ዘረኝነትና ታላቁ የፊልም ኢንዱስትሪ

0
1273

የአንድ ጥቁር አሜሪካዊ በአሰቃቂ ሁኔታ በፖሊሶች እጅ መገደል የዘረኝነትን ጉዳይ ዓለማቀፍ አጀንዳ አድርጎታል። የጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ሞት፣ የአንድ ሰው ብቻ ሳይሆን የብዙዎች እስኪመስል ድረስ፣ ዓለምን በአንድ ቋንቋ አነጋግሯል። ‹Balck lives Matter› በግርድፉ ሲተረጎም ‹የጥቁር ሕይወት ዋጋ አለው!› ከሁሉም አንደበት የሚወጣ ቃል ሆኗል።

እድሜ እየጨመረና በቀናት መካከል እየተሻገረ የሚገኘው የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የዓለምን ሕዝብ ሁሉ የማኅበራዊ ድረ ገጽ ቤተኛ በማድረጉ፣ በአሜሪካ የተከሰተው የአንድ ሰው ሞት ዓለምን ሁሉ ከዘረኝነት ቀስቅሷል። ቆዳዋን አሳምራ ችግሯን በምጣኔ ሀብት፣ በሥልጣኔ እና በእድገት የሸፋፈነችው አሜሪካም የጓዳዋ ምስጢር፣ የጥቁር አሜሪካውያን ጨምሮ የእስያ፣ የላቲንና የአረብ እንዲሁም ሌሎች ዜጎቿ ፈተና በአንድ ግለሰብ ሞት አደባባይ ተሰጥቷል።

ማኅበራዊ፣ የጤና፣ የምጣኔ ሀብትና፣ የጥበብ፣ የፖለቲካ፣ ሁሉም ጉዳይ ላይ ዘረኝነት ይኖር እንደሆነ ተጠየቀ፣ ተገኘም። በአዲስ ማለዳም ከጥበቡ መስክ በፊልሙ ዓለምስ ምን ተባለ የሚለውን ለመዳሰስ ሞክራለች። በዓለማችን ዝነኛና ስኬታማ ከሆኑ የፊልም ኢንዱስትሪዎች መካከል የአሜሪካው ሆሊውድ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው።

ሆሊውድ ዘረኛ ነው ወይ?
ጥቁር አሜሪካዊ ተዋናይ ክሪስ ሮክ በ2016 የኦስካር ሽልማትን የመክፈቻ ንግግር አድርጎ ነበር። በዛ ዓመት እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑ ጥቁር አሜሪካውያን ነበሩና ለሽልማት የታጩት፣ ነገሩን አንስቶ በጉዳይ ላይ ሐሳቡን ለመስጠት ሞክሯል። እንዲህም አለ፤ ‹‹ሆሊውድ ዘረኝነት ይታይበታል ወይ? አዎን ጥርጥር የለውም። ግን በሆሊውድ ያለው ዘረኝነት በአደባባይ እንደሚታየው ዓይነት አይደለም። የራሱ የሆነ መንገድ አለው››

የፊልምን ጥበብ ጨምሮ ማንኛውም የኪነጥበብ ዘርፍ ዓለማቀፋዊ እንዲሆን ይጠበቃል፤ በባህሪውም እንደዛ እንደሆነ ይታመናል። ያም የሚሆነው የሰዎች ታሪክ ስለሚነገርበት ነው። ለዛም ነው የፊልሞች መቼት የትም ይሁን መቼ፣ በማንኛውም ቦታ በእኩል ስሜት የሚታዩት። ታድያ በፊልም ሥራ ላይ እንዲሁም በፊልም ታሪኮች ላይ ከዘረኝነት ጋር የተያያዘ እንከን ይገኛል ብሎ መገመት ከባድ ነው። ነገር ግን አለ።

