በመንግሥት የተጀመረው የሴፍቲ ኔት አገልግሎት የታሰበውን ግብ እየመታ እንዳልሆነ ተገለጸ

0
647

የሴፍቲ ኔት አገልግሎት አቅም ለሌላቸው እና ከድህነት ወለል በታች ለሆኑ ዜጎች መደገፊያ እንዲሆን ታስቦ ቢዘጋጅም፣ እየተጠቀሙበት ያሉት ገቢ ያላቸው ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት በመሆኑ የታለመለትን ግብ እየመታ አለመሆኑ ተጠቆመ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ 7 በተለምዶው የረር በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ‹‹መንግሥት የአቅም ማነስ ያለባቸውን የሴፍቲ ኔት ተጠቃሚ እንድንሆን አገልግሎቱን ቢዘረጋልም፣ ነገር ግን በወረዳው የአቅም ማነስ ላለብን ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የገቢ ምንጭ ያላቸው ሰዎች ለተጨማሪ ገቢ እየተጠቀሙበት እየታዘብን ነው።›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የሴፍቲ ኔት አገልግሎት አሰጣጡ በቤተሰብ ልክ ሲሆን፣ በአንድ ሰው ሦስት መቶ ብር እንዲከፈላቸው ይደረግ እና የመንገድ ፅዳት አገልግሎት አንዱ የቤተሰብ አባል እንዲሠራ በማድረግ በዛ ልክ እንዲከፈል የሚደረግበት መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል። ነገር ግን አገልግሎቱ ሥራ አጥ ሆነው ምንም አይነት የገቢ ምንጭ ለሌላቸው፣ ከዛም በተጨማሪ በቤት ኪራይ ውስጥ ለሚኖሩ እና አረጋውያን ሆነው ጧሪ ለሌላቸው ሊሆን ቢገባም፣ የዚህ ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው እና የግል መኖርያ ቤት ያላቸው እንደሆኑም ምንጮች ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ከዛም በተጨማሪ ‹‹የኑሮ ውድነቱ እየባሰ ሲመጣ እና ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ደግሞ በችግራችን ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሲሆንብን፣ ሄደን ለወረዳ አስተዳደሩ እና ለሚመለከተው አካል ብንጮኽም፣ ከአንዱ ቢሮ ወደ አንዱ ቢሮ ከማመላለስ እና ከስድስት ወር በኋላ ተመለሱ ከማለት ውጪ ሰሚ አላገኘንም›› ሲሉም ተናግረዋል።

‹‹ቤት ለቤት ምዝገባ ተከናውኖ የአቅም ችግር ያለባቸው በሚለዩበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ ገቢ ላላቸው እና ከፍተኛ የሆነ የቤተሰብ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች እስከ ማካተት የደረሳችሁበት ምክንያት ምንድነው ብለን ስንጠይቅ፣ ከስድስት ወር በኋላ ይስተካከላል። እንዴት ሊመዘገቡ እንደቻሉና እንደ ችግረኛ እንደሚረዱ እኛም አናውቅም›› ተብለው ከወረዳ ሰባት የሴፍቲ ኔት አገልግሎት ሰጪ ክፍል በተደጋጋሚ እንደተገለጸላቸው የወረዳው ነዋሪዎች ይገልፃሉ።

ከዛም በተጨማሪ በወረዳው አቅም በሌላቸው ሥም በተደጋጋሚ ከኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ እርዳታ እንዲደረግላቸው ተብሎ የሚገባ ቢሆንም፣ ሌሊት ሌሊት እንደሚወጣ እና እርዳታው ሲከፋፈል ሳይታይ አልቋል እንደሚባሉም ጨምረው ይናገራሉ።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ የወረዳ ሰባት ዋና ሥራ አስፈፃሚን ለማግኘት ብትሞክርም ሳይሳካ ቀርቷል። ነገር ግን በወረዳው የሴፍቲ ኔት አገልግሎት ሰጪ ክፍል የኮሚቴ አባል ለአዲስ ማለዳ ሲያስረዱ፣ ‹‹ነዋሪዎቹ የሚያነሱትን ችግር እኔ በግሌ አስተውያለው›› ብለዋል። የሴፍቲኔት ፕሮግራም ከቤት ለቤት ምዝገባ ጀምሮ አብረው መሥራታቸውን አውስተዋ፣ በምዝገባው አቅምና የዕለት ገቢ የሌላቸውን እና በኪራይ ቤት ሆነውም ችግር ላይ የነበሩትን ብቻ ነበር የመዘገብነው ሲሉ ጠቅሰዋል።

‹‹ነገር ግን አሁን ላይ ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉትን ገቢ ያላቸውን ሰዎች በአገልግሎቱ እንዴት ሊካተቱ እንደቻሉ የእኔም ጥያቄ ነው።›› ሲሉ ችግሩን እንዳስተዋሉት ገልጸዋል። በተያያዘም ከወረዳ ሰባት ነዋሪዎች ተደጋጋሚ ጊዜ ሰዎች እየመጡ ይስተካከልልን ብለው እንደሚጠይቁ በማንሳት፣ ነገር ግን ለዚህ ምላሽ መስጠት የሚችሉት በዚህ ዘርፍ ላይ የተወከሉት ዋና ኃላፊው ብቻ እንደሆኑም ተናግረዋል።

በተጨማሪ የወረዳ 7 የሴፍቲ ኔት አገልግሎት ዋና ኃላፊ ቅድስት ማትዮስ፣ በአገልግሎቱ 814 የሚሆኑ ተጠቃሚዎች እንዳሉ ገልቷል። ለእነርሱም በቤተሰባቸው ልክ ክፍያው ይፈጸማል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ለሚነሱት ቅሬታዎች ደግሞ በቃል ብቻ ምንም አይነት ቅሬታን እንደማያስተናግዱ፣ ነገር ግን በደብዳቤ ቅሬታው እንዳልገባላቸው ተናግረዋል። ቢሆንም ስድስት ወር ተጠብቆ ዳሰሳ እና ማሻሻያ ይደረግ የነበረ ቢሆንም፣ ያንን እንዳያደርጉ ደግሞ ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ እንደገደባቸው እና በአጭር ጊዜ ግን ማሻሻያዎችን እንደሚያደርጉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here