የአደባባይ ላይ ሐይማኖታዊ ስብከቶች በመንግሥት ዐይን

0
1133

‹‹በየአደባባዩ ላይ የተለያዩ ሐይማኖት ተቋማት የስብከት ዓይነት አንድምታ ያላቸውን መልዕክቶች ያስተላልፋሉ። እነዛ መልዕክቶች በሚተላለፉባቸው አደባባዮች ላይ ያሉ የተለያየ እምነት ተከታዮች ከመኖራቸው ባለፈ፣ የሚተላለፉት መልዕክቶች ሰዎች ላይ የሥነ ልቦና ጫና እንደሚያደርስ በተደጋጋሚ በተቋማችን እየመጣ የሚቀርብልን ቅሬታ ያመላክታል።›› ያሉት የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ናቸው።

ይህን መባሉን ምክንያት በማድረግ አዲስ ማለዳ የአካባቢ ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተስፋዬ ጋሻው አናግራ ነበር። በተቋማችሁ እንዲህ አይነት ጉዳዮች እንዴት ታዩታላችሁ? ጥቆማስ ቢመጣ ያንን የመከታተል ሥልጣን እና ውሳኔ እንዲሰጥ ማድረግ ትችላላችሁ ወይ? ብላም ጠይቃለች። እርሳቸውም በሰጡት ምላሽ ‹‹ከአቅም በላይ አስቸግረውን የነበረው የሐይማኖት ተቋማት የመንገድ ላይ ስብከቶች ነው።›› ያሉ ሲሆን፣ ከዛም በተጨማሪ ቁጥጥሩን በራሳቸው ተነሳሽነት እንዳያደርጉ በበጎ ጎኑ የመውሰድ ነገር ላይኖር ይችላል በሚል ስጋት ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዛም በተጨማሪ ተስፋዬ እንደሚናገሩት፣ ኅብረተሰቡ የድምፅ ብክለት በአካባቢው ሲከሰት ይሄ ይወገድልኝ በማለት ጥያቄ ማንሳት መብቱ መስሎ ስላማይታየው እና ግንዛቤ እጥረት ስላለው እየተቸገረ ነው። ይሄንንም እኛ ታዝበናል ብለዋል። ጨምረውም የመንገድ ላይ ስብከቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ መጠየቁን አድንቀው፣ ነገር ግን መጀመርያ ጉዳዩ እኛን በዋናነት ስለሚመለከት እኛን ማሳወቅ ነበረባቸው፣ እኛም የተቸገርንበት ጉዳይ በመሆኑ ብለዋል።

አልፎ አልፎ ከአቅማቸው በላይ ሲሆን በሰፈር እና አካባቢውያቸው በሚገኝ የሌሊት መጠጥ ቤቶች ላይ ጥቆማ ለማድረስ ከሚመጡ ግለሰቦች ውጪ፣ የመንገድ ላይ ስብከቶች እና ከሐይማኖት ተቋማት ስለሚወጣው ድምፅ ድፍረት ኖሯቸውና መብታቸውም ስለሆነ ያንን አውቀው የሚጠይቁ የሉም፣ ይፈራሉ ብለዋል።

ነገር ግን የኅብረተሰቡ አመለካከት ላይ ከተሠራ በሕግ የማስጠየቅ መብት እንዳላቸው እና ተቋማቸውም በደረጃ እንደዚህ አይነት የሕግ ጥሰቶች ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚችሉ ተስፋዬ ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