በፊልም ዓለም ዘረኝነት በሦስት አንጻር ሊታይ ይችላል ሲሉ የፊልም ተንታኞች ያስረዳሉ። አንደኛው የተዋናይ መረጣ ጉዳይ ነው። ሌላው የፊልሙ አዘጋጆች ሲሆኑ ሦስተኛ በፊልሙ ላይ ሰዎች የተወከሉት መንገድ ነው።

ሆሊውድና ዘረኝነት
የጀርመኑ ዶቼቬሌ (Dw) በጉዳዩ ላይ መጠነኛ ዳሰሳ አድርጓል። ለዚህም ከ1928 ጀምሮ ለኦስካር ሽልማት የታጩ ፊልሞችን ቃኝቷል። በዚህም መሠረት ታድያ ጥቁሮችና እስያውያን በከፍተኛ ደረጃ የዘረኝነት ሰለባ መሆናቸው ተጠቅሷል። በጊዜው የሚሠሩ የካርቱን ሥዕሎችም ይህንን የሚያመላክቱ ነበሩ።

ይህ ታድያ የቆዳ ቀለማቸው ጥቁር የሆነ ሰዎች ብቻ ሳይሆን እስያውያንም የዘረኝነትና መገለል ሰለባ ናቸው። የማኅበራዊ ዘርፍ ጥናት ባለሞያዋ ናንሲ ዋንግ ዩን በጉዳዩ ላይ አንድ መጽሐፍ ለንባብ አብቅታለች። በመጽሐፉም እንደጠቀሰችው በቀድሞ ጊዜ የሆሊውድ ፊልሞች የእስያ ሰዎችን አስቂኝና ግራ የተጋቡ ሰዎች አድርገው ሲስሉ፣ ይህንንም ገጸ ባሕሪ የሚጫወቱት ነጭ ተዋንያን በገጽ ቅብ ጥበብ ፊታቸውን በቢጫ ቀለም አድምቀው ነው።

በፊልሙ ዘርፍ እስያውያን ያለፉበትን መንገድ የምታስረዳው ናንሲ፣ እስያውያን በዘርፉ ለሥራ እንደማይቀጠሩም ጠቅሳለች። ይልቁንም በፊልሞች ውስጥ አንዳች እስያዊ ገጸ ባህሪ የሚኖር ከሆነ፣ ነጮች በተለያየ የገጽ ቅብ መልካቸውን በመለወጥ ነበር የሚተውኑት።

እያደር ግን የተወሰኑ ለውጦች መታየት ሲጀምሩ፣ በ1970/80ዎቹ እነ ብሩስ ሊ ወደ ፊልም ኢንዱስትሪው ተቀላቀሉ፣ ቀጥሎም ጄት ሊ፣ ጄኪ ቻን እና የመሳሰሉ ተዋንያን ቀጠሉ። አብሮም ‹ማርሻል አርት› ሲተዋወቅ፣ እስያውያንን ሁሉ ከዚህ የማርሻል አርት ጋር ማገናኘትና ሁሉም እስያውያን የማርሻል አርትን እንደሚያውቁ ይታሰብ ጀመር።

ዶቼቬሌ በዚሁ ዘገባ ላይ ታድያ በካሊፎርኒያ የተደረገ አንድ ጥናትን አስቀምጧል። ጥናቱ እንደጠቀሰው ታድያ የሴቶችና ነጭ ያልሆኑ ተዋንያንም፣ የፊልም ገጸ ባህርያት ቁጥርም በጥቂቱ ጨምሯል። በዚህም መሠረት እስያውያን በአሜሪካ ሕዝብ ውስጥ 6 በመቶውን ሲይዙ፣ በ2017 እና 2018 በተሠሩ ፊልሞች ሦስት በመቶ ድርሻ አግኝተዋል። በተጓዳኝ ጥቁሮች ደግሞ 12.5 በመቶውን ይዘው ነበር። ይህም በፊልሞች ከታዩ ውክልናዎች ውስጥ ማለት ነው።

