ይህ አባባል በሳምንቱ በርካቶች በማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኃን በተለይም ፌስ ቡክ ገጾች በብዛት የተጋራ ነው።
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 6/2011 መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ በረከት ስምዖን የመነሻ ጽሑፍ ካቀረቡ በኋላ አስተያት የተሰጠው የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አምዶም ገብረሥላሴ ሲሆን በፌስቡክ ተጠቃሚዎች በኩል ብዙ አድናቆትን ሲቸረው ሰንብቷል።
‹‹ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ናቸው የሚለው ሕወሓት ነው›› በሚልና ሌሎች ትችቶችን ሲያቀርብ የነበረው አምዶም አቦይ ስብሃት ነጋን ጨምሮ በአዳራሹ የነበረው ተሳታፊ ሐሳቡን እንዳይጨርስ በጭብጨባ አናጥበውታል።
ከመድረክ በኩል ሐሳቡን ይጨርስ የሚል መማጸኛ ቢጠየቅም ጭብጨባው አልተቋረጠም። አምዶም ‹‹ስብሰባው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ እንጂ የሕወሓት አይደለም ሐሳቤን ልጨርስ›› ብሎ ቢማጸንም ሊቋረጥ ባልቻለው የእነ አቦይ ስብሃትና ሌሎች ሰዎች ጭብጨባ ታውኮ ሐሳቡን ሳይቋጭ ቀርቷል።
ይህን የተመለከቱ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ‹‹የሕወሓት አባላት እንዴት ለጥቂት ደቂቃ ሐሳብ ማድመጥ ይሳናቸዋል?›› በሚል ሲተቹ ሰንብተዋል። ‹‹ሕወሓት ለሐሳብ ብዝኃነት ቦታ እንደሌለው ሳይጠየቅ እየተናገረ ነው ወይ?›› የሚሉ አስተያየቶችም በብዛት ተሰንዝረዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011