ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ከ‹ስቴም-ፓወር› ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

0
373

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ /ኢንሳ/ ‹ስቴም-ፓወር› ከሚሰኝ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግ እና በሒሳብ ዘርፎች ዙሪያ ከሚሠራ ተቋም ጋር በዘርፉ ታዳጊዎችን የማብቃት ሥራዎች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።
በኢንሳ በኩል በስምምነት ሰነዱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) ስምምነቱ ኤጀንሲው ከፍተኛ የፈጠራ አቅም ያላቸውን ታዳጊዎችን በመደገፍ በሳይበር እና የሳይበር ደኅንነትን ለማረጋገጥ ለሚሠራው ሥራ ጉልህ አስተዋፅዎ የሚያበረክት ኃይል ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
የሳይበር ደኅንነትን ለማረጋገጥ ኤጀንሲው በራሱ ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ በርካታ ባለድርሻዎች በዘርፉ እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሚያስፈልግና በተለይም የሥራ ዕድልን እንዲፈጥር፣ ዘርፉ በራሱ ምርት እንዲሆን፣ አገልግሎት እንዲሰጥ እንዲሁም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተፅዕኖው የጎላ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ስምምነቱ እገዛ እንደሚኖረውም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
በስምምነቱ ወቅት ‹የስቴም-ፓወር› ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቅድስት ገብረአምላክ፣ ድርጅታቸው በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግ እና በሒሳብ ሥራ የፈጠራ አቅም ላላቸው ሕጻናትንና ወጣቶች ተግባር ተኮር እገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
ከኢንሳ ጋር የተደረገው ስምምነትም በድርጅታቸው በፈጠራ ሥራ ድጋፍ እየተደረገላቸው ከሚገኙ ታዳጊዎች መካከል በሳይበር ደኅንነት ዘርፍ ከፍተኛ አቅም ያላቸውን ወጣቶች ለኤጀንሲው እሴት እንዲሆኑ ዕድል የሚፈጥር ነው ሲሉ ሥራ አስፈጻሚዋ አብራርተዋል።
በኹለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው ስምምነት ከ3 እስከ 5 ዓመት እንደሚቆይም ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here