የማይነጥፉ የሚመስሉ እምባዎች

0
812

ስፍራው የካ ክፍለ ከተማ አዲስ አበባ ሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ ልዩ ስሙ ኮተቤ መሳለሚያ አካባቢ። አዲስ ማለዳ በአንዲት አነስተኛ ጊቢ ውስጥ በወጉ መራራቅ እንኳን በማይቻልበት እና ከሰሞኑ በጥቂትም ቢሆን ሲያካፋ በነበረው ሰማይ የተነሳ ከፊል አረንጓዴ መልበስ የጀመረ ምስኪን ጊቢ ውስጥ ተገኝታለች።

ጊቢው ውስጥ በእርግጥ ዘልቆ ገብቶ ዙሪያ ገባውን ለጎበኘ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው አልፎ ለሚሔደው ሁሉ በዛ አነስተኛ ጊቢ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ጓዳ መገመት የሚያዳግተው ጉዳይ አይደለም። በዚህ አነስተኛ ጊቢ የተገኘነው የለጋ ዕድሜዋን ሩጫ በአንድ ግለሰብ የተነጠቅ አንዲት ታዳጊ ባለታሪካችንን ቢቻል ከራሷ አንደበት ካልሆነ ግን ከወላጆቿ ስለ ተፈጠረው ሁኔታ ለመታዘብ ነበር።

ባለታሪካችን ጽናት (ስሟ የተቀየረ) የ11 ዓመት ታዳጊ እና የ5ኛ ክፍል ተማሪ ናት። ከመኖሪያ ቤቷ እምብዛም በማይርቀው የመንግስት ትምህርት ቤት የምትማረው ጽናት ነገን በልጆቻቸው ተስፋ ባደረጉ እንጂ ሞልቶ ባልተረፋቸው የወላጆቿ የዕጅ ወደ አፍ ኑሮ የምትኖር፤ የቤተሰቡ ሦስተኛ ልጅ እና ትንታግ ተማሪ እንደሆነች ከአራተኛ ወደ አምስተኛ ክፍል የተዛወረችበት የኹለተኝነት ደረጃ መስካሪ ነው።

እዚህ ግባ የማይባል ቤተሰቡን ኑሮ እጅግ ወደ ባሰ አስከፊነት ለወጠው በዓለም አቀፍ በቅርቡ ደግሞ በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽ ለጽናት እና ለቤተሰቦቿ ማዕድ ከማጉደል ባለፈ ሌላ ተጨማሪ ሰቆቃም ይዞባቸው መጥቷል። ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ ወረርሽኙ በኢትዮጵያ እግሩን ካስገባበት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ጀምሮ በመንግስት ትዕዛዝ በኢትዮጵያ የትኛውም ክልል ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመማመር ማስተማር ሒደቱን እንዲያቋርጡ መደረጉ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ታዲያ ቤተ ውስጥ መዋል ጀመረችው ጽናት የመጀመሪያዎቹ ኹለት እና ሦስት ሳምንታት ከእኩዮቿ ጋር ሰፈር ውስጥ ስትሯሯጥ እንዲሁም ከታታላቆቿ ጋር የባጥ ቆጡን ስታወራ ቀኑ ይመሻል።

የጽናት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ታዲያ በለጋ ዕድሜዋ እና የሩጫ ዘመኗ አንድ ትልቅ ጋሬጣ እንደተተከለበት በልጅ አእምሮዋ ትረዳዋለች ወይም ደግሞ ደመ ነብሷ ይነግራታል። ወላጆቿ ከተጣበበው ጊቢያቸው (ምናልባትም ለጊቢው ጥበት መንስኤም ሊሆን ይችላል) አንድ ጥግ ላይ ከመውደቅ መለስ ያለች ክፍል ሰርተው ለኑሯቸው መደጎሚያ የሚሆን ኪራይ የሚያገኙበት አንድ በ30 ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ያለ ወንደላጤ መምህር አከራይተዋል። ይህ ግለሰብ ታዲያ በተደጋጋሚ ጽናትን አሳቻ ሰኣት አድብቶ በመያዝ ያልተገባ ስፍራዎች ላይ ይነካት እንደነበር እና ጽናትም በልጅ አዕምሮዋ እና በለጋ ልቧ ፍራቻ እና ጥላቻ ለዚህ ግለሰብ ማሳደር ጀምራለች። ግለሰቡን ስታይ ከርቀት በሩጫ ማምለጥ፣ ጊቢ ውስጥ በድነገት ስትመለከተው የምትገባበት መጥፋት እና አንዳንዴም ከወላጆቿ ወደ ተከራይ ቤት መልዕክት እንድታደርስ ስትታዘዝ በእምቢተኝነት መመለስ በእርግጥ የጽናት ተግባራት ነበሩ።