የጥቁሮች ድርሻ ከእስያውያን አንጻር ከፍተኛ ቢመስልም፣ ጉዳዩ ግን ተመሳሳይ ነው። እንደ ዶቼቬሌ ገለጻ። ነጮች ነበሩ የጥቁር ገጻባህሪን ሳይቀር ወክለው የሚተውኑት። ታድያ አሁን ላይ ይህ ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ የቀረ ቢሆንም፣ በአንጻሩ የጥቁሮች ገጸባህሪ አሳሳል ላይ ችግሮች ይታያሉ። በዚህም አሁን ድረስ ጥቁሮች ወንዶቹ አስፈሪና ቁጡ፣ ሴቶቹ ደግሞ ተናጋሪ (ለፍለፊ) እና ጯኺ ተደርገው ይሳላሉ። ጥቁር ገጸባህርያትም ከዋናው ቀጥሎ የሚገኙ ረዳት ሆነው እንጂ በመሪነት አያኖሩም። በፊልሙ ሞት የሚኖር ከሆነም ጥቁሩ ቀድሞ ይሞታል፣ ዘገባው ያትታል።

ምንም እንኳ እነዚህ ዘረኝነትና ማግለል የሚታይባቸው የዘርፉ ጉዳዮች በጥቁር አሜሪካውያን ላይ ብቻ ቢመስልም፣ ከዛም አልፎ አፍሪካም ይደርሳል። ታድያ የአፍሪካ ነገር በፊልሞች ላይ የሚነሳ ከሆነ፣ አፍሪካ አስፈሪና አደገኛ እንዲሁም ሥልጣኔ ድርሽ ያላለባት አኅጉር ተደርጋ ትሳላለች።

በተመሳሳይ የላቲን ገጸ ባህርያት አሳሳልም ላይ ችግር አለ። በአሜሪካ ፊልሞች ላይ የላቲን ገጸባህርያት ከጾዊ ግንኙነትና ከወሲብ ጋር በተገናኘ የሚሳሉ ናቸው። ላቲኖች በአሜሪካ ካለው ሕዝብ 18 በመቶውን የሚይዙ ሲሆኑ፣ በፊልሙ ኢንዱስትሪ ያላቸው ውክልና ሲታይ፣ በአውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2000 ጀምሮ በተሠሩ 2 ሺሕ 638 ፊልሞች ላይ ላቲኖች ወሲብ ቀስቃሽ ተደርገው ተስለዋል።

ይህ የሆሊውድ የማግለል ጉዳይ ጀርመኖችንም ይነካል። ጀርመኖች ሁሉ ናዚ ተደርገው ሲቆጠሩ፣ ከዛም ቀጥሎ ሳይንቲስቶች እንደሆኑ ተደርገው ይሳላሉ። ይህም የሆነው የናዚ ፓርቲ ጀርመንን ይመራ በነበረበት ዘመን ወደ አሜሪካ በተሰደዱ ጀርመናውያን ሳይንቲስቶች ምክንያት ነው። ከእነዚህም ውስጥ የጀርመኑ ተወላጅ አልበርት አንስታይን ተጠቃሽ ነው።

ሩስያውያን በተመሳሳይ የሚሳሉበት መንገድ ከመደበኛው ወጣ ያለና የተዛባ ነው። በሆሊውድ ፊልሞች ላይ ሩስያውያን በጦርነት አውድ ውስጥ ነው የሚታዩት። ገጸ ባህርያትም ብርቱ፣ ኮስታራና ሩስያውያን ባልሆኑ ሰዎች የሚሸወዱ ተደርገው ነው። ከባድ ሕይወት የሚመሩና ብዙ ጊዜ ጉዳት የሚደርስባቸውም እነዚህ የሩስያ ገጸባህርያት ናቸው። እነዚህም ብዙውን ጊዜ ሩስያዊ ባልሆኑ ሰዎች የሚተወኑ ናቸው።

