የኃይል ማመንጫ ግድብ ከዚህ በኋላ እንደማይገነባ ተገለጸ

0
514

ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ምንም አይነት በመንግሥት የሚገነባ የኃይል ማመንጫ ግድብ እንደማይኖራት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ትኩረቱን ያደረገው የተጀመሩ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ጨርሶ ለአገልግሎት ማዋል ላይ ነው። ከዛ ባለፈ ምንም ዓይነት ኃይል ማመንጫ ግድብ ከዚህ በኋላ እንደማይገነባ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሞገስ መኮንን፣ በመንግሥት የተጀመሩትን ከማጠናቀቅ ውጪ አዳዲስ ግድቦችን ከዚህ በኋላ የመገንባት ፍላጎት እንደሌለው እና ወደ ሌሎች የኃይል ማመንጫ አማራጮች ፊቱን እንደሚያዞር ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባሻገር ሌሎች በመገንባት ላይ የሚገኙ ተጨማሪ የኃይል ማመንጫ ግድቦች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በመጪዎቹ ዓመታት ተጠናቀው ሲያልቁ ትኩረቱ ወደ አማራጭ የኃይል ማመንጫዎች እንደሚዞር ነው አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘችው መረጃ የሚያመላክተው።

የነፋስ ኃይል፣ የፀሐይ እና የእንፋሎት ኃይል ማመንጫዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚሠራ በመንግሥት በኩል አቅጣጫ መቀመጡን የተናገሩት ሞገስ፣ ይህም ለግሉ ዘርፍ ክፍት እንደሆነም አስታውቀዋል። በአሁኑ ሰዓት በርከት ያሉ የውጭ አገር ኩባንያዎች በእንፋሎት እና በፀሐይ ኃይል ማመንጨት ላይ ትኩረታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉ ሲሆን፣ ይህም በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃትን እና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ አልሚዎችንም የሚስብ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ግል ይዞት በሙሉ ወይም በከፊል ይዞራል ተብለው ከተወሰኑ የመንግሥት የልማት ድርጅት ውስጥ አንዱ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዓት ወደ ግል ይዞታ በሙሉም ሆነ በከፊል ለማዘዋወር እየተደረገ ያለ እንቅስቃሴ አለመኖሩንም አዲስ ማለዳ ከመሥሪያ ቤቱ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ በቂ ያልሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ሳታዳርስ ለጎረቤት አገራት ኃይልን ለሽያጭ ማቅረቧ ከፍተኛ የሆነ ትችት በዜጎች ዘንድ ሲቀርብ መቆየቱ የሚታወስ ነው። ከዚህ በላይ ግን አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ጉብኝት ባደረገችባቸው የኢንዱስትሪ መንደሮች እና ግዙፍ ፋብሪካዎች በኃይል እጥረት በርካታ ቀናትን ያለ ሥራ ማሳለፍ የተለመደ እንደሆነ መታዘብ ችላለች።

ከዚህ በኋላ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ላለመገንባት አቋም መያዙን ተከትሎ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡ በአምራች ዘርፉ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች እንደሚናገሩት፣ እየተገነቡ ከሚገኙ የኃይል ማመንጫዎች በፍጹም አቅም ወደ ሥራ የሚገቡ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን ለማንቀሳቀስ የሚችል አቅም ለማግኘት ችግር እንደሚሆን ጠቁመዋል። አክለውም ኢትዮጵያ ከኃይል አቅርቦት ጋር ያልተጣጣመ እና አምራችም ሆነ ሌሎች ዘርፎች ላይ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ከመደረጉ በፊት የኃይል አቅርቦት እንዲሟላ መደረግ ይኖርበታል ሲሉ ይናገራሉ።

አስተያየት ሰጪዎቹ ጨምረውም ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ባለፈ የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ላይ ለማልማት ሲመጡ የሚያጋጥማቸውን የኃይል እጥረት ለመፍታት አስቀድሞ ዝግጅት ሳይደረግ ግድቦችን መገንባት ማቆም ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን እንደሚጠራጠሩ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ከታዳሽ ኃይል እና ከውሃ የሚገኘው የኃይል አቅም ከ45 ጊጋ ዋት እስከ 50 ጊጋ ዋት ድረስ እንደሚደርስ የታወቀ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 ከ2300 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳልነበራት ታውቋል። ከሚመረተው የኃይል አቅም ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው ከውሃ የሚመነጭ ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ ከታዳሽ ኃይል መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here