በሌላ ሐይማኖት ላይ ዘለፋ እና ተንኳሽ የሆኑ የአደባባይ ላይ ስብከቶች የሚመለከተው አካል ቁጥጥር ሊያደርግባቸው እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቋል። ጉባኤው ሰኔ 1/2012 ለፌዴራል ፖሊስ በጻፈው ደብዳቤ እንደገለጸው፣ አንዳንድ አካባቢዎች በተለይም የበርካታ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች እና የዲፕሎማቶች መገኛ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የሐይማኖት ሰባኪዎች ከቤተ እምነቶቻቸው ቅጥር ግቢ ውጪ በመውጣት በአደባባይ ላይ የራሳቸው ወገን ያልሆኑ የእምነት ተከታዮችን በሚተነኩስ መልኩ ሐይማኖታዊ ትምህርቶች እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል። አንዳንድ ቦታዎችም ይህንኑ ትምህርት ከፍተኛ ድምፅ በሚያወጡ ድምፅ መሣሪያዎች ጭምር የሚታገዝ ሲሆን፣ ይህም ለሌሎች ተግባራት እና አገልግሎት ከሚለቀቁት ድምጾች ላይ ተጨምሮ ኅብረተሰቡ ለተሉያየ የድምፅ መበከል እና ሥነ- ልቦና ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነ ታሳቢ በማድረግ መሆኑን በደብዳቤው አስታውቋል።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 44 (1) ላይ ማንኛውም ሰው በንፁህ እና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት ያለው መሆኑን ይደነግጋል። ይህንንም የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ ተፈፃሚ ለማድረግ የድምፅ መጠንን ለመወሰን መመሪያም ስላለ በዛ መሰረት ተፈፃሚ እንደሚደረግም ስለ ቅጣት አሰጣጡ እና ጥፋት ስለመሆኑ ተብራርቶ ተቀምጧል።

በተለያዩ አካባቢዎች ቡና ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ ጋራጅ፣ የብረታ ብረት ብየዳዎች፣ ጎዳና ላይ ንግድ ማስታወቂዎች እና ቅስቀሳዎች የሚወጣው ድምጽ መጠን በሕግ ከተቀመጠው በላይ እንደሆነ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትና በአደባባዮች የሚለቀቁት ድምጾች በአካባቢው የሚገኙ ሰዎችን የጆሮ ጤንነት እየጎዱ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ አቤቱታዎች እንደሚደርሱ ተጠቁሟል።

ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ሐይማኖት ተቋማት (መምህራን እና ሰባኪያን) ከፍተኛ ድምፅ በሚለቁ የድምጽ መሣሪያዎችን በመጠቀም ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ የጎዳና ላይ ስብከት እያደረጉ ሲሆን፣ አልፎ አልፎም በእምነት ወደ ማይመስሏቸው ቤተ እምነቶች ስፍራ በመጠጋት ያስተምራሉ። ይሁን እንጂ እንደ ኢትዮጵያ ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጻ ከሆነ፣ ጎዳና ላይ ትምህርት ይዘት አስፈላጊ ሲሆን ሁሉም አማኞች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲጠነክሩ ስብከቱ (በቤተ እምነቶች) ተጠናክሮ ቢሰጥ ተቋሙም የሚደግፈው ነገር ነው።

ቀሲስ ታጋይ እንደሚሉት አሁን አሁን ግን እየቀረቡ ያሉት የአደባባይ እና የጎዳና ላይ ስብከቶች የራስ እምነትን ከመግለፅ ባለፈ የሌሎችን እምነት እና አስተምሮ መተንኮስ አዝማሚያ የሚታይባቸው እና ከገንቢነታቸው ይልቅ አፍራሽነታቸው እየጎላ የመጣ ነው። ይህም ቅድሚያ ካልታረመ በተለያየ ሐይማኖት ተከታዮች እና አማኞች መካከል የግጭት መንስዔ የመሆን እድሉ ሰፊ ሊሆን እንደሚችል፣ በዚህም ጉባኤው ስጋት እየገባው መምጣቱን ጠቅሰዋል።