በጥቅሉ ብዝኀነትን ከማሳየት አንጻር፣ የዓለም ሕዝብ ሁሉ መሰባሰቢያ የሆነች በምትመስለው በአሜሪካ የሚገኘው ሆሊውድ ተመስጋኝ አይደለም። ይሁንና ነገሩ አሁን ላይ ለውጥ እያሳየ ይመስላል። ዶቼዌሌ በድረገጹ እንደዘገበው፣ ቫዮላ ዴቪስ የተባለች ጥቁር ተዋናይት በዋና ገጸባሕሪነት የምትተውንበት ‹How to Get Away With Murder› የተሰኘው ተከታታይ ፊልም በ2015 ኤሚ የተባለውን የፊልም ሽልማት ሲቀበል፣ እንዲሁም በ2018 ‹Crazy Rich Asians› የተሰኘው ፊልም በርካታ እስያውያን ተዋንያንን ያሳተፈ ሆኖ፣ በቦክስ ኦፊስ ቀዳሚ ተርታ ላይ ሲቀመጥና መሰል ኹነቶች ሲከሰቱ፣ ለውጦች እንዳሉ ማሳያ ነው፤ እንደዘገባው።

የታገደው ፊልም
‹ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ› በአሜሪካ እርስ በእርስ ጦርነትን መቼት አድርጎ የተሠራ የፍቅር ፊልም ነው። ይህ በ1939 የተሠራ ሲልም በርካታ የኦስካር ሽልማቶችን የተቀበለ ሲሆን፣ አሁን የጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ ለዘረኝነት በነቁ ዐይኖችና ለውሳኔ በቀረቡ አሠራሮች፣ ከሚታይባቸው ድረገጾች ሁሉ እንዲወርድ ተደርጓል። ይኸው ፊልም ታድያ አስቀድሞም ጥቁሮችን የሳለበትን መንገድ መነሻ በማድረግ ብዙ ወቀሳ ሲያስተናግድ ነበር። ታማኝ ጥቁር ባሮችን ሲስል፣ ባርያ አሳዳሪዎችን ደግሞ ጀግና አድርጎ አስቀምጧልና።

በአንጻሩ ይህ ፊልም ከወጣበት ጊዜ አንጻር የነበረውን እውነት መነሻ ያደረገ ነው በማለት፣ አውዱንና ታካዊ ዳራውን በመመልከት፣ ምክክር ተደርጎበት ሊመለስ እንደሚችልም ተጠቅሷል።

ይህ ይነሳ እንጂ ‹The Birth of a Nation› የተሰኘና በ1915 የወጣው ፊልም በሆሊውድ ከተሠሩ ፊልሞች ሁሉ ዘረኝነት የሚታይበት ነው የሚሉ ሙግቶች እንደሚነሱ ይነገራል። በዚህ ፊልም ውስጥ በአሜሪካ ከነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ጥቁሮች የፖለቲካ ሥልጣን ማግኘታቸውን ተከትሎ፣ አስፈሪና ጨቃኝ ተደርገው የተሳሉበት ነው።

እንደተባለው ግን ለውጦች አሁን ላይ አሉ። ጥቁሮች የሚተውኑበት፣ ጥቁሮች በራሳቸው የመረጡትን ታሪክ የሚናገሩበት አውድ አለ። በፔንሲልቬንያ ዩኒቨርስቲ የፊልም መምህር እና የፊልም ታሪክ ተመራማሪ ዶናልድ ቦግሌ በጻፈው፣ ‹Hollywood Black: The Stars, The Films, The Filmmakers› የተሰኘ መጽሐፍ ይህን ጉዳይ በስፋት ከትቦታል። ለዚህም ‹Black Panther› የተሰኘውና በኹለት ዓመታት በፊት 2018/2010 የወጣው ፊልም ይጠቀሳል።

