እህትን ለመጠበቅ…ትክክለኛው ጊዜ

0
709

የቤት ውስጥ ጥቃት ከኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ ብቻ 20 በመቶ ጨምሯል፤ የተባበሩት መንግሥታት።
‹አድርጉልኝ!› ‹ለውጡልኝ› ‹አሻሽሉልኝ› ‹ችግር አለና እወቁልኝ› ይህና ይህን መሰል ጥሪ አስቀድሞ ይመለከታቸዋል ላላቸው አካላት ያቀረበ ሰው፣ ምላሽ ካላገኘ ውሳኔዎችንና እርምጃዎች በእጁና በፈቃዱ ላይ ለማኖር ይገደዳል። በአሜሪካ ዘረኝነትን በሚመለከት የሆነው የዚህ አንዱ ማሳያ ነው። የሴቶችን ጉዳይ በሚመለከትም ተመሳሳይ ክስተት የሚፈጠርበት ጊዜ ሩቅ የሚሆን አይመስልም። እስከዛ ግን ሌላ አማራጭ ተገኝቷል።

እንዲህ ሆነ። በምዕራብ እስያ የሜዲትራንያን ባህር ዳርቻ አቅራቢያ በምትገኘው ዌስት ባንክ፣ ሴቶቹ የራሳቸውን ቋንቋ ፈጠሩ። የቤት ውስጥ ጥቃት በዚህ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሰሞን በርትቷልና፣ በእኩል ሰዓት በመስኮቶቻቸው በኩል የብረት ድስት እና ማንኪያ (ማማሰያ) በማውጣት እነዚህንም በማጋጨት ድምጽ አሰሙ።

የዚህ ድምጽ መልእክት አንድ ነበር፣ እሱም እንዲህ የሚል ነው፤ ‹‹ቤትሽ ውስጥ ጥቃት የደረሰብሽ ወይም እየደረሰብሽ ያለሽ ሴት፣ አምልጠሽ መውጣት ቢያስፈልግሽ፣ ወደ እኛ ቤት ነይ፣ በራችን ለአንቺ ክፍት ነው!››

ይህ ሴቶች እርስ በእርስ ያሳዩት መደጋገፍ በዓለም ዙሪያ በምሳሌነት የተጠቀሰና ሊጠቀስ የሚችል/የሚገባም ነው። ቢቢሲም ይህን ጉዳይ ሲዘግብ፣ እንዲህ ባለ አስቸጋሪና ለሴቶች ፈተናው በበዛበት ወቅት፣ ሴቶች እርስ በእርስ መረዳዳትና መደጋገፍ፣ አንዳቸው ባላቸው አቅም ሌላቸውን የመደገፍ ነገር፣ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ በማሳያ ጠቅሷል።

ራባብ በዌስት ባንክ ነዋሪ ናት። በመኖሪያ አካባቢዋ ሴቶችም በማማከር ትታወቃለች። እርሷ ደግሞ ከዚህ ባሻገር በማኅበራዊ ድረ ገጽ በተለይ ኢንስታግራም እና ዋትስ-አፕን በመጠቀም ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች ጋር ተደራሽ ለመሆን እየጣረች ትገኛለች።

ሞባይሏ አቃጨለ፣ አንድ መልእክት እንደደረሳት ለማሳወቅ። ከፍታ ተመለከተችው፣ መልእክቱም ይላል፣ ‹‹ባል ሚስቱን አስከፊና አግባብ ባልሆኑ የስድብ ቃላት ቢናገር፣ ያ ጥቃት ነው ይባላል?››

ራባብ ለቢቢሲ እንዳስረዳቸው ብዙ ሴቶች የቤት ውስጥ ጥቃት ምን እንደሆነ እንኳ አያውቁም። እናም ለዛ ነው ትላለች ራባብ፣ ትንሽም ቢሆን ጥቂትም ቢመስል መረጃን መቀባበል ትልቅ ተጽዕኖ ሊፈጥር የሚችለው። ይህም በማኅበራዊ ድረ ገጽ የሚደረግ ንግግር ጥቃት ከሚያደርሱባቸው ሰዎች ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ተዘግተው እንዲቀመጡ ለተገደዱ ሴቶች አማራጭ መንገድ ነው ብላም ታምናለች።

በሌሎች ከተሞችም ሴቶች በተመሳሳይ ዓላማ ግን የተለየ አካሄድን ተጠቅመዋል። ለምሳሌ ሕንድ ትጠቀሳለች። በሕንድ ከዋና ከተማው በብዙ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ታሃር በረሃ አካባቢ የሚሰማው የሴቶች የቤት ውስጥ ጥቃት፣ በሕንድ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች ሁሉ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘ ነው። እዚህ ለሚገኙ ሴቶች የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ መከሰትና እሱን ተከትሎ የመጣው የእንቅስቃሴ ገደብ፣ አስቀድሞ ከነበሩበት ድህነት ላይ ታክሎ ችግሩን በእጥፍ የሚያብሰው ሆኗል።

