የኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ 98 በመቶ ኪሳራ ውስጥ መግባቱ ተገለጸ

0
858

የኢትዮጵያ ሆቴል ባለሙያዎች ማኅበር በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ኢትዮጵያ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ 98 በመቶ ቀውስ ውስጥ መግባቱን አስታወቀ።
ማኅበሩ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ይህ ኪሳራ መከሰቱን የገለጸው ትላንት ግንቦት21/2012 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ይህንን ተከትሎ መንግሥት የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ከገባበት ጫና እንዲያገግም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በመንግሥት በኩል ለዘርፉ ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም አንዳንድ ሆቴሎች ለረጅም ዓመታት ያገለግላሉ ሠራተኞችን ጨምሮ ጠቅላላ የሰው ኃይላቸውን ደሞዝ መቀነስ ከሥራ ማባረራቸውን በማንሳት ይህ ኢትዮጵያዊነትን ያላማከለ አሠራር እንዳሳሰበውም ማኅበሩ አስታውቋል።
በመሆኑም የሆቴል ባለቤቶች በኢትዮጵያ የተጋረጠውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተግዳሮት ለመሻገር ከመጨካከን ወጥተው ለሠራተኞቻቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉና ከእኩይ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማኅበሩ አሳስቧል።
በተያያዘ ምሳሌ በመሆን ለሠራተኞቻቸው አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ ያሉ የሆቴል ባለቤቶችን ማህበሩ አመስግኗል። ወቅቱን ለመሻገር ከመንግሥት ጎን በመቆም እንደሚሠራም በመግለጫው አመላክቷል።
አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት የተለያዩ ሆቴሎች ሠራተኞቻቸውን ያለ አግባብ ክፍያ ሳይፈጽሙ ከሥራ ገበታቸው እያፈናቀሉ መሆኑን መዘገቧ የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here