉኛ እንደተደበደቡ እና የሚዲያ አካላትም ካሜራቸው እና የድምጽ መቅረጫቸው በጸጥታ አካላት ከመወሰዱም ባለፈ ከፍተኛ የሆነ ድብደባም እንደተፈጸመባቸው አዲስ ማለዳ ምንጮች ከስፍራው አስታውቀዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍን ጨምሮ ስድስት አጀንዳዎችን ይዞ ግንቦት 13/2012 ምክር ቤቱ 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን ለማካሄድ በተሰበሰበበት ወቅት 180 አባላት በመገኘታቸው ጉባዔው ስብሰባውን ጀምሯል። ከዚህ ቀደም በበጀት ዓመቱ በጀት በጸደቀበት ወቅት አንድ ጊዜ ከተሰበሰበ በኋላ መስከረም ወር ላይ በወንጀል የሚፈለጉ የምክር ቤት አባላትን ያለመከሰስ ከለላ ለማንሳት ከመሰብሰቡ ውጭ ምንም አይነት መደበኛ ጉባኤ አካሂዶ አለማወቁ ደግሞ በምክር ቤት አባላት ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደተደረገበት ተጠቁሟል።

የክልሉ ምክር ቤት በበኩሉ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ እንደሆነ እና አዳዲስ የካቢኔ ሹመቶችንም ለማጽደቅ አጀንዳ መያዙን አስታውቋል። የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩትን የመልቀቂያ ጥያቄ በአብላጫ ድምጽ በመቀበል ካጸደቀ በኋላ፣ በክልሉ ፕሬዘዳንት የቀረበውን የመንግሥት የሥራ አፈጻጸምም እየገመገመ እንደሚገኝ ታውቋል።በግምገማ ውሎውም ምክር ቤቱ በ12 አባላት ላይ ያለመከሰስ መብታቸውን ከሙስ እና ከሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አንስቷል።

ይሁን እንጂ በምክር ቤት አባላት ላይ የተፈጠረውን ድብደባ እና ጉዳት እንዲሁም ዛቻ በማስመልከት ተጨማሪ ማብራሪያ እና የመንግሥትን ምላሽ ለማግኘት አዲስ ማለዳ ወደ ክልሉ የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ኃላፊዎች ያደረገችው ሙከራ ‹ቆይተን እንደውላለን!› በሚል የአጭር የጽሑፍ መልዕክት ምላሽ ውጭ በቂ ምላሽ ሳታገኝ ቀርታለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 81 ግንቦት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here