እናም መፍትሔ ያሉት አንድ መንገድ ነው፣ ይህም የስልክ መስመር መዘርጋት ነው። በዚህም ሴቶቹ ችግራቸውን ስልኩን ለሚያነሱት ሴቶች ያካፍላሉ። ምክር ያገኛሉ፣ እርዳታና ድጋፍም ይደረግላቸዋል። ይህንንም በበጎ ፈቃደኝነት ሴቶች ራሳቸው እየሠሩት ይገኛሉ።

ቢቢሲ በዓለም ዙሪያ ያሉ የሴቶችን እንቅስቃሴ በቃኘበት ዘገባ፣ ብራዚልንም እናገኛለን። ከ200 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚገኝባት ብራዚል ከፍተኛ የሆነ የቤት ውስጥ ጥቃት ለዘመናት ነበር፣ አሁንም አለ። የብራዚል መንግሥት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረትም፣ በየኹለት ደቂቃው አንድ የጾታዊ ጥቃት ይፈጸማል። ካለው ድህነት አንጻርም በአንድ ቤት ውስት ብዙ ሰዎች እንዲኖሩ ስለሚገደዱ፣ ሴቶች ጥቃት ካደረሱባቸውና ከሚያደርሱባቸው ሰዎች ጋር አብረው መኖር አማራጭ የማያገኙበት ጉዳይ ነው።

በብራዚልም ታድያ ሴቶች እርስ በእርስ ለመደጋገፍ የራሳቸውን መንገድ ዘይደዋል። ቢያንስ ሰብሰብ ብለው በየእለቱ ምግብ በማዘጋጀት ለተቸገሩና ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶች ያደርሳሉ። የሚመካከሩበትን አውድም አዘጋጅተዋል። እርስ በእርስ በቻሉትና በአቅማቸው መደጋገፍንም አማራጭ አድርገው ይዘዋል።

በቴክሳስ ሂውስተን ተማሪዎች ተባብረው፣ በማኅበራዊ ድረ ገጽ በመነጋገርም በበጎ ፈቃደኞች መሪነት ቀላል የማይባል ሥራን በሴቶች ጥቃት ዙሪያ እየከወኑ ይገኛሉ። እነርሱ የዘየዱት መላ ደግሞ ወዲህ ነው፣ የዓላማው በጎ ፈቃደኞች ከቤታቸው ሲወጡ ለየት ያለ ሹረብ ደርበው ነው። ይህም እርዳታ የሚፈልጉ ሴቶች ማንን እናናግር ብለው ሲያስቡ ቀርበው እንዲያናግሯቸው የሚያስችል መለያ ነው።

በዚህ ሥራ በጎ ፈቃደኛ የሆነችው አሺራ አኑሩድራን ለብዙዎች ቤት መቀመጥ ከመውጣት የባሰ ሕይወትን አደጋ ላይ መጣል እንደሆነ ካየችውና ከታዘበቸው ጠቅሳለች። ታድያ እነ አሺራ ችግር የደረሰባቸውን ሴቶች በተለያየ መልኩ የሚደግፉ ሲሆን፣ ይህም በየእለቱ በየቤታቸው ምግብ ጭምር ማድረስንም የሚያካትት ነው። በሕግም ቢሆን መፍትሄ ማግኘት የሚችሉበትን አጋጣሚ በመክፈት እርዳታ ማግኘት እንደሚችሉ ይነግሯቸዋል።

በፈረንሳይ የሆነውን ደግሞ ሲኤንኤን ዘግቦታል። በዛም በአገር ደረጃ ምስጢራዊ ቃላት ተዋውቀው ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታ ውስጥ ካሉ ያንን ቃል ብቻ እንዲጠሩና መፍትሄ እንደሚደርስላቸው ተገልጿል። ይህ የተጀመረበት ክስተትም የአንዲት ሴት አጋጣሚ ነው።

ሴቲቱ ወደ አንድ መድኃኒት ቤት አቀናች፣ በሰዓቱ ክፍት የነበሩት መድኃኒት ቤቶች ብቻ ነበሩ። ይህች ሴት መድኃኒት ልትገዛ ግን አልነበረም፣ ይልቁንም የትዳር አጋሯ እያደረሰባት ስላለው ጥቃት ለመድኃኒት ቤት ባለሞያው ወይም ፋርማሲስቱ ለመንገር ነበር። ተናገረች፣ ፖሊሶችም ደርሰውላት ጥቃት አድራሹ ታሰረ።
ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ ባለሞያዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ በወረርሽኙ ምክንያት ቤታቸው እንዲቀመጡ የተገደዱና ለጥቃት የተጋለጡ ሴቶች ፖሊሲም ጋር ለመደወል ይፈራሉ።

እናም በፈረንሳይ እንዲሁም በስፔን አንዳንድ ከተሞች ለጾታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች መድኃኒት ቤቶች ሲሄዱ ምሥጢራዊ ቃል በመጥረት ድረሱልኝ ማለት እንዲችሉ አሠራር ተመቻችቷል። አንዳንድ ስፍራም በተመሳሳይ በንግድ ማእከላት ወይም በሱፐር ማርኬቶች ጭምር ተመሳሳይ ይዘት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገዋል። እነዚህ ቦታዎች ሳይዘጉ ከሚቆዩ አገልግሎት ሰጪ ማእከላት ዋናዎቹ መሆናቸው ይታወቃል።

እንዲህ ያለ አሠራርን ወደ አገራችን ብናመጣስ? ጥቃት ደርሶብኛል ለማለትና አውጥቶ ለመናገር የሚፈሩ፣ ተናግረውም መፍትሄ ባያገኙ የባሰ የሚገጥማቸውን ጥቃት በመፍራት ያለውን ችለው የሚኖሩ መፍትሄ አያገኙ ይሆን?

