በአማራ ክልል በተከሰተ የኩፍኝ ወረርሽኝ 46 ሕጻናት ሕይወት ማለፉ ተገለጸ

0
829

በአማራ ክልል የኩፍኝ ወረርሽኝ በመከሰቱ የ46 ሕጻናት ሕይወት ማለፉን የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዮት ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው በወረርሽኙ ከ7 ሺሕ 200 በላይ ሕጻናት እንደተጠቁ የታወቀ ሲሆን፤ ይህም በክልሉ በወረርሽኝ መልክ ከተከሰቱ በሽታዎች ውስጥ በቀዳሚነት መቀመጡም ተገልጿል፡፡
በወረርሽኙ በክልሉ በኹሉም ዞኖች የተከሰተ ሲሆን እስካሁን በ87 ወረዳዎች ላይ በሽታው መከሰቱን የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽና መልሶ ማቋቋም ባለሙያ ሲሳይ አወቀ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
የኩፍኝ በሽታ በአሁኑ ጉዜ በክልሉ አስጊ መሆኑን የገለጹት ሲሳይ፣ ለኮቪድ-19 ወረርሽን መከላከል የተሰጠውን ያህል ትኩረት ካልተሰጠው ኮቪድ-19 ከሚያስከትለው ጉዳት በላይ በክልሉ የከፋ ነገር ሊከሰት እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ያሉ የጤና ተቋማት ትኩረታቸውን ኮቪድ-19ኝን መከላከል ላይ በማድረጋቸው እና ለቅድመ ክትባትና ድህረ ክትባት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ ለጤና ተቋማት ባለመድረሳቸው ችግሩን እንዲባባስ እንዳደረገው ሲሳይ አመላክተዋል፡፡
ምንም እንኳን ወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በሽታውን የመከላከል ስራውን ፈታኝ ቢያደርገውም ከስርጭቱ ፍጥነትና ገዳይነት አንጻር በተለይ ትኩረት ሰጥተን ጎን ለጎን ካልተሰራ ከፍተኛ ችግር ያጋጥመናል ሲሉ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡
ስለሆነም የክልል ጤና ቢሮ ከሰኔ 23/2012 እስከ ሐምሌ 2/2012 ለተከታታይ 10 ቀናት በኹሉም የክልሉ ቀበሌዎች የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ከአስተማማኝ የጎን ለጎን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ስራ ጋር በማቀናጀት እና ለዘመቻው በቂ የሰው ኃይል በማዘጋጀት የህጻናት የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ለመስጠት አስፈላጊን ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱ ተጠቁሟል፡፡
ነገር ግን የኩፍኝ በሽታ ቅድመ መከላከል ክትባት የሚሰጠው እድሚያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ብቻ መሆኑ ለወረርሽኙ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጾ እያደረገ መሆኑ የተዘነጋ ጉዳይ መሆኑን ሲሳይ ጠቁመዋል፡፡ የኩፍኝ በሽታ ያጠቃል ተብሎ የሚታሰበው እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናትን ነው ከሚለው አመለካከት በተቃራኒ በክልሉ በተገኙ የበሽታው ተጠቂዎች በአብዛኛው እድሜያቸው ከአምስት እስከ 15 ዓመት የሆኑ ታዳጊዎችን መሆኑ ነው ሲሉ ሲሳይ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል፡፡ ስለሆነም ቅድመ ክትባቱን እድሜቸው እስከ አስራ አምስት ዓመት ለሆኑ ታዳጊዎችም ቢሰጥ መልካም መሆኑን ሲሳይ አመላክተዋል፡፡
የበሽታው ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱን የጠቆሙት ሲሳይ፣ የበሽታን ሽርጭት ለመግታት የሚስችል የክትባት መድኃኒት እጥረት በከፍተኛ ደረጃ መኖሩን አክለው አመላክተዋል፡፡ ለዚህ በሽታ ክትባት የሚውል መድኃኒት በባለፈው ዓመት ጥይቀው ምላሹ የተገኘው በተገባደደው በጀት ዓመት መሆኑንም ሲሳይ አስታቀውሰዋል፡፡
ሲሳይ እንደሚሉት በመንግስት በኩል ለበሽታው የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን በመጠቆም፣ ልክ እንደ ኮቪድ-19 ትኩረትና ቁርጠኝነት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሲሳይ አክለውም በክልሉ አሁን ላይ ከኮቪድ-19 ወረርስኝ በላይ አሳሳቢ የሆኑ ሌሎች በሽታዎች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
የኩፍኝ በሽታ ህጻናት እና አዋቂዎችን ለአዓነስውርነት እና ተያያዥ አካል ጉዳት መከሰት አንዱ መንስኤ በመሆኑ እያንዳንዱ ግለሰብ እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታችሁ ሁሉ ከላይ እስከታች ህብረተሰቡን የማስተማር እና ለክትባቱ የቅስቀሳ ስራውን በየደረጃው ከሚገኙ የጤና ሞያተኞች ጋር በመቀናጀት ማከናወን እንደሚገባ ሲሳይ አሳስበዋል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here