የመሐመድ ሐሰንን (ዶ/ር) ‘ማለት የምፈልገው’ በሚል ርዕስ በግል ተሞክሮ ላይ ተመሥርቶ የኢትየጵያን ታሪካዊ ተቃርኖዎች የሚተነትን መጽሐፍ ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) አንብቦ በአጭሩ እነሆ ቅምሻ ይለናል።
የመፅሐፉ ርዕስ፦ ማለት የምፈልገው
ደራሲ፦ መሐመድ ሐሰን (ዶ/ር)
አሳታሚ፦ ታሪክ አሳታሚ
የታተመበት መዘን፦ 2011
የሰው ልጅ ትናንትን እያጣቀሰ ነገን እያለመ ዛሬን የሚኖር ፍጡር ነው። ሰው የትናንትን ሰፊ ሁለንተናዊ ኹነት ከሳይንስ ሰባተኛ ሰማይ ወይም ከጥበብ አርያም ላይ ቆሞ ሳይሆን ከብዙ ሰበዝ ከተሰፋ የግል የማንነት ሙዳይ ላይ ሆኖ ስለ ትናንቱም ሆነ ስለ ዛሬው ዓለም ሊነግረን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ከግል ማንነት ሙዳይ ተነስቶ የሚደረግ የኋልዮሽ ተምኔታዊ እና ሊቃዊ ጉዞ (Retrospective imagination) ለዛሬ የፖለቲካ ጨዋታ ትርክት ለመቀመርም እንጂ ለታሪክ ቀጥተኛ ግብዓት ላይሆን ይችላል። ሰው ትናንትን የሚጎበኘው የዛሬን ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጥንተ ነገር ለመተንተን የሚያስችል ቀመር፣ ንድፈ ሐሳብ ወይም ሕግ ፍለጋ ይሆናል።
ከግል የሕይወት ልምድ እየቀዱ ውስብስቡን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከሚመረምሩ ማስታወሻዎች መካከል ‘ማለት የምፈልገው’ በሚል ርዕስ በቅርቡ ለአንባቢ የቀረበው መጽሐፍ አንዱ ነው። መጽሐፉ ታሪክን እንደ ፖለቲካ መተነንተኛ ተንተርሶ ንድፈ ሐሳብ መቀመሪያ ጥሬ ዕቃ ያደርገዋል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውጣ ውረድን ዋና ዋና ሕገ ምክንያቶች ያስሳል። በተመረጡ ሕገ ምክንያቶች ኃይል ታሪኩ እንሚዞር የሚያስረዳ ቀመርና ንድፈ ሐሳብ ይገነባል። በገነባው ንድፈ ሐሳብም ከጥንት እስከ ዛሬ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ ይተነትናል።
‘ማለት የምፈልገው’ በሃያ ስድስት አጫጭር ምዕራፎች የተደራጀ ባለ 333 ገጽ መፅሐፍ ነው። ርዕሱ ማለት የምፈልገው እንደሚያስረዳው በንግግር ተግባቦት ላይ የተመሠረተ ድርሰት ነው። ደራሲው መናገር ወይም ማለት የሚፈልገውን ከግል የሕይወት ተሞክሮ እየቀዳ ያሰናዳው ድርሰት ነው። ‘ማለት የምፈልገው’ በሰዎች ንግግር መካከል አፅንዖት በመስጠት ሊነገር የተዘጋጀን ሐሳብ ቀድሞ የሚመጣ አድማጭን የሚያነቃቃ ሐረግ ነው። ሐረጉ የእናንተ ሐሳብ እንዳለ ሁኖ የኔንም አድምጡኝ የሚል ትሁት መልዕክት ያዘለ ይመስላል። በዚህ ማስታወሻ ደራሲው በኢትዮጵያ ታሪክ የማያበቃ ትርክት እና ንግግር መሐል የእኔ ትረካ ይኸውና አድምጡኝ የሚል ይመስላል። ለዚህ ነው በመልዕክቱ “እኔ ደግሞ ታዋቂ ባልሆንም ማለት የምፈልገው አለኝ” ያለው።
