ሲሚንቶ አከፋፋዮች ከዋናው ሲሚንቶ አምራቾች በተገቢው መንገድ ቀጥታ ሲሚንቶ መረከብ ባለመቻላችን የደላሎች መጠቀሚያ ሆነናል ሲሉ ቅሬታቸውን አሰሙ።
ቁጥራቸው የበዛ አከፋፋዮች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም የቅብብል ስርአቱ የተስተካከለ ባለመሆኑ እና አከፋፋዮች ከዋና አምራቾች፤ ለምሳሌ ደርባ ፣መሰቦ ፣ ዳንጎቴ ከመሳሰሉት አምራች ድርጅቶች በቀጥታ መቀበል ባለመቻላችን ከትርፍ ይልቅ ለከባድ ኪሳራ እየተዳረግን ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ከዛም በተጨማሪ አከፋፋዮቹ እንደ ዋና ችግር የሚያነሱት እራሳቸው ከዋና አምራቾች ጋር ተነጋግረው እና ክፍያም ፈፅመው ነገር ግን ሲሚንቶውን በተገቢው ሰአት ሳይደርስላቸው ከ 9ወር አስከ 15 ወር ድረስ እንደሚቆይባቸው ተናግረዋል፡፡
ይህ በሚሆንበት ሰዓት ደግሞ ሲሚንቶው ደላሎች እጅ እንደሚገባ እና በጊዜው ለኛ ባለመድረሱ ምክንያት እኛም ደላሎች በሚያወጡት ዋጋ ከእነርሱ እንድንጠቀም እና በዛም የሲሚንቶው ዋጋ መናር እንደሚታይበት ተናግረዋል፡፡ በዛም ከደላሎች እየተረከቡ ያሉት 1 ኩንታል ሲሚንቶ በ 440 ብር ሲሆን ለማከፋፈል ደግሞ እስከ 460 እንደሚሆን ተናግረዋል ፡፡
በዚህም አዲስ ማለዳ መገናኛ አካባቢ በመገኘት ባደረገችው ማጣራት እና በስፍራው የሚገኙትን ዋና አከፋፋዮች ባነጋገረችበት ወቅት ተጠቃሚው ህብረተሰብ ጋር ሲደርስ ካለ መጠን እንደሚወደድ እና ለዚህም ዋና ምክንያት ደግሞ መንግስት ከዋና አምራቾች ጋር እኛ ብቻ እየተጋናኘን እንድናከፋፍል ጣልቃ ባለመግባቱ ነው ብለዋል፡፡
ዋናው ያመጣው ተፅዕኖው እንደሚሉት አከፋፋዮቹ የሲሚንቶ ዋጋ በመጨመሩ ለኪሳራ እየተዳረግን ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የንግድ እና ኢንዱስትሪ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሆኑት ወንድሙ ፍላቴ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በቀጣይ ሲሚንቶ ከዋናው አምራቾች በመረከብ በመንግስት የልማት ድርጅቶች በኩል ብቻ እንዲስራጭ ያስፈለገበት ምክንያት ተብለው የሚነሱትም የሲሚንቶ ምርት በግብአትነት ጥቅም ላይ የሚውልባቸው የልማት ዘርፎች በመኖራቸው እና በአግባቡም እንዲዳረስ በማሰብ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
በዋነኛነት ደግሞ የመንግስት ፕሮጀግቶች ሲሆኑ ለምሳሌ እንደ አባይ ግድብ የመሳሰሉ ታላላቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች አሉ፤ ሌሎች የኮንስትራክሽን ዘርፉ አለ እና በግል ባለ ሃብቱ የሚለማ፤ እነዚህ ሁሉ ተጠቃሚዎች እያሉ ዋጋው ካለ አግባብ እየጨመረ በመምታጣቱ ነው ይህ ውሳኔ መተላለፍ ያስፈለገው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል፡፡
ወንድሙ እንደሚሉት ከአምራች ፋብሪካዎች 1 ኩንታል ሲሚንቶው ሲወጣ ከ228 ብር አስከ 258 ብር ነው ያሉት ኃላፊው በዚህም በህገወጥ ደላሎች የገበያ ሰንሰለት ውስጥ ገብቶ ደግሞ አከፋፋዮች ጋር 440 ብር አስከ 460 ብር ይደርስና ተጠቃሚው ጋር ሲደርስ አስከ 600 ብር እየተሸጠ መሆኑ ከባድ አድርጎታል ብለዋል፡፡ ነገር ግን ምንም አይነት የደላሎች መስመር ባይኖር አንድ ኩንታል ተወደደ ቢባል ከ 320 አስከ 350 ቢሄድ ነው ብለዋል፡፡
ወንድሙ ጨምረውም እስካሁን ባለው ተጠቃሚ የሆኑት አምራቾች ሳይሁኑ ህገወጥ ደላሎች መሆናቸውን ገልጸው ፤ አሁን ያለውን ያለ አግባብ ዋጋ ጭማሪ ችግርም ለመቅረፍ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል የተላለፈው ውሳኔ ዋና መንገድ ነው ተብሎ መታሰቡንም ተናግረዋል፡፡
ነግር ግን ይላሉ ወንድሙ ይሄ ሲባል ህጋዊ ነጋዴዎችን ጉዳት ላይ አይጥልም ‹‹ በህጋዊ መንገድ ከአምራቾች ተረክበው አግባብ ባለው ዋጋ ለቸርቻሪ ነጋዴዎች የሚሸጡ እንዳሉ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ዝረዝር አፈፃፀም ሲወጣ እና ወደ ትግበራ ሲገባ የሚወሰኑ ውሳኔዎችም ሊኖሩ ይችላሉ ሲሉ ወንድሙ ፍላቴ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 83 ግንቦት 29 2012