ቀኖች ቀንን እየተኩ ነጉደው በአንድ ጎደሎ ቀን ግን ግለሰቡ ከውጭ ቆይቶ ወደ ቤቱ በሚገባበት ወቅት ጽናት እና ታላቅ እህቷን በቤት ውስጥ መኖራቸውን ያስተውላል። በዚህ ጊዜ ታዲያ በፍጥነት ወደ ተከራየው መኖሪያ ቤት በመግባት በልብስ የተሞላ ላስቲክ ይዞ ወደ አከራዮቹ ቤት በመምጣት ለጽናት እህት የሚሰራው ስራ ስላለው በአቅራቢያቸው ወዳለው ልብስ ሰፊ ጋር በመሔድ የታጠቡ ልብሶቹን እንድታስተኩስለት ይልካታል። በዚህ ወቅት ታዲያ ጽናትን በግላጭ ያለ ገላጋይ ያገኘው መምህር፤ ቢወልዳት እሷን ምናልባትም ታላቅ የ13 ዓመት ዕድሜ ያላትን እህቷን ያደርሳል። ገና ሩጣ ያልጠገበችውን፣ አጥንቷ ያልጠነከረ ታዳጊን ታዲያ በጠንካራ ጥፊ ራሷን እንድትስት ካደረገ በኋላ ለእንስሳዊ ፍላጎቱ የወሲብ ማርኪያ አደረጋት።

ከደረሰባት አቅል የሚያስት ጥፊ እና መደፈር ጉዳት ጋር ተደማምሮ ረጅም ሰዓት ራሷን ስታ ቆየችው ጽናት ታላቅ እህቷ ከተላከችበት ስትመለስ በደም አበላ ተውጣ መሬት ላይ ተዘርራ ታገኛታለች። በድንጋጤ ጩኸቷን ያሰማችው የጽናት እህት በጎረቤቶች እርዳታ ወደ ሕክምና ተቋም ተወስዳ ክሊኒክ አልጋ ላይ ራሷን ማወቅ ጀመረች የሆነችውንም በጭንቀት፣ ድንጋጤ እና ሕመም ውስጥ ሆና በድንገት ተጠርተው እየተጣደፉ የሕክምና ተቋሙ ውስጥ ለተገኙት እናቷ አጫወተቻቸው። ነገር ግን ጽናት መናገር የቻለችው በተከራዩ ሰው ከፍተኛ የሆነ ድብደባ እንደደረሰባት እንጂ የመደፈሯን ግን መናገር አልቻለችም። ይሁን እንጂ በጤና ባለሙያዎች ዘንድ ግልጽ ምልክቶች በማየታቸው በምርመራ መደፈሯን ለቤተሰቦቿ አረዷቸው።

ይህ የጽናት ታሪክ ታዲያ የባለ ታሪካችንን ታዳጊዋን ሕይወት በከባዱ ጥላሸት የቀባ እና አንገቷን የሚያስደፋ ጉዳይ ነው። አዲስ ማለዳ በባለ ታሪካችን ቤት በተገኘችበት ወቅት ጽናት ከእናቷ ጋር እኛን ለማናገር ወደ ውጭ ስትወጣ ከአደጋው በኋላ ማለትም ከወር ተኩል ገደማ መሆኑ ነው የመጀመሪያዋ ነው። በእርግጥ ጽናት ተጎድታለች፤ የልጅነት ለዛዋ እና የፊት ጸዳሏ ደብዛው ጠፍቷል፣ የልቧ ስብራት ከውስጧ አልፎ ገጽታዋ ላይ በጉልህ ተጽፎ ይነበባል።

በእናቷ ጉያ ተቀምጣ ከበዛው እና ድምጽ አልባው እምባዋ ጋር እየታገለች በተወሰኑ ደቂቃዎች ውስጥ አንድ ቃል ትወረውርና ተጨማሪ ጥያቄ ለመጠየቅ ስንሞክር በዛው ቅጽበት ድንጋጤ ውስጥ ገብታ ዝም ትላለች። እምባዋ ግን አሁንም ይፈሳል፣ መቼም ማቆሚያ ያለው አይመስልም፤ ጉዳዩን በሕግ የተያዘ ቢሆንም ቅሉ ጉዳት አድርሷል ተባለው ግለሰብ ግን ከዛን ቀን በኋላ ጨርቄን ማቄን ሳይል ከተሰወረ እና ፖሊስም ግለሰቡን ማደን ከጀመረ ዋል አደር ብሏል ግን አሁንም ውሃ ሽታ እንደሆነ ነው።