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የተለያዩ ሰዎችን ሐሳብ መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመውሰድ ሞክራ ነበር። ከእነዛም ውስጥ በሐሳቡ የሚስማሙ ቢበዙም፣ ለማሳካት ግን እንደማይሆን ስጋታቸውን አንድ ላይ ያነሳሉ። አንድ በጉዳዩ ላይ ሐሳቡን ያካፈለ ሰውም ለአዲስ ማለዳ እንዲህ አለ፣ ‹‹ሴቶች እርስ በእርስ መረዳዳታቸው ትልቅ ዋጋ አለው። ግን ችግር ገጠመን ብለው ፖሊስ ጋር በቅርበት ሄደው ቢያናግሩ፣ የሚያገኙት መልስ እንደሚጠበቀው ላይሆን ይችላል።››

ይህ አስተያየት ሰጪ ከሰማውና ከታዘበው እንዲህ ጠቀሰ። ጥንዶች መንገድ ላይ ይጣላሉ። ወንዱም ሴቷን ክፉኛ ፊቷን በጥፊ ይመታታል። በአጋጣሚ በአቅራቢያው ፖሊሶች ነበሩና ሁኔታውን አይተው ይቀርባሉ። ‹‹ምን ሆናችሁ ነው፣ ለምን መታሃት?›› በማለት ፖሊሱ ይጠይቃል። ‹‹ተይ ያልኳትን አልሰማ ብላኝ ነው!›› ብሎ ወንድየው ለፖሊሱ ይመልሰል።

ፖሊሱም ‹‹የሚልሽንማ ስሚ! በሉ ሂዱ! ተስማሙ›› ብሎ ይሸኛቸዋል። ይህቺ ሴት በሰዓቱ አንዳች ቅሬታ አሰምታ ቢሆን ኖሮ ፖሊሱ ይከላከልላት ነበር? ለሴቷ ሊከላከልላት የሚችልበት አጋጣሚ ጠባብ ነው። እናም አስተያየት ሰጪ እንዲህ ሲል የሐሳቡን መቋጫ አደረገ፣ ‹‹በዓለማቀፍ ደረጃ ሴቶች ላይ ጥቃቶች ይደርሳሉ። ይህ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው። ይጠብቃል የሚባለውና መፍትሄ የሚፈለግበት የሕግ አካልም ጋር መፍትሄ የማይገኝ ከሆነ ግን፣ ችግሩ የበለጠ ይወሳሰባል።››
በኢትዮጵያ በርካታ የመንግሥት ተቋማት በሮቻቸውን የዘጉ ሲሆን፣ የፍትህ አካላት ግን የሴቶችን ጉዳይ ለመከታተል በሮቻቸው ክፍት መሆናቸውን ተናግረዋል። በሴታዊት የተዘጋጀው አለኝታ የተሰኘው ነጻ የስልክ መስመርም (6388) ‹አቤት› ለሚሉና ችግራቸውን ይነግሩት ላጡ ሴቶች ክፍት ነው።

አሁን በኮቪድ 19 ምክንያት የቆየው የእንቅስቃሴ ገደብ በተወሰነ ደረጃ ተከፍቷል። ቢሆንም አሁንም የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙ ዳግም ሊያገረሽ እንደሚችል እየተነበየ ይገኛል። በዛም አለ በዚህ ከዌስት ባንክ ጀምሮ እስከ ቴክሳስ ድረስ፣ እንዲሁም በፈረንሳይና በስፔን ሴቶች እርስ በእርስ በመተባበር እንዲሁም መላ በመዘየድ ለጊዜው ጥቂት ትንፋሽ አግኝተዋል። በየአገሩም ይህ የሴቶች ትብብር ከምንም ጊዜ በላይ አሁን የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶንዩ ጉቴሬዝ፣ በወረርሽኙ የመጀመሪያ ሳምንታት ሰሞን እንዲህ አሉ። ‹‹ሰላም የጦርነት አለመኖር አይደለም። በዚህ የእንቅስቃሴ ገደብ ባለበት ወቅት የቤታቸው ያሉ ብዙ ሴቶች ሰላምን ሊያገኙበት በሚገባ በገዛ ቤታቸው ጥቃትን እያስተናገዱ ነው። እናም በየቤቱ ሰላም እንዲሆን ለዓለም ሁሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ሁሉም የየአገራት መንግሥታት ለወረርሽኙ በሚሰጡት ምላሽ የሴቶችን ደኅንነት ጉዳይ ቅድሚያ እንዲሰጡት አስገነዝባለሁ።››

ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here