‘ማለት የምፈልገው’ አራት ቅድመ ምዕራፎች ያሉት ሲሆን ከምስጋና፣ መታሰቢያነቱ፣ መልዕክቴን እና መግቢያ በሚሉት ርዕሶች አቀርቧል። መታሰቢያነቱ “ለአገራቸው መሻሻል መበልፀግ” ሙከራ ላደረጉ ሁሉ ተሰይሟል። ብዛት ያላቸው የአገር መሪዎች፣ አስተዳዳሪዎች፣ አርበኞች፣ ምሁራን ከዘመነ ምኒልክ እስከ ዘመነ አብዮት ብሎም በቅርብ ጊዜ በእስር ስለተሰቃዩ የነጻነት ተሟጋቾች ሁሉ መታሰቢያ ሆኖ ቀርቧል። መጽሐፉ የያዘው ፖለቲካዊ ጥንተ ነገሮች ለተማሪዎች እና ለወዳጅ ሲቀርቡ የነበሩ ሐሳቦች ሆነው ለሰፊው አንባቢ እንዲሆኑ ተደርገው ቀርበውበታል። ደራሲው እንዳለው በእነርሱ ፊት ‘ማለት የምፈልገው’ ብያለሁ። አሁን ደግሞ በሌላ ጊዜና ቦታ ስል የነበረውን በመጽሐፍት መልክ ‘ማለት የምፈልገው’ ብዬ አቅርቤአለሁ ነው የሚለን።
ይህ መጽሐፍ የ“ያ ትውልድ” ያልተለመደ የትህትና ድምፅ ነው። የዛን ትውልድ ስህተት እና ጥንካሬ ለመመስከር ተብሎ የተጻፈ ማስታወሻ ነው። በተለይም የዛ ትውልድ ስህተት እንዳይደገም ለተከታዩ ትውልድ የቀረበ ስጦታ ነው። “ያ ትውልድ” ስህተቱን ነቅሶ የማስተማር ኃላፊነት እንዳለበት ይገፃል። በተጨማሪም እንደ አገር “ወደ ተሻለ ሁኔታ” ልንራመድ ያልቻልነውና ወደፊት እንድንራመድ ባለንበት ቆመን ወደኋላ እንዲጎትተን ያደረገን ምንድን ነው? የሚል ዐቢይ ጥያቄም አንስቷል።
በምዕራፍ አምስት ባልተለመደ ሁኔታ ከጥንት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ የታሪክ ኹነቶች ከዓለም ዐበይት ክስተቶች ጋር በጊዜ ተዋረድ በንፅፅር አቀርቧል። ይህ ንፅፅር ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ አሁኑ ሕዝባዊ እምቢተኝነት በኢትዮጵያ ድረስ በአጭር ቀርቧል። ከላይ ለተጠቀሰው የፖለቲካ እንቆቅልሽ የኋልዮሽ ጉዞ ሁለት ዋና አዕማድ እንደ ሕገ ምክንያት አቅርቦ በየምዕራፍ የሁለቱን አዕማድ ሚና ይተነትናል። ብሔራዊ አገረ መንግሥት ግንባታ፣ የሥልጣን ሽግግር፣ የባሕር በር ጉዳይ፣ የኤርትራ ችግር፣ የሶማልያ ጉዳይ ፣ የፓርቲ ፖለቲካ፣ ምርጫ እና የመሪነት ጉዳዮች ሁሉ በመጽሐፉ ተዳስሰዋል።
ዐምደ ዕውቀት
የጠፋው የታሪክ ንቃተ ሕሊና እንደ ችግር
“የታሪክን ጉዞ ያልተገነዘበ
ሁሉንም ያደንቃል እያጨበጨበ
ብልህ ግን ያስተምራል አይደናበርም
መሔድ መመለሱን አይጠራጠርም”
መጽሐፉ ይህን ዐምድ ከላይ በተጠቀሰው የከበደ ሚካኤል ግጥም ተመሥርቶ ይተነትናል። የኢትዮጵያውያን ችግር ታሪክ ካለመረዳት ይመነጫል ይለናል። በተለይም “ያ ትውልድ” የከሸፈው በቂ የታሪክ ንቃተ ሕሊና ስላልነበረው ነው ብሎ ይሞግተናል። ታሪክ ካለማወቃችንም በላይ በተናጠል ለማረም መሞከራችን ዋነኛው የፖለቲካችን የችግርም ነው ይለናል። የታሪክ ግሉል እና የተነጠሉ ተራኪዎች እንጂ አቃፊ ትርክትም ሆነ የታሪክ ልቦና የለንም ይላል። ከታሪክ ተምረን ልዕለ ታሪካዊ ማኅበረሰብ በመሆን ፈንታ የታሪክ እስረኞች እና ምንዱባን እንደሆንን ይነግረናል። ዛሬ ላይ ቆመን ትናንትን ለማረም፣ ነገ ለመገዳደል ዝግጁ ሆነናል ይለናል። በዚህ ምክንያት ታሪክ ሐዘናዊ ገጹ በኢትዮጵያ ይደጋገማል። ይህ ትራጄዲ ሲደጋገም በሞኞች ላይ የተደረሰ ኮሚክ ይመስላል። ሁልጊዜ ያለፈው ምዕራፍ ላይ ደጋግመን ኖረን ደጋግመን የምንሞት አዲሱን ገጽ ላለመጀመር የተማማልን ይመስላል። ከታሪክ መማር ብንጀምር ዋናውን የፖለቲካ ሰንኮፍ መንቀል እንደምንችል ይመክረናል።