‹‹ልጄን ቅስሟን እንደሰበረው የረገጠው ኹሉ ይጨልም፤ እኔ ፈጣሪን አምናለሁ ልጄን እንዲህ በቁሟ የገደላትን ሰው እንደሚበቀልልኝ አልጠራጠርም›› የሚሉት የጽናት ወላጅ እናት ከልጃቸው ባልተናነሰ የእርሳቸውም እምባ ገብተን እስክንወጣ ድረስ አላቆመም ነበር። ወላጅ እና ለአዲስ ማለዳ መረጃዎችን በሚሰጡበት ወቅት ጽናት በጥልቅ ትካዜ ውስጥ ትሆንና እንደመባነን ብላ እንደገና ወደ ነባራዊ ሁኔታው ትመለሳለች። እጅግ ልብን በሚሰብር እና ታዳጊዋ ባለችበት የእድሜ እርከን ልትቋቋመው የማትችለው አይነት ሕመም እንደሚሰማት በራሷ አንደበት ለአዲስ ማለዳ ትናገራለች። ”በትክክል መቀመጥ እና ወደ መጸዳጃ ቤት መሔድ ይጨንቀኛል ምክንያቱም ከፍተኛ የሆነ ሕመም ስለሚሰማኝ›› ስትል በለሆሳስ ትናገራለች።

እንቅልፍ ለመተኛት እንደምትቸገር እና ብትተኛ እንኳን የተረጋጋ እንቅልፍ እንደማትተኛ ወላጅ እናቷ ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።
የጽናትን ታሪክ እንደ ማሳያ አነሳን እንጂ በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ኃላፊ አልማዝ አብረሐም በዋልታ ቴሌቪዝን ቀርበው እንደተናገሩት ኮቪድ 19 መከሰት በኋላ ባሉት ኹለት ወራት ውስጥ ከአንድ መቶ በላይ ሴቶች እና ወንድ ሕጻናት በወላጅ አባቶቻቸው ሳይቀር መደፈራቸውን ይፋ አድርገዋል። በዚህ አጭር ጊዜ ይህን ያህል ሰፊ ቁጥር በተለይም ደግሞ በአዲስ አበባ ብቻ መሆኑ የጉዳዩን ጥልቅነት እና ስር መስደዱን የሚያመላክት እንደሆነ በርካቶች ሲወያዩበት መሰንበቱ ይታወሳል። በተለይ ደግሞ ባመኗቸው እና ልባቸውን በጣሉባቸው በአሳዳጊዎችም ሆነ በወላጆቻቸው መደፈራቸው ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል።

ከአዲስ አበባ በተጨማሪም በክልሎች በተለይም ደግሞ በአማራ ብሄራወ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ከመዘጋቱ ጋር ተያይዞ ከ2መቶ 80 በላይ ሴት ሕጻናት ያለ እድሜያቸው እንዲዳሩ መደረጉን ሪፖርቶች አመላክተዋል። በዚሁ ክልል አስገድዶ መድፈርም በተጓዳኝ ከፍተኛ የሆነ ደረጃ ላይ ደርሷል።

በእንጀራ ልጁ ላይ አስገድዶ መድፈር የፈጸመው የምዕራብ ጎንደር ነዋሪ የሆነ የ60 ዓመት ግለሰብን ማንሳት ይቻላል።ወንጀሉ የተፈጸመው በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ ሲሆን ጥር 21/2012 ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ ተከሳሽ ሰረበ ተገኘ አባቴ ብላ አምና ከጎኑ የሆነችውን የ13 አመት የእንጀራ ልጁን በሽጉጥ በማስፈራራት አስገድዶ እንደደፈራት የክስ ዝርዝሩ ያስረዳል። ተጠርጣሪውም ለጊዜው ቢሰወርም በዳንሸ ከተማ መያዙም ተገልጿል። የሶሮቃ ንዑስ ወረዳ ፖሊስ ምርመራውን አጣርቶ ጉዳዩን ለዓቃቤ ህግ ያስተላለፈ ሲሆን

ዓቃቤ ህግም የተላለፈውን የወንጀል ህግ በመጥቀስ እና ግለሰቡ በማስፈራራት እና ጉዳት ደረሰባትን ታዳጊ ዕደሜ መጠን ከግምት ውስጥ ባመስገባት ክስ መመስረቱንም ለማወቅ ተችሏል ። ክሱን የተመለከተው የሶሮቃ ንዑስ ወረዳ ፍርድ ቤት ተከሳሽን ጥፋተኛ በማለት ተከሳሽ እንዲከለከል ፍርድ ቤቱ ቢፈቅድም መከላከያ ማስረጃ ሊያቀርብ አልቻለም ። ፍርድ ቤቱ የድርጊቱን አስነዋሪነት በመግለፅ ጥፋተኛነቱን በማሳየት የዓቃቤ ህግን አንድ ማክበጃ በመቀበል ተከሳሽ የ8 ልጆች አባት በመሆኑና ከአሁን በፊት ሪከርድ ባለመኖሩ ኹለት ማቅለያዎችን ፍርድ ቤቱ መያዙ ተገልጿል ። ወንጀሉ እሱንም ሆነ ሌሎችን ያስተምራል በሚል ተከሳሽ እጁ ከተያዘበት ጀምሮ የሚታሰብ ግንቦት 21/2012 በዋለው የወንጀል ችሎት በ11 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ እንደወሰነበት የጠገዴ ወረዳ ኮሙንኬሽን አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here