የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በአስር ወራት 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱን ገለጸ

0
897

በጀት ዓመቱ አስር ወራት ከወጪ ንግድ ሶስት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ በአፈፃፀም የተመዘገበው 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር መሆኑን በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወንደሙ ፍላቴ ገለጹ፡፡
ይህ አፈፃፀም በ2011 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ከተገኘው 2.15 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ12.6 በመቶ (271 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር) ብልጫ ማስመዝገቡን ተገልጿል፡፡
በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ከተያዘላቸው ዕቅድ በላይ አፈጻጸም ያስመዘገቡት አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጫት ሲሆኑ ከተያዘላቸው ዕቅድ ከ50 በመቶ እስከ 99 በመቶ ክንውን ያስመዘገቡ ምርቶች እንደቅደም ተከተላቸው ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ ስጋ፣ ቅመማ ቅመም እና ወርቅ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከተያዘው ዕቅድ አንጻር በውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ50 በመቶ በታች ዝቅተኛ ገቢ ያስመዘገቡ የወጪ ንግድ ምርቶች ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እና የቁም እንሰሳት መሆናቸውን አስታውሰው፡፡
አጠቃላይ የወጪ ንግድ ምርቶች ከአምናው ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በገቢ ቡና 16 በመቶ፣ አበባ 9 በመቶ፣ የቅባት እህሎች 10 በመቶ ፣ ጫት 7 በመቶ ፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት 22 በመቶ፣ ወርቅ 144 በመቶ ፣ የቁም እንሰሳት 22 በመቶ እና አትክልትና ፍራፍሬ 46 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በዋናነት የወጪ ንግድ ጭማሪ ያሣየበት ምክንያት የምርት ትንተናና የክምችት ክትትል በማድረግ በተገባው የኮንትራት ውል መሰረት እንዲላክ ድጋፍ ማድረግ፣ በህገ- ወጥ መንገድ በክምችት የተያዙ ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዲገቡ መደረጉ፣ አንዳንድ ከተሞች ከፍተኛ ህገ- ወጥ የምርት ክምችት መኖሩን በድንገተኛ ቆጠራና ክትትል በማድረግ ህጋዊ እርምጃ እተወሰደ መሆኑና በተለይም ከጉሙሩክ ኮሚሽንና ከክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮዎች ጋር በመቀኛጀት የኮንትሮባንድ ቁጥጥር እና ህገ-ወጥ ንግድ ማጠናከር በመቻሉ እንደሆነ አቶ ወንደሙ አስረድተዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here