ብላክ ፓንተር የተሰኘው ፊልም ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር የሚገናኝ እንደሆነም ብዙዎች የተቀበሉት ሲሆን፣ ጥቁሮች በተሳተፉበት ፊልምነት ደግሞ አዲስ አብዮት የቀሰቀሰ ይመስላል። በዚህ ላይ ጥቁር የሆኑ የፊልም ተመልካቾች ግብረ መልስ ምን ይመስላል የሚለው ላይ ዶናልድ ለፊላዴልፊያ ኢንኳየረር ሲናገር፣ ተመልካቾች ፊልሙን አይተው ሲወጡ በገጻቸው ላይ ደስታ ይነበብ እንደነበር አንስቷል።

ይህም ደስታ የመጣው ጥቁር ጀግና ተስሎ በዛም ውስጥ መውደቅና መነሳት ቁልጭ ብሎ ስለቀረበ ነው። ይህም አፍሪካን በጥሩ መልኩ ያሳየ ሲሆን፣ ከአለባበስ ጀምሮ በቅኝ ግዛት ያልተነካና ያልተበከለ ባህልም ታይቶበታል። ሴቶችም ጠንካራና ብርቱ ሆነው ተስለዋል።

የጥቁር ተዋንያን ፈተና
ባለፉት ዓመታትም ጥቁር ተዋንያን ብዙ አማራጭ የነበራቸው አይደሉም። ይህን የሚያነሳው የ‹ብላክ ሆሊውድ ትምህርት እና ሀብት ማእከል ዋና ዳይሬክተር ጆን ፎርብስ ነው። ጆን እንዳለው በቀደመው ጊዜ ጥቁር ተዋንያን አግባብ ያልሆነ ድርሻ ወይም ገጸባህሪ ቢሰጣቸውም፣ በዘርፉ ለመቆየት ማድረግ ያለባቸውን ማድረግ ነበረባቸው። ይህም ማለት በ1900 መጀመሪያ የሚሰጣቸውን የሞኝና የደካማ ገጸባህሪም ቢሆን ወክለው ይጫወቱ ነበር ነው።

ጆን እንደሚለው ከሆነ፣ በተለይ ተዋናይና የኦስካር ሽልማትን ለመቀበል የመጀመሪያ ጥቁር ወንድ የሆነው ሲድኒ ፖይቲየር መምጣት በኋላ፣ ይልቁንም ከ1950ዎቹ ወዲህ፣ ሆሊውድ ለጥቁር ተዋንያን ያለውን እይታ የለወጠ ይመስላል። ‹‹ፖይቲየር ሁሌም ጠንካራ የሆነ ገጸባህሪ መፍጠር ችሎ ነበር። ይህ በትዕይንተ መስኮት ውስጥ የፈጠረው የጥቁር ሰው ምስልም ብዙዎች የኮሩበት ነበር።›› ጆን ለኢንኳየረር እንደጠቀሰው።

በቅርብ ዓመታትም እንደ ዊል ስሚዝ ያሉ ተዋንያን፣ በሥራ ባገኙት ትርፍ የዘረኝነት ልዩነትን ማጥበብ ችለዋል። ታድያ ይህን ስኬት ተከትሎ ትልቅ ኃላፊነት ይመጣል። እንደ ዊል ያሉ የቦክስ ኦፊክ ከዋክብት፣ ሆሊውድ ለውጦችን እንዲያሳይ ግፈት የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው።

ሲኤንኤን እንደዘገበው ከሆነ፣ ጥቁር ተዋንያን በኦስካር ከፍተኛ ችግር ይገጥማቸዋል። ታሪክ እንደሚያስረዳው ታድያ በ1940 ሃቲ ማክ ዳንኤል የመጀመሪያዋ ጥቁር ተዋናይት ሆና በረዳት ተዋናይት ዘርፍ ስትሸለም፣ ይህን ሽልማት ያገኘችው ‹ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ› በተሰኘው ፊልም ላይ ባሳየችው ትወና ነው። ታድያ ሎስ አንጀለስ በሚገኝ አንድ ሆቴል በተካሄደው በዚህ የሽልማት ስነስርዓት ላይ፣ ተዋናይቱ ተነጥላ ኋለኛ ወንበር ላይ ነበር የተቀመጠችው።