ዐምደ ፖለቲካ (የሃይማኖት)
የከሽፈው የብሔራዊ መንግሥት ግንባታ
እኛ ኢትዮጵያውያን “የሃይማኖት ጦርነት ውስጥ ገብተን ስንተላለቅ ኖረናል”። ይህ የታሪክ ዕዳ በአግባቡ ስልለታከመ የብሔራዊ መንግሥት ግንባታ እንደከሸፈ ዋናው ምክንያት ተደርጎ ቀርቧል። የተደበቀው ሃይማኖታዊ ቅራኔ ሳይታከም በመቅረቱ የፖለቲካችን ቁልቁል መውረድ ዋነኛ ምክንያት ነው ይለናል። ‘ማለት የምፈልገው’ የብሔራዊ መንግሥት ግንባታ ኢዲሞክራሲያዊነቱ፣ ጨቋኝነቱ እና አግላይነቱ በተለይም በሃይማኖትዊ አግላይነቱ ምክንያት በጅምር እንዲቀር ምክንያት እንደሆነ ያስረዳል።
በምዕራፍ አምስት የቀረበው የብሔራዊ መንግሥት ግንባታን ከእንግሊዝ፣ ከአሜሪካ፣ ከፈረንሳይ፣ ከጣልያን፣ ሩሲያ አንፃር በመተንተን በተለይም የሕንድን ስኬት እና የሶማሊያን ውድቀት በማሳየት የብሔራዊ አገር ግንባታ አንድ ዓይነት ቀመር እንደሌለው ያስረዳል። ሆኖም የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ በክርስቲያኖችም ቀመር የተመራ መሆኑ እናም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ከፖለቲካ ሒደቱ መገለልን ይተርካል። ይህም የአገሪቷ ፖለቲካ ዋና የችግር ጉዳይ እንደሆነ ያስረዳል። ይህንንም የልጅ ኢያሱ ሁሉን አቃፊ የፖሊሲ ሙከራዎች እና በሃይማኖት ትርክት የተገመደው የፖለቲካ ሴራ እንዴት እንዳከሸፈው እንደ ታሪካዊ ምሳሌ ቀርቧል። የሃይማኖት መድሎ የበኩር ልጅ የሆነው የጎሳ ፖለቲካ የኢያሱ ፖሊሲ እንዲከሽፍ የመደረጉ ዉጤት እንደሆነ በቁጭት ያስረዳል። በዘመነ ኢሕአዲግ ይህ ቁስል የመግዢያ መሣሪያ ቢሆንም የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት ተቋማት ቢደክሙም የሕዝብ በተለይም የሙስሊሙ እምቢተኝነት በአጭሩ ይዳሰሳል።
የዚህ ዐምድ ዋና አመክንዮ መሠረቱ “የሃይማኖት ጥያቄም እንደዚሁ በእኩልነት እና በመግባባት የተመሠረተ መፍትሔ ተገኝቷል ለማለት አያስደፍርም” የሚል ሐሳብ ነው። ይህ እንዳይሆን እና በታሪክ ላይ ሕዝቡ እንዳይስማማ እና ብሔራዊ አገረ መንግሥት ግንባታው እንዳይቀጥል ልዩነት (በተለይ ሃይማኖታዊ ልዩነት) የአምባገነን አገዛዝ መሣሪያ ሆኗል ይላል። ይህም የፖለቲካችን ኋላ ቀርነት ዋና መንስኤ ሆኖ ቀጥሏል ይለናል። በምዕራፍ 8 “ሁለቱ ሃይማኖቶች የአቤልና የቃየል ነገር” በሚል ርዕስ ከጥንት መሠረታቸው ጀምሮ የፍቅር እና የቅራኔ ቡራቡሬ ታሪክ አቅርቧል። የእኛና የእነሱ ፖለቲካ ብቸኛ ከሆነው ሃይማኖታዊ ምግብ እስከመለየት እንደሔደ ይተነትናል። አብረው ሳይሆን ተለያይተው እየበሉ እንዴት ነው መቀራረብና መቻቻል ሊመጣ የሚችለው? በማለት ይሟገታል። መቻቻል ካለስ ልዩነቱ እንዴት ሊሰፋ ቻለ ብሎ ይጠይቃል። የዚህ የልዩነት እና የማግለል ፖለቲካ ውጤት በልጅ ኢያሱ ዙሪያ ከተፈተለ ሴራ ደጋግሞ ይተርካል። ደራሲው ይህን አግላይ ፖለቲካ እና የምግብ ልዩነት ትርክት በራሱ በጻፈው እና በሜሪ አርምዴ ግጥም እንዲህ ብሎ ያፈርሰዋል።
