በዚህ ሳምንት ለንባብ የበቃው የተረፈ ራስ ወርቅ ‹‹የአንኮበሩ ሰው በጀኔቫ›› የተሰኘ መጽሐፍ ሦስት ክፍል እንዳለው ጸሐፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በመጀመሪያው ክፍል የኢትዮጵያና ዓለም አቀፉ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ታሪክና እድገት ሲተረክ፤ በሁለተኛው ክፍል ይኸው ይዘት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ቀርቦበታል። መጽሐፉ በተለይም በኢትዮጵያ ከአፄ ምኒልክ እስከ ዛሬ ያለውን የቴሌኮሙዩኒኬሽን ታሪክና እድገት ያትታል። ሦስተኛው ክፍል ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርሲቲያን በዓለም አቀፍ ምኅዳር ስላላት ይዞታ ጨምሮ ሌሎችም በደራሲው የተሠሩ ጥናቶች እንደተካተቱበት ገልጸዋል።
በሰሜን ሸዋ አንኮበር የተወለዱት ጸሐፊው ዋና መስሪያ ቤቱ ጄኔቫ በሚገኘው ዓለም አቀፉ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ማኅበር ለ40 ዓመታት ሠርተዋል። የማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አማካሪ ሆነው ሲያገለግሉ ‹‹በቴሌኮም›› ማስፋፋትና ማዘመን ሥራ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን ማካሄዳቸው ጠቅሰዋል።
መጽሐፉ በ400 ገጽ የተቀነበበ ሲሆን በመጀመሪያው ዕትም አንድ ሺሕ ቅጅ ታትሞ በ195 ብር ዋጋ ለገበያ ቀርቧል።
ደራሲው ከዚህ ቀደም ‹‹ታም ታም ቱ ኢንተርኔት›› የተሰኘ በአፍሪካ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ታሪክ ላይ ያነጣጠረ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የቀረበ ባለ 600 ገጽ መጽሐፍ ለንባብ ማቅረባቸውን ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ገልጸዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011