ታድያ ይህቺ ተዋናይት የመጀመሪያዋ ተሸላሚ ጥቁር በመሆን በጉዳዩ ላይ ለውጦች እንደሚመጡ ተስፋ እንዲታይ ምክንያት ብትሆንም፣ በፊልሙ የነበራት ድርሻ በብዙዎች በተለይም በጥቁር ማኅበረሰብ ተቀባይነት አላገኘም ነበር። እንድትተውን የተሰጣት ድርሻና ገጸባህሪም አግባብ ያልሆነና አሳፋሪ ነው የሚል አቤቱታም ቀርቦበታል።

ታድያ ግን ተዋናይቷ በፊልሙ ላይ ባትሳተፍ ይሻል ነበር ለሚሉ፣ ተዋናይቷ የተሰጣትን የቤት ሠራተኝነት ድርሻ ባትቀበል፣ በፊልሙ ላይ አንድም ጥቁር ገጸባሕሪ አይኖርም ነበር የሚል መልስ የሚሰጡ አሉ። የእርሷ ነጥብም በዘርፉ ተሳትፎ ሊኖረን ይገባል የሚል ነው የሚሉ እይታዎችም ሲነሱ ተሰምቷል።

ይህ ከሆነ ከሰባ በላይ ዓመታት አልፈዋል። እንደ ቀደመው ጊዜ ሳይሆን ጥቂት የማይባሉ ጥቁር ተዋንያን በሆሊውድ ላይ የተለያየ ድርሻ ወክለው ይተውናሉ። በኦስካር ሽልማቶች ላይም በመካከል የዓመታት ልዩነት ቢኖርም እንኳ፣ ይታጫሉ፣ ይሸለማሉም።

ዶናልድ ቦግሌ ይህንን ጉዳይ አስታውሷል። አያይዞም ሌላ ክስተት ሲያነሳ፣ ሌና ሆርን የተባለች ጥቁር አሜሪካዊት ተዋናይት፣ በምትሠራበት ስቱዲዮ ሰፊ ማስታወቂያ ይሠራላት የነበረች ቢሆንም፣ ፀጉሯን ለመሠራት ማንም ለመንካት ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ ያንን ማድረግ የሚችሉ ጥቁሮች ይጠሩ እንደነበር ይናገራል።

የስፓይክ ሊ ‹Da 5 Bloods›
አሜሪካዊው የፊልም ደራሲ፣ ዳይሬክተርና ፕሮድዩሰር እንዲሁም ፕሮፌሰር ሼልተን ጃክሰን ‹ስፓይክ› ሊ፣ በቬትናም ጦርነት ዙሪያ የሚያጠነጥን ፊልም ለእይታ አቅርቧል። በዚህም አፍሪካ አሜሪካውያን የነበራቸውን ድርሻ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጧል። ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ይህ ፊልም የቬትናምን ጦርነት በተለየ መልክ ነው ያስቃኘው።

ፊልሙ የአራት አፍሪካ አሜሪካውያንን ታሪክ የሚናገር ሲሆን፣ እነዚህ ሰዎች ከጦርነቱ ማብቃት ዓመታት በኋላ ወደ ቬትናም ተመልሰው የቀደሙ ጓደኞቻቸውን አስክሬን ለመውሰድና በስፍራው የተቀበረና በጦርነቱ ጊዜ ለደቡብ ቬትናም ተባባሪዎች የሚከፈል የነበረ ወርቅን ለማውጣት ነው።