እርሳቸው እንደሚሉትም በዚህ ማስጠንቀቂያ ላይ የተለየ የሃይማኖት ተቋም የለም። ነገር ግን እንዲህ እንዲደረግ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ከሁሉም ቤተ እምነት፣ ከእነርሱ እውቅና ውጪ የሚንቀሳቀሱ አሉ ብለዋል። ‹‹የኦርቶዶክሱም እንደ ባህታዊ ነን የሚሉ፣ በፕሮቴስታንትም ሊሆን ይችላል ነብይ ነን የሚሉ፣ በእስልምናም ዱአ እናደርጋለን የሚሉ ሊሆኑ ይችላሉ።›› ሲሉ ገልጸዋል።
ድምጽ ማጉያዎችን ተከራይተው ለረጅም ጊዜ የሌሎችን ሐይማኖት በመግፋት ለሌሎች ቤተ እምነት በር ድረስ በመጠጋት ወደ ግጭት የሚመሩ ተግባራት እየተፈጠሩ መሆናቸውንም ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ገልጸዋል።

‹‹እኛ ከንስሃ መግባቱ እና ከትምህርቱ ጋር አይደለም ችግራችን። ግጭት በሚያስነሳ ጉዳይ ግን የሚደረጉ ትንኮሳዎች ስለሆኑ የሚተላለፉት መልዕክቶች ይዘቶቻቸው ላይ እንደ ተቋም ይሄን መቆጣጠር፣ እንዳይከሰቱ ማድረግ የእኛ ኃላፊነት ነው። ይሄም ያስፈለገው በዚህ ምክንያት ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ለመቆጣጠር ከመሮጥ ቀድሞ መጠንቀቅ ያስፈልጋል በሚል ነው።›› ብለዋል።
ከቤተ እምነት ጊቢ ውጪ የሚደረገውን መቆጣጠር ያለበት ሕግ አስከባሪ እንደመሆኑ መጠን፣ እኛ ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ ጽፈናል፣ ከእኛ የሚጠበቀውን አድርገናል ያሉት ቀሲስ ታጋይ፣ ቀጣዩ የሕግ አስከባሪዎች ሥራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ከዛ በስተመጨረሻ ጉዳዩን እንዲያስፈፅም ለተላከለት የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጄይላን አብዲ አዲስ ማለዳ ስለ ጉዳዩ የታዘቡት ነገር እንዳለ እና ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ስለተላከላቸው ደብዳቤ ማስፈጸም ጀምራችሁ ይሆን ወይ ብላ ጠይቃ ነበር። እርሳቸውም በሰጡት ምላሽ፣ ደብዳቤው የተላከ ቢሆንም ነገር ግን ወደ ማስፈጸም አልገባንም ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁን እና እርሳቸው እንደታዘቡት ከሆነ በየመንገድ ላይ ያሉ ስብከቶች ለእነርሱ ሥራ ፈተኛ እንደሆነባቸው ነው። ጄይላን እንደሚሉት ‹‹ከተላከው ደብዳቤ በመነሳት ወደ እኛ ተቋም ከመላኩ በፊት ሐይማኖት ነክ ነገር እንደመሆኑ የኃይል እርምጃ እንድንወስድ ደብዳቤ ከሚላክ፣ ጉባዔው የሐይማኖት ተቋማትን እንዳለ በመሰብሰብ ሰላማዊ ውይይት ማድረግ መቅደም ነበረበት›› ባይ ናቸው። ከዛም አልፎ ችግር ከመጣ ወደ ሰላም ሚኒስቴር ተወስዶ ከአቅም በላይ ሲሆን ወደ እኛ ተቋም ቢመጣ ተዋረዱን ጠብቋል ማለት ነው ይላሉ።

