በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 አንቲቦዲ የቅኝትና ዳሰሳ ምርመራ ከዛሬ ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ መካሄድ መጀመሩን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ይህ የምርመራ አይነት የኮቪደ-19 በሽታ ያለበት ሰው ላይ ቫይረሱን ለመለየት የሚረዳ የሞላኪዩላር ምርመራ ነው ተብሏል።
የጤና ሚኒስቴር በፌስ ቡክ ድሕረ ገፁ እንዳስታወቀው ከሆነ ይህ የአንቲቦዲ የቅኝትና ዳሰሳ ምርመራ ከዛሬ ሰኔ 15 እሰከ ሀምሌ 7 ቀን 2012 ድረስ በሀገራችን የሚካሄድ ይሆናል።
ምርመራው ከሰውነታችን ከ3 እስከ 5 ሚሊ ሊትር ደም ናሙና በመውሰድ የሚደረግ እና የበሽታው ተከላካዮች (አንቲቦዲ) እንደየበሽታው ዓይነት የሚለያዩ ሲሆን ምርመራው ኮቪድ-19 ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ለሚደረገው የቅኝት ዳሰሳ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተገልጿል፡፡
ነገር ግን የአንቲቦዲ ምርመራ ውጤትን ብቻ ተጠቅሞ ህክምና መስጠት እንደማይቻልም ተገልጿል፡፡
ይህ የቅኝት ዳሰሳ በሀገራችን ያለውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለማወቅ በአዲስ አበባ፣ ድሬደዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ይካሄዳል ተብሏል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ፣ የጤና ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለትግበራው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉም ሚኒስቴሩ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ በነፃ የስልክ መስመር 8335 ወይም በ952 ወይም በመደበኛ የስልክ ቁጥር 0118276796 በመደወል ወይም በኢሜል አድራሻ [email protected] በመጠቀም ወይም ባሉበት ክልል በተዘጋጁ ነፃ የስልክ መስመሮች በመደወል ሪፖርት እንዲያደርጉ ወይም በአካባቢው ለሚገኙ ጤና ተቋማት በስልክ እንዲያሳውቁም ተጠይቋል፡፡



