ኮቪድ 19፣ የዜጎች ደኅንነት እና የዓባይ ውጥረት

0
1016

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ጉዳይ ማለትም የዓለም ዐቀፉን ወረርሽኝ፣ የሰላም እና መረጋጋት በዜጎች ላይ የሚያሳድረው ደኅንነት ዕጦት እና የዓለም ዐቀፉን ትኩረት በመሳብ ዓለም ወደ ኢትዮጵያ እንዲያማትር ያደረገውን የሕዳሴው ግድብ ውጥረት መነሻ ተደርጓል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በምን ዓይነት መንገድ መጣች፣ አሁን ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል፣ በቀጣይስ ከመንግሥት እና እንደ አገር ወይም ሕዝብ ምን ይጠበቃል የሚሉ ጉዳዮችም የዚህ ጽሑፍ ዋና ሐሳቦች ናቸው።
በሦስቱ ዓለም ዐቀፍ እና አገራዊ ጉዳዮችን በመመርኮዝም ውጥረቶች መነሻቸው፣ የሚያደርሱት አገራዊ ጉዳት እና መድረሻቸውን በሚመለከት የተለያዩ ዘርፎችን በከፍተኛ ባለሙያነት የሚመሩ የተለያዩ ግለሰቦችን በማናገር እና ሰፊ እንዲሁም ጠለቅ ያሉ ትንታኔዎችን በመሰብሰብ የአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ የዚህ ሳምንት የሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ አድርጎታል።

መንፈቅ ካለፈው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ጥቂት ጊዜያትን ወደ አሮጌው ዓመት መገባደጃ ሳብ አድርጎ ነበር በቻይናዋ ሁቤ ግዛት ውሃን ከተማ አሃዱ ያለው ኮሮና ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተከሰተው። በዉሃን ከተማ የተጀመረው ይኸው ወረርሽኝ ታዲያ በከባድ የሞት ሰይፍ ዓለምን ለማካለል ወራት ብቻ ነበር የበቁት። አየር፣ የብስ፣ ውሃ መጓጓዣዎች ለኮቪድ 19 ወሳኝ ከአገር አገር መጓጓዣ መንገዶቹ ሲሆኑ፤ የሰዎች አካላዊ ቅርርብ፣ ንክኪ እና ጥንቃቄ የጎደለው ማኅበራዊ መስተጋብር ደግሞ ፍጹም ምቹ ምህዳሩ እንደሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት በይፋ ሲለፍፍ መቆየቱም ይታወሳል።

በሀብት ማማ ላይ ተቀምጠው ልዕለ ኃያልነታቸውን በዓለም ኹሉ ላይ ሲያስተጋቡ የነበሩ እና በቴክኖሎጂ ምጥቀታቸው ቀሪውን ዓለም ሲያስደምሙ የነበሩ አገራት በኮቪድ 19 ሰይፍ ስር ወድቀው መዳኛ ለማግኘት የዓለምን ምስጢራ እየበረበሩ ይሄ ነው የሚባል መፍትሔ ሳያገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ዐይናቸው እያየ ወደ መቃብር ለመስደድ ተገደዋል፣ እየቀበሩም ይገኛሉ።

በተለያዩ አገራት ተስፋ ሰጪ የሆኑ የቤተ ሙከራ ግኝቶች እንዳሉ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ዘንድ ቢሰማም፤ ይህ ነው የሚባል ፍቱን መድኃኒት ማግኘት አሁንም የታላላቅ ቤተ ሙከራዎችን የሞሉት ተመራማሪዎች የዕለት ተዕለት የቤት ሥራ እና እንቅልፍ የሚነሳ ጉዳይ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል። ከመድኃኒት እና ፍቱን ፈውሶች ጋር ተያይዞም የተለያዩ አገራት የራሳቸውን ባህላዊ መድኃኒቶችን እና ፈዋሽ ዕጾችን በመጠቀም ጅምላ ጨራሽ ከሆነ ወረርሽኝ ራሳቸውን ለማዳን የሚያደርጉት ትንቅንቅም እንዳለ ማሰብ ያስፈልጋል።

ከቻይናዋ ውሃን እስከ ምድር ጫፍ ኒውዚላንድ ድረስ ወረርሽኙ ያልዳሰሰው የዓለም ክፍል የለም። ይሕ ዓለምን በወርዷ እና በቁመቷ ያካለለው ወረርሽኝ ታዲያ ዐስር ሚሊዮንን ለተሻገረው የተጠቂዎች ቁጥር እና ከግማሽ ሚሊዮን ለላቀው የሟቾች ቁጥር ምክንያት ነው። ከተወሰኑ አገራት በስተቀር በተለይም ደግሞ ወረርሽኙ ከተነሳበት የሩቅ ምሥራቅ አገራት ይልቅ በአውሮፓ እና አሜሪካ አገራት የተቀጠፈው የሕያዋን ነብስ ቁጥር ስፍር የለውም። ከእነዚህም ውስጥ የወረርሽኙ መነሻ የሆነችው ቻይና ወረርሽኙን ተቆጣጥራ ወደ ቀደመው ዕለት ተዕለት ተግባሯ በተመለሰችበት ወቅት ኢጣሊያ እና ስፔን ከአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ እንደ አህጉር እጅግ የከበደበት ጊዜ ላይ ነበር።