“እስላም አረደ
ክርስቲያን አረደ
ጨጓራና ጉበት
ያም ስጋ ያም ስጋ በላሁ ምናለበት
እንዴት ይጣፍጣል የእስላም ቤት እንጀራ
በቅዳሜ በእሁድ በበዐል የተሠራ
ምግብህና ምግቤ አይመሳሰሉ
አንተም ለብቻህ እኔም ለብቻዬ እየተባባሉ
አለያዩትና ሰውን ሰው በሙሉ
ውሸት ሲናገሩ አንድ ነን ይላሉ
ማንም ማንን እንዳያምን እየተማማሉ
ሰውን አስጨረሱት እየተጋደሉ።”
መጽሐፉ ሁለቱ ሃይማኖቶች “በቅንነት የተጀመረ ወዳጅነት” በዐውደ ጦርነቶች የዘለቀ ግንኙነት በስተመጨረሻም ሁለቱም ተቋማዊ ጥንካሬያቸውን የተከታዮቻቸው ክብር የአገሪቱን ኅልውና መጠበቅ ተስኗቸው በዘመነ ኢሕአዲግ አገዛዝ ሥር እንዴት እንደ ወደቁ ይተርካል። ይህም የአገዛዙ ባሕርይ ላንዱ ዐቃፊ ለሌላው አግላይ ሆኖ ብሔራዊ መንግሥት ሳይኖር እንዲቆይ መደረጉን በምሳሌ በሥነ ግጥም አጅቦ አቅርቧል።
በነዚሁ ሁለት ንድፈ ሐሳባዊ አዕማድ (the political and the intellectual) በመጠቀም የኤርትራ እና የሶማሊያ፣ ባጠቃላያ ውስብስቡን የአፍሪካ ቀንድ እና የመካከለኛ ምሥራቅ ፖለቲካ እና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ይዳሰሳል። በተለይም ውስጣዊ የሃይማኖታዊ ልዩነቶች የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቶች ፖሊሲዎች እና ትግበራዎች ላይ ያስከተለውን ተፅዕኖ ይዳስሳል። በአንድ ወገን ኢሕአዲግ ለውጭ መንግሥታት በተለይ ለእንግሊዝና ግብፅ ያደረገው አጎብጅ ባሕርያት ያስከተለው ተፅዕኖ እስከ ባሕር በር ማሳጣት ድረስ ተንትኖታል። በዚህ ትረካ ለየት የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔሮች እና ሃያማኖቶች የአንድነት ፖለቲካ ዐፄ ምኒሊክ ከልጅ እያሱ ጋር እኩል መመስገናቸው ነው። በዘመናችን አደባባይ ፖለቲካ በምኒልክ ላይ ያለውን ትችትና ውግዘት ሁሉ ወደ ኃይለሥላሴ በማዞር “የራስ ተፈሪ ክዳት” እስከ ኃይለስላሴ አድሏዊ መንግሥት ግንባታ ይተርካል።
የኤርትራ ችግር በደጋው ክርስቲያን እና በቆለኛ ሙስሊም ማኅበረሰብ በተለይም የሙስሊሙ ከመንግሥት ግንባታ መገለል ከዜግነት ደረጃ ዝቅ መደረግ ዋነኛ መንስዔው እንደሆነ ይተነትናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ “የዓረብ ቅጥረኛ” ትርክት ሙስሊሙን ከመቅረብ የማራቅ ፖለቲካ ቀጣይ ውጤት ነው ብሎ ይሞገታል። ይህን ሲያደርግ የአረብ መንግሥታት በኢትዮጵያ ላይ የሚከተሉትን የውጪ ፖሊሲ እና የጂኦፖለቲካዊ ሁኔታ ከግምት አያስገባም። ሁሉም ችግር ከሁለቱ ሃይማኖቶች ግጭት እና ቅሬታ የሚመነጭ ያደርገዋል።