በዚህም ጉዞ ስፓይክ የሚያሳየው እነዚህ ወታደሮች ጋር ያለውን ትዝታና እንደ ጥቁር ወታደር ልጥረትና ትግላቸው እውቅና የማይሰጣቸው ስለመሆኑ፣ እንደውም በዘረኝነት ለመገለል ተጋላጭና ዒላማ መሆናቸውን ነው። ይህ ፊልም ታድያ በመጀመሪያ ስፓይክ እጅ ሲገባ፣ አራቱ ገጸባህርያት ነጭ ወታደሮች ወይም ዘማቾች ነበሩ። ይህም በኦሊቨር ስቶን መጀመሪያ የተዘጋጀ ነው። ስፓይክ ግን እነዚህን ገጸባህርያት አፍሪካ አሜሪካውያን በማድረግ፣ የታሪኩን ይዘት ሙሉ ለሙሉ ቀየረው።

እውነተኛ የጦርነት ክስተቶችን መሠረት ያደረጉ ፊልሞች ብዙዎቹ ነጮችን እንጂ ጥቁሮችንም ሆነ ሌሎችን ያማከሉ አይደሉም። ስፓይክ ለቢቢሲ እንዳለው ከሆነ በሲኒማ ታሪክ የጦርነት ፊልሞች ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዙ፣ ነጭ ጀግኖችን ብቻ የሚያወድሱ ናቸው። በዚህም ‹ Dunkirk› የተሰኘው ፊልም የሚጠቀስ ነው። ፊልሙ መቼቱን የኹለተኛውን የዓለም ጦርነት መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ የኢንግሊዝ፣ ቤልጄም እና የፈረንሳይ ወታደሮች ደንኪርክ ከተባለችው ከተማ ለመውጣት ከጀርመኖች ጋር ሚያደርጉትን ውጊያ የሚያሳይ ነው።

ታድያ በፊልሙ ሕንዳውያን እንዲሁም አፍሪካውያን አለመታየታቸው ብዙ የፊልም ተመራማሪዎችን አስደንቋል። ምክንያቱም ፊልሙ መሠረት ባደረገው እውነተኛ የጦርነት ታሪክ፣ አስፈላጊ ግብዓት የሚያመላልሱ የነበሩ የሕንድ ወታደሮች፣ ከሰሜን አፍሪካ የተውጣጡ ከፈረንሳይ ወራዊት ጋር የተገኙ ጥቁሮች፣ ደቡብ እስያ እና ምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ ሰዎች ሊታዩ ይገባ ነበር።

ለማጠቃለል
ታድያ ዘረኝነት ወቅታዊ ጉዳይ ሆኖ ተነሳ እንጂ፣ ጾተኝነትም በሆሊውድ ተመሳሳይነት ያለው ቅሬታ ይነሳበታል። ዘረኝነትና ፆተኝነት ሲገናኝ ደግሞ፣ በተለይ ለሴት ተዋንያት ፈተና እንዲሁም የሚሳሉ ገጸባህርያት ላይም እጅግ ክፈተትና እንከን የሚገኝበት እንዲሆን አድርጓል።

እንደሙዚቃ ሁሉ ፊልም የዓለም ቋንቋ ሆኗል። የአንዳንድ አገራት የፊልም ዘርፍ ከሌሎች ያደገ ቢሆንም፣ ሁሉም ግን ሰውነትን አጉልተው እንዲያሳዩ ይጠበቃል። ነጮች በብዛት በሚገኙበት በተለይ ተጽእኖ ፈጣሪ በሆነው ሆሊውድ፣ የፊልም ባለሞያዎች የኖሩበትን የዘረኝነት መልክ ሊያንጸባርቁ ይችላል። ሰው ናቸው። በዚህ ላይ ለውጥ ለማምጣት ምንአልባት ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ አንጋፋና ተጽእኖ ፈጣ መሆን የቻሉ ጥቁር የፊልም ባለሞያዎች ግን ለውጡን ለማምጣት አቅም አላቸው። እናም ይህ ለውጥ ቢያንስ በተዋናይ መረጣ እንዲሁም በፊልም የመጋረጃ ጀርባ ሥራ ላይ እንዲሳተፉና፣ ሙሉ ለሙሉ ዘርፉን እንዲቀይሩ የሚያስችላቸውን ኃይል ይሰጣቸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here