ለዓመት የተጓተተው ዕቃ ግዢ ሂደት በ227 ሚሊዮን ብር ውል ተደመደመ

0
652

ለአንድ ዓመት ገደማ የቆየው እና ኹለት የግዥ ጨረታ ሂደቶችን ያስተናገደው የ22 ዩኒቨርሲቲዎች የፕሪንትና ፎቶ ኮፒ ማሽን ግዢ በ227 ሚሊዮን ብር ከሰባት ድርጅቶች ጋር ውል ተፈጸመ።

ለ22 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ለሦስት ዓመታት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የታሰቡ የጋራ መጠቀሚያ ዕቃዎችን በማዕቀፍ ስምምነት ግዥ ለመፈፀም ነሐሴ 21/2011 በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዓለም ዐቀፍ ግልፅ ጨረታ የመንግሥት ኤጀንሲ አውጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ የጨረታ ሂደቱ በዚያው ዓመት ተጠናቆ ግዥው ሊጠናቀቅ እንዳልቻለ ለማወቅ ተችሏል።

ለዚህም እንደ ምክንያት የተነሳውን ጉዳይ ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ ሲያብራራ፣ ተጫራቾች በወቅቱ ያቀረቡት የተፈላጊ ዕቃዎች ደረጃ ለኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ኤጀንሲ ተልኮ የደረጃ ምዘና ሲደረግ ከሚፈለገው ደረጃ በታች ሆኖ በመገኘቱ ሊዘገይ እንደቻለ የኢትዮጵያ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ መልካሙ ዴፋሊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት ጨረታው በድጋሚ መስከረም 29/2012 ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ላይ ተዘግቶ በዚያው እለት ከጠዋቱ 4፡30 ሰዓት ላይ መከፈቱን መልካሙ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ጨረታው ዳግመኛ የተከፈተው ተጫራቾች ያቀረቡት ደረጃ ከ70 ወደ 80 ከፍ እንዲልና የግዥ አገልግሎቱ ቀድሞ አስቀምጦት የነበረውን የዕቃዎች ደረጃ ከ90 ወደ 80 ዝቅ እንዲል በማድረግ በተሰሚነትና ምዘና ኤጀንሲ በኩል ስምምነት ላይ ተደርሶ ዳግመኛ ጨረታው እንደወጣ መልካሙ አብራርተዋል።

መልካሙ እንደገለጹት ብዙ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የውጭ ምርቶች በድርጅቶች በኩል ከደረጃ በታች ይገባሉ። ይህም ድርጅቶች የሚያቀርቡት የዕቃዎች ደረጃ እና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚገዙ ዕቃዎች ደረጃ ብዙ ጊዜ አለመመጣጠን እንደሚያጋጥም አስታውቀዋል። በመሆኑም የደረጃ ልዩነቱን ለማጣጣም በአቅራቢ ድርጅቶች በኩል የቀረበውንና ግዥ ከሚፈጸምላቸው መሥሪያ ቤቶች በኩል የቀረበውን የደረጃ ልዩነት ለማጣጣም አማካይ ደረጃ ላይ የማገናኘት ሥራ እንደሚሠራ ተጠቁሟል።

በወጣው ዓለም ዐቀፍ ግልፅ ጨረታ 112 ድርጅቶች ከሎት አንድ እስከ ሎት አምስት የጨረታ ሰነድ የገዙ ሲሆን፣ 44 ተጫራቾች በጨረታው ለመሳተፍ የመጫረቻ ሰነዳቸውን አቅርበው እንደነበርም ታውቋል።

የፕሪንተርና የፎቶ ኮፒ ማሽን ቶነሮች ላይ አስራ አራት ተጫራቾች የመወዳደሪያ ሰነዳቸዉን አቅርበዋል። በሎት ኹለት ላይ ተጫራቾች ባቀረቡት የቴክኒክ ሰነድ ላይ የቅድመ ግምገማ ተከናዉኖ ከተወዳደሩት 13 ተጫራቾች መካከል ኹለት ተጫራቾች በቅድመ ግምገማዉ የወደቁ ሲሆን፣ 11 ተጫራቾች ብቻ የቴክኒክ ግምገማ አልፈዋል።

አስፈላጊዉ የቴክኒክ ግምገማ፣ የድኅረ ግምገማ እና የፋይናንስ ግምገማ ተከናዉኖ በሎት ኹለት የፕሪንተርና ፎቶ ኮፒ ማሽን ቶነሮች ግዥ ላይ የተወዳደሩ አሸናፊ ተጫራቾች ተለይተዋል።

በዚሁ መሰረት የተለዩት ተጫራቾች ግዥ ለመፈጸም ኤጀንሲው ከናሽናል ማርኬተርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በ14.4 ሚሊዮን ብር፣ ከናኖዳስ ትሬዲንግ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በ169.3 ሚሊዮን ብር፣ ከማፍ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በ33 ሚሊዮን ብር፣ ከአዲስ ኢሜጅ ትሬዲንግ በ305 ሺሕ ብር፣ ከቪር ጄኔራል ትሬዲንግ በ803 ሺሕ ብር፣ ከቶነር አሴምብሊ ማኑፋክቸሪንግ በ678 ሺሕ ብር እና ከርካድ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ በ9 ሚሊዮን ብር ግዥ ለመፈጸም ኤጀንሲው የአሸናፊነት ደብዳቤ ለሰባት አሽናፊ ድርጅቶቹ መስጠቱን መልካሙ ተናግረዋል። በአጠቃላይ አገልግሎቱ ከሰባት ድርጅቶች በ227.59 ሚሊዮን ብር ግዥ ይፈጸማል።

ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here