የሳሙኤል ሀንቲግተን የባሕል ወይም የሥልጣኔ ግጭት (clash of civilization) ትርክትን የተዋሰ ይመስላል። ተመሳሳይ ንድፈ ሐሳብ በመጠቀም የሶማሊያ ኢትዮጵያ ግንኙነት ይተነትናል። የሁለቱ ሃይማኖቶች ቅራኔ የልጅ እያሱ አቃፊ የውስጥ ፖሊሲ መንግሥት ግንባታ መክሸፍ የሶማሊያ ግንኙነት እንዲበላሽ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ቀርቧል። የእኛ (ክርስቲያን) የነርሱ (ሙስሊሞች) ፖለቲካ የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ እንቆቅልሽ ፈጥሯል ይለናል። ይህም ከዚያድባሬ እስከ ዘመነ አልሸባብ ድረስ ይዞን እንዴት እንደመጣ ይተነትናል። እንደ አገር ከተመሠረትንበት ዕድሜ አንፃር እሰካላሳለፍነው ታሪክ ሒደት ይህንን ከብዙ ዓመታት በፊት ተቀብለን መመለስ ይኖርብን ነበር በማለት በቁጭት ይገልጻል። ይህም የሆነው ጥሩ ከታሪክ የሚማር የታሪክ ንቃተ ሕሊና ያዳበረ ሕዝብ ስለልሆንን ነው ይለናል።
የግራ ዘመም ፖለቲካ እንደ አዲስ ሃይማኖት?
ከምዕራፍ 12-18 በቀዝቃዛው ጦርነት ሰማይ ሥር የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ፓርቲዎች ምሥረታ እና ክስመት በዝርዝር አቅርቧል። የግራ ዘመም አዲስ ግጭት ቅራኔ ፈጥሮ አገሪቱን ፖለቲካ እንዴት እንዳወሳሰበው እና ደም እንዳፈሰሰ ይተነትናል። “ያ ትውልድ” ከዓለም ዐቀፍ ዐውድ ጋር እንዴት እንደተፈጠረ ያሰማውን ዓለም ዐቀፋዊ ተራማጅ የነጻነት ድምፅ ይዘክራል። “ከዓለም የተራማጅ ኃያሎች ጎን ቆሟል” ይለናል። ለዚህ የሀገር ውስጥ የውጭ ሀገር ተማሪዎች ማኅበራት ሚና ባጭሩ አቅርቧል። ምንም እንኳን አንድ የግራ ዘመም ሃይማኖት ቢኖራቸው በውስጣቸው ከሐሣብ ልዩነት እስከ ትውልድ አስጨራሽ ጦርነት ውስጥ እንደገቡ ይተርካል።
ይህ ከመጽሐፉ ሁለተኛው ንድፈ ሐሳባዊ ዐምድ የተለየ ትንተና ነው። ታሪካዊው የሁለት ሃይማኖቶች ቅራኔ በሌላ አዲስ ዓይነት ተተክቶ የሃይማኖት ጉዳይ ሳይነሳም ቅራኔው በትክክል ሳይፈታ ታልፏል ይላል። ዋናው ጉዳይ የሃይማኖት ቅራኔ ሳይሆን በተማሪዎች ብሎም በተመሠረቱ ፓርቲዎች አወዛጋቢው ጉዳይ ሥልጣን እና ሥልጣን ብቻ ይሆናል። ከተማሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ደርግ እና ኢሕአዴግ የፖለቲካችን ዋናው ችግር በቂ የታሪክ ግንዛቤ አለመኖሩና የሥልጣን ስግብግብነቱ በጎ ነገር እንዳያስቡ ሕሊናቸውን ስላወረው ነው ይለናል።
‘ማለት የምፈልገው’ ከምዕራፍ 19-25 በዘመነ ኢሕአዴግ በዓለም ዐቀፍ ፀረ ኢትዮጵያ ሴራ ሥር የተከናወኑ ጉዳዮችን ይዳስሳል። ምርጫ 97፣ የትግራያ ነጻ አውጪ ድርጅት ቀድሞ ሠራዊት እና በተለይ ደግሞ ጄኔራል አማን አንዶም፣ ተፈሪ በንቲና አጥናፉ አባተ መስዋዕትነት የነሱ ሐሳብ ሳይተገበር የኤርትራን ችግር እንዴት እንዳወሳሰበ በግለሰቦች ሥነ ባሕርይ እና አመለካከት በመመርኮዝ ይተነትናል። በመጨረሻም በግጥም ሐሳቡን ያጠናክራል።
“አማንም ተጓዝ ወደ ማይቀረው ሞት
ተፈሪም ተጓዝ ወደማይቀረው ሞት
አጥናፉም ተጓዝ ወደማይቀረው ሞት
መሞት ይሻላል ከመሔድ ሽሽት
እንግዲህ ኢትዮጵያን ማን ይፈውሳት?”
ፈሪዎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች
በምዕራፍ 23 “የመሪዎች ፍርሐት መሠረቱ ምንድን ነው?” በሚል ርዕስ በተለይ “የሥልጣን ማጣቱ ስጋት” የአምባገነን መሪዎች ባሕርይ ነው ይላል። የመግደል፣ የማሰር አባዜ ከነዚህ ከመሪዎች ሥነ ልቦና ይመነጫል ይላል። ዐፄ ኃይለሥላሴ ኮሌኔል መንግሥቱ እና አቶ መለስ ፈሪዎች ነበሩ ብሎ ሌሎቹ መሪዎች እያሱን ዐፄ ምኒሊክ፣ ዐፄ ዮሓንስን፣ ዐፄ ቴዎድሮስን ጀግና ብሎ ይሞግታል። ከጀግኖቹ መካከል ሁለቱ ፍርሐትን በሞት ሲያሸንፉ፣ ዐፄ ምኒሊክ “ፍርሐትን በሥልጣን አስተለልፈው” በሕይወት እያሉ አሸንፈውታል በማለት አንባቢን ይሞግታሉ።
በማጠቃለያ ምዕራፍ በሁለቱ አዕማድ የረጅሙ የአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ በመዳሰስ “አዲስ ታሪክ እየተሠራ ነው” ወዳለው ወቅታዊ የፖለቲካ ለውጥ ጠቅሶ ያጠቃልላል። ዕውቀት በተለይም “ያሳለፍነውን ጥሩና መጥፎ ሂደቶች” መፍትሔ ነው ይለናል። መጽሐፉ ብዙ ሞጋቾች አከራካሪ ሐሳቦችን ይዞ የፖለቲካ እንቆቅልሾቻችንን ሊያሳየን ይሞክራል። መጽሐፉ ሲጀምር የደራሲው ከሙስሊም እና “ያ ትውልድ” ማንነት ግላዊ የሕይወት ገጽ ብዙ ተሞክሮ ያቀርባል የሚል ጉጉት ያሳድራል።
የደራሲው አጻጻፍ በግል ሕይወት ትርክት ቢቀምረውም ይዘቱ ግን ከግል ሕይወት ተሞክሮች፣ ዝርዝር ጉዳዮች ከውልደት ጀምሮ የሚያቀርብ ሳይሆን፣ በዚህ ሒደት ውስጥ ደራሲው በገቢር ወይም በኀልዮት፣ በነቢብ እና በምናብ ያየውን የሰማውን የፖለቲካ ትርዒት ተርኮልናል። ያልታከመው ሃይማኖታዊ የፖለቲካዊ ቅራኔ ከዘመናችን ገዢ የማንነት ፖለቲካ ጋር በሰምና ወርቅ መልክ አቅርቦልናል። በዚህ ጽሑፍ ደራሲው የነገረንን ይህን ያህል ካዳመጥን ብዙ የተነሱ አከራካሪ ጉዳዮችን እያጠበብን የፖለቲካ ታሪካችንን ችግሮች በጥልቀት መረዳታችንን እንቀጥላለን። ታሪክን በተረዳነው ቁጥር እንደ ሕዝብ ከታሪክ እስረኝነት ነፃ እንወጣለን ። ወደሚቀጥለው የታሪክ ገጽም እንጓዛለን።
ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011