በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ጀሞ ኹለት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው ለሚሰሩ ሰዎች በተሰጠ የገበያ መአከል ካሉት የንግድ ሱቆች ላይ ሙሉ በሙሉ ዝርፊያ መፈጸሙ ተገለጸ። በዘጠኝ የሚሆኑ ሱቆች ላይ ደግሞ የእሳት ቃጠሎ ጉዳት ደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን የገበያ ማዕከል በመባል የሚታወቀው የገበያ ማዕከል በስሩ 142 የሚሆኑ የንግድ ሱቆች ያሉት ሲሆን የንግድ ቤቶች ባለቤቶች ለ አዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ማክሰኞ 23/2012 በተነሳው ግርግር ምክንያት አጠቃላይ ንብረታቸው እንደተዘረፈ እናም የተቀሩት በእሳት እንደተቃሉ ገልፀዋል፡፡
ይህም ችግር በተፈፀመበት ዕለት ማክሰኞ 23/2012 ሲሆን በሰአተቱ የነበሩ ፖሊሶች ብናሳውቃቸውም እራሳችሁን አትርፉ ( እናም ወደ ቤታችሁ ሂዱ) ከማለት በቀር ምንም አይነት እርዳታ አላደረጉልንም ነበር በማለት ተናግረዋል፡፡
በቦታው ላይ የሚሰሩት ነጋዴዎች እንደሚሉት ከሆነ ድርጊቱን ፈጻሚዎች እንደማያውቋቸው እና ነገር ግን ጠዋት ሱቅ ለመክፈት ስንመጣ አደጋው ደርሶ ጠበቀን ብለዋል፡፡ ከዛም በተጨማሪም በቦታው ላይ አደጋውን ያደረሱት ሰዎች ማንነታቸውን ለማወቅ አልቻልንም ያሉት ነጋዴዎች ፤ነገር ግን ተመልሰው በመምጣት ከቃጠሎው ውድመት የተረፈውን ንብረት ወስደውብናል በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ከዛም በተጨማሪ ንብረት የወደመባቸው ነጋዴዎች የንግድ ቦታውን የሰሩላቸው የቀድሞው ቀዳማይት እመቤት አዜብ መስፍን እንደሰሩት እና ‹‹ እነርሱም የደሃ ደሃ ተብለው ቦታው እንደተሰጣቸው›› ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ተደጋጋሚ ጥቃት እና ጥፋት በቦታው ላይ እንደሚደርስ የሚገልፁት ነጋዴዎች አሁን ላይ ምን እንደምናደርግ ጭንቀት ላይ ነን ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ስጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጎዳይ ጋር በተያያዘ ጉዳቱ በተፈፀመበት ሰአት የፀጥታ አካላት በአካባቢው ነበሩ ወይ ምን አይነትስ እርምጃ ተወሰደ፣ ጉዳዩን ለማብረድ ምን ተደረገ የሚለውን ሰበታ ከተማ 04 ክፍለ ከተማ 3 ፖሊስ ጣቢያ ደውላ አዲስ ማለዳ እንዳጣራችው ከማክሰኞ ጀምሮ መረጋጋት እንደሌለ እና እንደታዘቡት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ጀሞ ኹለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር እንደሚገኝ እና መረጃ በእነርሱ በኩል እደሚወጣ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጉዳይ ጋረ በተያያዘ ስለ ጉዳዩ ምን እንደነበር እና እንዴት እንደተከተ አጠቃላይ መረጃ ለመጠየቅ አዲስ ማላዳ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስን ለማግኘት ብትጥርም ሳይሳካላት ቀርቷል፡፡ ነገር ግን አዲስ ማለዳ ከስፍራው ባገኘችው መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው የኦሮሚያ ፖሊስ ደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ሱቆች ሲዘረፉ እና ሲቃጠሉ ዳር ቆመው ከማየት በዘለለ ያደረጉት ምንም አይነት እርዳታ አለመኖሩን ጠቁመዋል።
የአርቲስ ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በአዲስ አበባ አብዛኛው አካባቢዎች በርካታ ጉዳቶች የደረሱ ሲሆን የሕንጻዎች መስታውቶች ተሰባብረዋል፣ ተሸከርካሪዎች መሰባበር እና የመቃጠል አደጋዎች እንደደረሰባቸው አዲስ አበባ ፖሊስ ማስታወቁ ሚታወስ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በርካታ ግለሰቦች በተፈጠረው ችግር ምክንያት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውም የሚታወስ ነው። ከሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተጠርጥረውም የቀርሞው አክቲቪስት እና በኦሮሞ ወጣቶች ዘንድ ተቀበይነት እንዳላቸው የሚነገርለት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባል ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን እስር ተከትሎም በአዲስ አበባ በተለያዩ ሰፈሮች የተደራጁ ቡድኖች ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም አዲስ ማለዳ ለመታዘብ ችላለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 87 ሠኔ 27 2012


