ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች አድማ በማድረጋቸው የነዳጅ አቅርቦት ተስተጓጎለ

0
1010

ድንበር ተሻጋሪ የፈሳሽ ጭነት አሽከርካሪዎች አድማ በማድረጋቸው ምክንያት ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎሉ ታወቀ።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ነዳጅ ማደያዎች የነዳጅ አመላላሽ ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች አድማ መምታታቸውን ተከትሎ የነዳጅ አቅርቦት እንደቀነሰ እንደተነገራቸው ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ አንዳንድ ነዳጅ ለማስሞላት በረጃጅም ሰልፎች ውስጥ ሆነው ወረፋ ሲጠብቁ አግኝታ ያነጋገረቻቸው አሽከርካሪዎች እና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች እንደሚሉት፣ ወደብ ላይ ነዳጅ ቢኖርም ነገር ግን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት አሽከርካሪዎች ሥራ በማቆማቸው እጥረቱ እንደተከሰተ እና ‹‹ከሰሞኑ ይመጣል›› መባላቸውን ተናግረው ጉዳዩም እያሳሰባቸው መሆኑን አንስተዋል።

በተያያዘም በግል ተሽከርካሪዎቻቸው ወደ አገር ውስጥ የነዳጅ ምርቶችን የሚያስገቡ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶችን አዲስ ማለዳ ባነጋገረችበት ወቅት ያገኘችው ምላሽ እንደሚያመለክተው፤ እነርሱ ጋር የሥራ ማቆም አድማ እንደሌለ እና ነገር ግን የመንግሥት የፈሳሽ ጭነት አሽከርካሪዎች የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን እየሰሙ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ (ሰኔ 13/2012) 85ኛ እትሟ፣ የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች መገለል እየደረሰባቸው መሆኑን እና በዚህም ምክንያት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አሽከርካሪዎች ሥራቸውን እያቆሙ መሆኑን መዘግቧ ይታወሳል።

ከዚህ ጋር ተያያዞ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣንም በከባድ መኪና ሾፌሮች ላይ የሚደርሰውን መገለል ለመቀነስ በማሰብ በየመንገዱ ኬላዎች ላይ የተለያዩ አገልግሎቶቸ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ እየሠራ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረው ነበር። ይሁን እንጂ አሁንም ተመሳሳይ ቅሬታ እያቀረቡ ያሉ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች አልጠፉም። በዚህም የነዳጅ አቅርቦት ላይ ችግር እየተፈጠረ መሆኑን በከተማዋ የሚገኙ የነዳጅ ማደያ ሠራተኞች እና ተጠቃሚዎች ይናገራሉ።

ከዛም በተጨማሪ ማብራሪያቸውን የሰጡት የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ክብረት ዓለማየሁ እንደገለጹት፣ በተከሰተው የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች በጉዟቸው ወቅት ከዚህ ቀደም ተሽከርካሪዎችን በማቆም እረፍት ያደርጉባቸው በነበሩ ከተሞች እንዳያርፉ በነዋሪዎች መገለል ደርሶባቸዋል። እንዲሁም በጫካ ውስጥ አቁመው ሰው በሌለባቸው አካባቢዎች እንዲያርፉ ተደርገዋል ሲሉ መጠቆማቸውም ይታወሳል።

በዚህም በርካታ አሽከርካሪዎች በጉዟቸው ወቅት ምግብ ለማግኘት እንኳን እንደተቸገሩ ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም የከፋው ነገር ደግሞ አሽከርካሪዎች በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች ከሚገኝ ቋሚ መኖሪያቸው እንዲለቁ እየተደረጉ መሆኑንም አዲስ ማለዳ ዘግባ ነበር።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ታደሰ ኃይለማርያም፣ አሁን የነዳጅ አጥረት እየተስተዋለ ያለው የአቅርቦት እጥረት አጋጥሞ አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል። ከዛም በተጨማሪ የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ሥራ የማቆም አድማ አድርገዋል። በዚህም ነው የነዳጅ እጥረት እየተስተዋለ ያለው የሚለውን ቅሬታ ስህተት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ታደሰ እንደሚገልጹት ከሆነ ከሰሞኑ እየተስተዋለ ያለው የነዳጅ እጥረት የአጭር ጊዜ እንደሆነና ኅብረተሰቡንና ነዳጅ ቀጂዎችንም ጭምር እንደዛ እንዲያስቡ ያደረጋቸው የወቅቱ ሁኔታ ተጽእኖ ነው ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘው እንደሚሉት፣ በዋናነት እጥረቱ ያጋጠመበት ምክንያት ከሎጂስቲክስ ጋር የተያያዘ መሆኑን እና አንዳንድ ቦታዎች ላይ መንገድ ጥገና በመኖሩ እንዲሁም መንገዶችም ለአሽከርካሪዎች እና ለተሽከርካሪዎች እንደልብ መንቀሳቀስ የማያስችሉ በመሆናቸው ነው። በተጨማሪም በፍጥነት ለማሽከርከር የማያስችልበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው ነው፣ እጥረቱም ለአጭር ጊዜ ነው የሚቆየው ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎችና አዲስ ማለዳም በተዘዋወረችባቸው ነዳጅ ማደያዎች፣ ነዳጅ ለመቅዳት ከፍተኛ የሆነ ሰልፍ እና በአብዛኞቹ የነዳጅ ማደያዎች ላይም ‹ናፍጣ የለም› የሚል ማስታወቂያ መለጠፋን ለመታዘብ ችላለች።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here