‹‹ነገር ግን እነዛን ደረጃዎች ሳያልፍ የቆየ መሆኑ ችግሩን አጠንክሮታል›› የሚሉት ጄይላን ሐይማኖታዊ መሆኑ ደግሞ ሳያሳውቁ ወደ እርምጃ መግባት ችግሩን ያባብሰዋል። በቀላሉ መፍታት ተገቢ ነው።›› ብለዋል። ለምሳሌም ተከታዩን አነሱ፣ ‹‹የእስልምና እምነት ተከታዮች ከሆኑ ያ ችግር የሚስተዋልባቸው ተቋሙን ለይቶ ከስህተቱ እንዲቆጠብ ማድረግ፤ በኦርቶዶክስም ከሆነ እንደዛው፤ በፕሮቴስታንትም ከሆነ እንደዛው መደረግ ነው ያለበት።›› ይላሉ። ነገር ግን ይሄን አልፎ በሚመጣ ላይ መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ ቢደረግ ተገቢ ነው ሲሉ የፌዴራል ፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጀይላን አብዲ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የሥነ መለኮት መምህር ዘማች በንቂ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በሐይማኖት ላይ የሚወሰኑ ማንኛውም አይነት እርምጃዎች ጥንቃቄን ይፈልጋሉ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ረጅም ጊዜ ታሪኳ ሲታይ የብዙ ሐይማኖት ተከታዮች ያሉባት አገር ናት። እንዲሁም ረጅሙን ጊዜ በመከባበርና በመቻቻል ነው ስታሳልፍ የነበረው። አሁን ምናልባት የተወሰን ነገር ያንን እንዳያደፈርስ መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው ይላሉ።

‹‹ይህች አገር የብዙ ሐይማኖት ተከታይ እና የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር እንደመሆኗ እንደ ልብ ብዙ ነገር ለመከልከል የሚቆጥበን ነገር አለ። የምንፈልገውን ብቻ ሳይሆን የማንፈልገውንም እየሰማን መኖርን ለምደንበታል። ይህን እንዳያጠፋውም እሰጋለሁ።›› ይላሉ። ዘማች እንደሚሉት ከሆነ የሕገ መንግሥት መብትንም እስከ መግፈፍ ይደርሳልም ይላሉ። ይህ ማለትም የእምነት ነፃነት፣ የፈለጉትን እምነት የማመን እና የመስበክ ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ነው ብለው፣ ሰዎች ይሄን ተስፋ ተሰጥቷቸው ሲንቀሳቀሱ፣ እንደዚህ አይነት እርምጃ መወሰዱ ምናልባት ብዙዎችን ወደ አደባባይ ሊያስወጣ ይችላል።›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አስተያየት ሰጪ ለአዲስ ማለዳ ይህን በሚመለከት ሐሳባቸውን ሲያካፍሉ፣ የመንገድ ላይ ስብከቶችን ጨምሮ ማንኛውም የድምጽ ብክለት በሕግ ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ዕይታቸውን ገልጸዋል። ይህም ወርዶ እስከ መኪና ጡሩንባ የሚደርስ ነው ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ መቻቻልና መረባበሽ የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።
‹‹መንገድ ላይ ድምጽን አጉልቶ ሐይማኖትን መስበክና የሌላውን ትክክል እንዳልሆነ መናገር ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። በዚህ ዘመንም አይሠራም። ግጭት ከማስነሳት አንጻር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው። ከዛም ባለፈ ደግሞ ድምጹ ይረብሻል። ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ስብከቶቻችን በየተቋማቸው ማድረግ አለባቸው። በዛም ሆነው የሚሰሙት ድምጽም ሳይቀር አልፎ መሰማት የለበትም።›› ሲሉም አክለዋል።

እኚህ አስተያየት ሰጪ ታድያ፣ ነገሩን መንግሥት ልብ ካለው በየመንገዱ በመኪና እንዲሁም በእግረኛ በድምጽ ማጉያ ‹የበረሮና የአይጥ ማጥፊያ› ብለው ከሚጮኹት ጀምሮ፣ የመኪና ጡሩንባ ያለአግባብ እስከሚያሰሙት ድረስ ቁጥጥር ሊኖር ይገባል ብለዋል። የተረጋጋና ጸጥታ የሰፈነበት አካባቢ ሊኖር እንደሚገባና ያንን ማግኘትም የሰዎች መብት እንደሆነም አያይዘው ገልጸዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here