የአዲስ አበባ አስተዳደር በልማት ምክንያት አርሶ አደር አላፈናቅልም አለ

0
499

አዲስ አበባን ከዚህ በኋላ ወደ ጎን የማስፋት ዕቅድ እንደሌለው ያሳወቀው የከተማ አስተዳደሩ በልማት ምክንያት አንድም አርሶ አደር እንደማያፈናቅል አሳወቀ። በጣም ዝቅተኛ ካሣ የወሰዱና በከፋ ችግር ውስጥ የሚኖሩ የልማት ተነሽዎችን ካሣ ሊከልስ እንደሚችልም ጠቁሟል።
የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪተሪ ፌቨን ተሾመ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከተማዋ ከዚህ በኋላ ወደ ላይ እንጂ ወደ ጎን የመስፋት ዕቅድ የላትም። በመሆኑም በቤት ልማት ሥም የሚፈናቀል አንድም አርሶ አደር አይኖርም ነው ያሉት። ‹‹ልማት እንዲህ ከሆነ ይቅር›› በሚያሰኝ ደረጃ አርሶ አደሮችም ሆኑ ከመሐል ከተማዋ በመልሶ ማልማት የተነሱ ነዋሪዎች ላይ የተለያዩ ጉዳቶች መድረሳቸውን ያነሱት ፌቨን ከዚህ በኋላ ነዋሪ የነበረው እየተጎዳ የሚካሄድ ልማት እንደማይኖርም አንስተዋል።
‹‹ከካሣ ጋር ተያይዞ ተመልሶ የሚታይበት ሁኔታ ይኖራል›› ያሉት የሥራ ኃላፊዋ አንዳንዶች እስካሁንም ካሣ እንዳልተከፈላቸው ጠቁመዋል። የተከፈላቸውን በተመለከተም በጣም አናሳ ነበር ወይ የሚለው ጥናት እየተካሄደበት ስለመሆኑ አክለዋል። ይሁንና ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ለተነሱት ሁሉ ወደ ኋላ ተመልሶ ካሣ የመክፈል ሂደት እንደማይኖር አስገንዝበው በቅርብ የተነሱና በጣም አነስተኛ ካሳ ተከፍሏቸው በችግር ውስጥ የሚገኙትን የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች ሕይወት ለመደጎም ካሣ እንደአዲስ የሚከለስበት ውሳኔ ጥናቱ ሲጠናቀቅ ሊከተል እንደሚችል ጠቁመዋል።
በ2004 በተለይም ኮዬ ፈጬ አካባቢ ለሚገነቡ ቤቶች ለእርሻ ማሳቸውና ለመኖሪያ ቤታቸው ካሣ ተከፍሏቸው የቤት መስሪያ ምትክ ወደተሰጣቸው አካባቢ የሔዱ አርሶ አደሮች ቢኖሩም፣ እስካሁንም በማሳቸው ላይ ግንባታ ያልተጀመረባቸው አርሶ አደሮች ካሣ የተቀበሉበትን ማሳ እያረሱ እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ በሥፍራው ባደረገችው ቅኝት አረጋግጣለች። በተጨማሪም ከሰባት ዓመት በፊት ለእርሻቸው ካሣ ቢወስዱም ለመኖሪያ ቤታቸው ስላልተከፈላቸውና ምትክ ቦታ ስላላገኙ እስካሁን ያልተነሱ አርሶ አደሮች አሉ። ስለእነዚህ አርሶ አደሮች ዕጣ ፈንታ የጠየቅናቸው ፌቨን ከዚህ በኋላ ካሉበት እንደማይነሱ ጠቅሰዋል። ይሁንና ካሣ ወስደው አለመነሳታቸው ቀድመው በተወሰኑት አርሶ አደሮች በኩል ‹‹እኛስ›› የሚል ሌላ ጥያቄ አያስነሳም ወይ ለሚለው ምላሽ የሰጡን ፕሬስ ሴክሪታሪዋ አሁን ያሉበት ቦታ ከአካባቢው ጋር ካልተስማማ ምትክ ተሰጥቷቸው ይነሱ ይሆናል እንጂ ከዚህ ቀደም ባለው መንገድ አይፈናቀሉም ብለዋል።
በኮዬ አካባቢ ኮንዶሚኒየም ቤት በደረሳቸው ነዋሪዎች ቀድመው ከተፈናቀሉት አርሶ አደሮች ጋር የጸጥታ ሥጋት ስለመኖሩ አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ መረጃ አግኝታለች። ስጋቱም ‹እኛ እያለን አንድ ሰው ወደዚህ ኮንዶሚኒየም አይገባትም› የሚል መሆኑም ተጠቅሷል። አዲስ ማለዳ ላቀረበችው ጥያቄ ፌቨን ሲመልሱ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው ተብሎ መብራትና ውኃ ሳያገኙ የሚኖሩ እንዳሉ በመጥቀስ ሥጋቱ ሊኖር ይችላል ብለዋል። አስተዳደሩም ቀድመው ለልማት የተነሱትን ወገኖች ሕይወት ለማሻሻል እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አሁን ያለው አመራር እጅግ በተወሳሰበ ጊዜ ወደ ሥልጣን መምጣቱን የሚናገሩት ፌቨን የሚከተለው አካሄድም በልማት ሥም የተጎዱትን እንዴት ኑሯቸውን ማሻሻል እንደሚቻል ነው። ለዚህም አጋዥ ይሆናል የተባለው ‹‹የከተማ ግብርናና አርሶ አደር ልማት ቢሮ›› በታኅሣሥ መጨረሻ በከተማው ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል። ዓላማውም በልማት የተነሱ አርሶ አደሮችን ከዚህ ቀደም ይዘውት ከነበረው ሠፋፊ እርሻ ይልቅ ባለው ትንሽ ማሳ ላይ እንዴት በግብርና መለወጥ እንደሚቻል ሥልጠና እየሰጡ ወደ ሥራ ማስገባት ነው ተብሏል።
ለዚህም ቢሮው በቂ በጀት ተይዞለታል የተባለ ሲሆን የሌሎች አገራት ተመሳሳይ ተቋማት ከተሞቻውን የሚመግቡበት ዘዴ በመሆኑ በአዲስ አበባም ይህንኑ ለመተግበር ታቅዷል። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደመም ከተማዋ የከተማ ግብርናን አደራጅታ እንደቆየች በመጥቀስ ምን የተለየ ነገር ያመጣል ለሚለው በተደራጀ መንገድ አለመሥራቱን የሚጠቅሱት ፌቨን በአዲስ የሚዋቀረው ቢሮ የልማት ተነሽ አርሶ አደሮቹን ቅሬታና ጥያቄ ለመፍታት በሚያስችል አኳኋን እንደሚደራጅም አንስተዋል።
ከመሐል አዲስ አበባ በመልሶ ማልማት የሚፈናቀሉና ወደ ከተማዋ ዳርቻ የሚሔዱ ተነሽዎችም በተመሳሳይ ስለመጎዳታቸው ያነሱት የሥራ ኃላፊዋ ከዚህ በኋላ እንደማይደገም ጠቅሰዋል። በለገሃር አካባቢ በአረብ ኢሚሬቶች ትብብር ይገነባል የተባለው የ50 ቢሊየን ብር የከተማ መንደር ግንባታ ፕሮጀክት አሁን በሥፍራው የሚኖሩ አንድ ሺህ 600 አባወራዎችን እንዳይፈናቀሉ አድርጎ የሚገነባ መሆኑም ማሳያ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here