ለማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሚሰጠው የሰነድ ማረጋገጫ አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ ቆመ

0
463

የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በተመለከተ መሸጥ፣ መለወጥ፣ ስም ማዞር እና የመሳሰሉት እንቅስቃሴዎችን ተከትሎ በመንግሥት በኩል የሚሰጠው የሕጋዊነት ማረጋገጫ አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ መቆሙ ተገለጸ።
የኢፌዴሪ ሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው በኢትዮጵያ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ ሊኖር የሚችለውን መጨናነቅ እና አካላዊ ርቀትን አስጠብቆ ማስተናገድ ባለመቻሉ አገልግሎት መስጠት ለማቆም መገደዱን ገልጿል። የጽሕፈት ቤቶ ምክትል የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አለምሸት መሸሻ ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ መኖሪያ ቤት፣ የንግድ ቤት እና መሰል የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን ላልተወሰነ ጊዜ ለማቆም መገደዳቸውን እና ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ውጭ ምንም አይነት ተጨማሪ ምክንያት በጽሕፈት ቤቱ ዘንድ እንደሌለ አስታውቋል።
አለምሸት ጨምረው እንደገለጹት በአዲስ አበባ ባሉት 14 የጽሕፈት ቤቱ ቅርንጫፎች እና በድሬዳዋ ከተማ ባለው አንድ ቅርንጫፍ በቀን ውስጥ እስከ 6 ሺሕ ደንበኞችን የሚያስተናግድ ሲሆን ይህም ለወረርሽኙ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ተብሎ በመታመኑ በውል ለማይታወቅ ጊዜ አገልግሎት መስጠት ማቆሙን ለማወቅ ተችሏል።
ምክትል ዳይሬከተሩ ይህን ይበሉ እንጂ አዲስ ማለዳ ምንጮች እንደገለጹት ጽሕፈት ቤቱ አገልግሎት መስጠት ያቆመው በሐሰተኛ እና በተጭበረበሩ ሰነዶች የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች በሽያጭ ወደ ሌላ ወገን እየተላለፉ መሆናቸው እና መንግሥት ጆሮ በመድረሱ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ምንጮች አያይዘውም ጽሕፈት ቤቱ በከፊል አገልግሎት መስጠት ያቆመበት ምክንያት ከፍተኛ የአገልግሎት ተጠቃሚ ያለበትን የመኪና እና ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ስም እና ባለቤትነት ዝውውር በተመለከተ ምንም አይነት ለውጥ ሳያደርግ ካለው የተጠቃሚዎች ቁጥር አንጻር ዝቅተኛ ቁጥር ያለውን የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በሚመለከት ያወጣው መመሪያ ከኮቪድ 19 ውጭ እንደሆነ አስታውቀዋል።
የተነሳውን ጉዳይ በሚመለከት አለምሸት ምላሽ ሲሰጡ ‹‹የተባለው ጉዳይ ፍጹም ሐሰት ነው›› ሲሉ ይጀምራሉ። ቀጥለውም ወደ ጽሕፈት ቤቱ ይህን ያህል የተጭበረበሩ ሰነዶች በተለይም የቤት ካርታዎች እንደማይመጡ እና በተደጋጋሚ ግን ችግር የሆነባቸው የሐሰተኛ መታወቂያዎች ጉዳይ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አያይዘውም ‹‹ይህን ስንል ግን ሐሰተኛ የመኖሪያ እና ንግድ ቤቶች ሐሰተኛ ካርታዎች አይመጡም ማለት አይደለም›› ሲሉ አስታውቀዋል።
ጽሕፈት ቤቱ ሐሰተኛ ሰነዶችን በተለይም ደግሞ በመኖሪያ ቤት ካርታዎች ዘንድ የሚታየውን በሚመለከት ሲያስረዱ ከስድስት ወር ወዲህ በሚመለከተው አካል ማረጋገጫ እንደሚያስፈልግ እና በካርታው ጀርባ ላይ ማኅትተም መኖሩን በማረጋገጥ አግልግሎት የሚሰጡ ሲሆን ትንሽ የሚያጠራጥሩ እና ትክክለኛነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ሁኔታዎች ሲፈተሩ ግን በስልክ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ትክክለኛነታቸውን ለማረጋገጥ ሙከራ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ከሐሰተኛ ሰነዶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በርካታ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሚገኙ በተለይም ከአዲስ አበባ ፖሊስ የሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በተለይም ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመኖሪያ ቤቶች የባለቤትነት እና በመሬት የይዞታ ካርታ ጋር በተያያዘ በርካታ የማጭበርበር ተግባራት እንደሚከወኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘንድ ሲዘገብ መቆየቱም ይታወሳል።
ከዚህም በተጨማሪ በሐሰተኛ መታወቂያ እና ሐሰተኛ የገንዘብ ቼክ በተመለከተ ከግል እና ከመንግሥት የንግድ ባንኮች በርካታ ገንዘቦችን እንደተመዘበሩ እና ይህም በባንኮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያደርሱ ለማወቅ ተችሏል።
የኢፌዴሪ ሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ ጽሕፈት ቤት በኮቪድ 19 ምክንያት አቋርጨዋለሁ ያለውን ተንቀሳቃሽ ያልሆኑ ንብረቶችን በሚመለከት ያቋረጠውን አገልግሎት በቅርቡ የወረርሽኙን ስርጭት ታሳቢ አድርጎ ሊያስጀምረው እንደሚችልም ጠቁሟል።

ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here