ሰሞነኛ መነጋገሪያ ከሆኑት የማኅበራዊ ትስስር እንዲሁም መደበኛ መገናኛ ብዙኀን መካከል የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የነበሩት ኬሪያ ኢብራሒም ድንገተኛ የሥልጣን መልቀቅ ጉዳይ አንዱ ነው። የአፈ ጉባዔዋን ሥልጣን መልቀቅ መነጋገሪያ ካደረጉት ጉዳዮች መካከል የሚመሩት ምክር ቤት መጪውን አገር ዐቀፍ ምርጫ በተመለከተ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ያስፈልገዋል በሚል ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራለትን እና በሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚሽን የሚቀርብለትን ምክረ ሐሳብ መርምሮ ውሳኔ በሚያስተላልፍበት ዋዜማ መፈጠሩ ነው።
በሥራ ላይ ባለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሰረት የሉዓላዊነት ሥልጣን ባለቤትነት የተሰጣቸው ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የተወከሉበት ይህ ላዕላይ ምክር ቤት ከሌሎች አገራት በተለየ ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን ያለው ሲሆን የክልሎችን በጅት ድልድል ቀመር፣ በክልሎች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሔ መፈለግ፣ የፍትሐ ብሔር ሕግ ሊወጡላቸው የሚገቡ ጉዳዮችን መለየት እና ሌሎች ሥልጣኖች አሉት።
ኬሪያ በራሳቸው ፊርማ የተበተነ የጉባዔ ጥሪን ካስተላለፉ በኋላ ሥልጣናቸውን ባልተለመደ ሁኔታ በትግራይ ቴሌቪዥን በኩል ብቅ ብለው በሰጡት መግለጫ ማሳወቃቸው አነጋጋሪ ሆኗል። ‘‘ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቦቼ እና ለሕሊናዬ የገባኹትን ቃል ለማክበር ስል በገዛ ፈቃዴ ከፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔነቴ የተሰናበትኩ መሆኔን አሳውቃሉ’’ በማለት እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ገፊ የሆኗቸው ምክንያቶች ሕገ መንግሥት በአደባባይ ሲጣስ እና አምባገነን መንግሥት ሲመሰረት ተባባሪ ላለመሆን ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
ሕውሓት በፌደራል ደረጃ አንድ የቀራትን ትልቅ ሥልጣን ይዘውት የነበረው ኬሪያ* ከሥልጣን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ የሚሉትን አንዳንዶች አሜን ብለው የተቀበሉት ያክል፤ ሌሎች ደግሞ ፓርቲያቸው ጥብቅ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን የምትከተል በመሆኑ ፖለቲካዊ አንድምታው አለው ሲሉ ተሟግተዋል። በተለይ ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የአገራዊ ምርጫውን በተመለከተ ሕገ መንግሥት ትርጓሜ ላይ ውሳኔ ይሰጣል በተባለበት እና አፈ ጉባዔዋ ጠርተውታል በተባለለት ጉባዔ ዋዜማ መሆኑ ፖሊቲካዊ ትርጉሙ እንዲጎላ አድርጎታል። አንዳንድ ተከራካሪዎች ደግሞ ሕወሓት የፌደራል መንግሥቱን ለማሳጣት የቀራትን አንድ ጥይት ተኩሳ አባክናዋለች ሲሉም ተሳልቀዋል።
የኬሪያ በገዛ ፈቃድ ድንገቴ ሥልጣን መልቀቅ ከፖለቲካዊ አንድምታው በዘለለ የብዙዎች የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ተጠቃሚዎችን ሲያነታርክ የከረመው የሴትየዋ የግል ገበና ጉዳይ ሆኗል። ከተራ ካድሬነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እስከ ሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ ብሎም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔነት የደረሱት ኬሬያ፣ ትዳራቸውን መሥዋዕት አድርገው ሲሉ ይከሷቸዋል። ይህንንም ተከትሎ የቀድሞ ባለቤታቸው እና የሦስት ልጆቻቸው አባት ናቸው የተባሉ ግለሰብ ፎቶ ግራፍም በማኅበራዊ ገፆች ላይ ሲንሸራሸር ሰንብቷል። ከትዳራቸው የተፈናቀሉት ግለሰብ በሰዎች እርዳታ የልብስ ስፌት መኪና ተገዝቶላቸው ራሳቸውን በማስተዳደር ላይ እንደሚገኙ እና ብዙ ጊዜ ‘‘ሚስቴን ነጠቀችኝ’’ ሲሉ ሕወሓትን በተደጋጋሚ ያማርራሉ በማለት ግለሰቡን እናውቃቸዋልን ከሚሉት ወገኖች ወሬው ተናፍሷል።
የኬሪያ በዚህ ወቅት ሥልጣን መልቀቅ ሕወሓት በማዕካላዊ መንግሥት እንዴት እየተገፋች እንደሆነ አንድ ተጨባጭ ማሳያ ነው ብለው ደጋፊዎቻቸው ይከራከራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ የሴትየዋ ሥልጣን በዚህ ወቅት መልቀቅ ቆራጥነታቸውን እና ለድርጅታቸው ያላቸውን ታማኝነት ያረጋገጡበት ከመሆኑም ባሻገር የመርኅ ሰው መሆናቸውን ማረጋገጫ አድርገው የወሰዱት አሉ፤ የእርምጃቸውን ትክክለኛነት በመደገፍ።
በሌላ በኩል ደግሞ ሥልጣናቸውን ደንብና ስርዓትን ባልተከተለ መልኩ መልቀቃቸው የራሳቸውን ክብር ያሳነሰ ብቻ ሳይሆን ቆሜለታለሁ የሚሉትን ሐሳብ ክስረት ላይ የጣለ ነው ብለው የተከራከሩ አልጠፉም። በሥልጣናቸው ትልቅነት ያክል ተጽዕኖ የማሳደር ዕድላቸውን አምክነዋል ሲሉ ቁጭት አይሉት ሐዘኔታ የተቀላቀለበት መከራከሪያ ነጥብ ያነሱም አሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሥልጣኑን ቢለቁትም ባይለቁትም የሚመጣ ለውጥ የለም ዝም ብለው ለፉ ሲሉ ደምድመዋል። እነዚህኞቹ ወገኖች የኬሪያ ሥልጣን መልቀቅ ከአንድ ሳምንት ወሬነት የዘለለ አንድምታ አይኖረውም በማለት ጉዳዩን አቃልለውታል።
የሆነው ሆኖ አፈ ጉባዔ ኬሪያ ኢብራሒም በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣን መልቀቃቸው ነጥብ አስጥሏቸው ይሁን አስቆጥሮላቸው ጊዜ መልስ የሚሰጠው ይሆናል።
ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012