በየዕለቱ ለሚረግፈው የሰው ነብስ የሚቻላቸውን አድርገው መቀነስ ባለመቻላቸው መፍትሄው ከመለኮት ካልሆነ በቀር ምድር ላይ ያልተሞከረ ጉዳይ ላለመኖሩ የኢጣሊያው ጠቅላይ ሚኒስቴር ጁሴፔ ኮንቴ በተሰበረ አንደበት ሲናገሩም የተደመቱበት ጉዳይ ነበር።

ይህ ሁሉ ሲሆን ታዲያ ለወትሮው ደዌዎችን በቀጠና በመከፋፈል በምጣኔ ሀብት ያልጎለበቱ እና ፍጹም ድህነት ውስጥ ያሉ አገራትን የወረርሽበኞች ሁሉ ምንጭ፣ የደዌዎች ሁሉ መፍለቂያ በማድረግ ሲነገር፣ ሲለፈፍ አልፎ ተርፎም በስርዓተ ትምህርት ውስጥ በመካተት ስርጸቶች ሲከናወኑ ኖረዋል። ይህ በሆነበት ሁኔታም፤ ዓለምን ያስጨነቀው ይኸው ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅትም አፍሪካን በዋናነት በመጥቀስ ወረርሽኙ ከፍተኛ የሆነ እልቂት ሊያስከትል እንደሚችል ሲተነበይ እና ሲተነተን ቆይቷል።

የዓለም ጤና ድርጅትም በዚህ በኩል ሰፋ ያለ ትንታኔ በመስጠት አፍሪካ ውስጥ የሚያሳድረው የጤና እክል ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር እና በመመርኮዝ በአህጉሩ ላይ የሚኖረው ሁኔታ እጅግ እንደሚከፋም ትንበያዎች ተቀምጠው ነበር። ተንታኞች የተነሱበት አመክንዮ እና ድምዳሚያቸው በብዙዎች ዘንድ ትርጉም የሚሰጥ እንደሆነ ቢታመንም ቅሉ የነባራዊ ሁኔታው ጉዳይ ግን ከዚህ የተለየ ለመሆኑ እማኝ ለማምጣት የሚያሻ ጉዳይ አይደለም።

አንድ ወረርሽኝ በዋናነት ከኢቦላ ውጪ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ መነሻቸው ከአፍሪካ ውጭ ሲሆን ነገር ግን በዓለም የጤና ድርጅት የወረርሽኞች ስርጭት ውስጥ አፍሪካን ሙሉ በሙሉ በማካተት የበሽታው ተጠቂ እና የብዙ በሽተኞች መገኛ ተደርጎ መሳል አንደኛው ጉዳይ ነው። ለዚህም ደግሞ ከአራት ዓመታ በፊት ከወደ ደቡብ አሜሪካ ተነሳ የተባለው እና አዲስ የተወለዱ ሕጻናትን በስፋት ያጠቃል ስለተባለው የዚካ ቫይረስ በትንሹም ቢሆን ማንሳት ይቻላል።

ጉዳዩ ከደቡብ አሜሪካዊቷ አገር ብራዚል ወደ ታላቋ አሜሪካ በመሄድ ወላዶችን ሲያስጨንቅ የነበረው ዚካ በዓለም ጤና ድርጅት ዘንድ የበሽታው ስርጭት ከወደ አፍሪካ የበረታ ይሆናል በሚል አፍሪካን ካርታ በቀይ ቀለም በማቅለም የአደገኛ ቀጠና በማድረግ ሲያስተጋባ ከቆየ በኋላ እና ከአፍሪካ ወደ አሜሪካ የሚደረጉ በረራዎችን በተመለከተ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ እና የጤና ምርመራዎችም እንዲጠናከሩ ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ዚካ ቫይረስ ከአሜሪካ እና ደቡብ አሜሪካ አገራት አልፎ አልፎም ከካሪቢያን የደሴት አገራት የዘለለ ለመከሰት ሳይችል በክትባት እህል ውሃው ተቋርጧል።

የኮቪድ 19 ጉዳይ እና ኢትዮጵያ
ዓለምን አሸብሮ በድህረ ወቀትም ከባድ የሆነ የአስተሳሰብ እንዲሁም የኃይል ሚዛን በዓለም ላይ ይፈጥራል የተባለው ወረርሽኝ ቀድሞም እምብዛም ለማያወላዳው የኢትዮጵያ የጤና ስርዓት ላይ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚሆን በርካቶች በአንድ ድምጽ የሚስማሙበት ጉዳይ እንደሆነ ዋል አደር ብሏል። በጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን፣ በምጣኔ ኃብቱም ሆነ በማኅበራዊ ዘርፉ ከፍተኛ እንዲሁም በፖለቲካውም ጎራ ቀላል የማይባል ውጥንቅጥ እንዳስከተለ በየዕለቱ የምንመለከተው ጉዳይ ነው።

በጎንደር ዩኒቨርስቲ የጤና ሳይንስ የትምህርት ክፍል ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሽታየ ዓለሙ (ፕ/ር) ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ በቋፍ ላይ ለነበረው የጤና ስርዓት ይህ ወረርሽኝ ጭራሽ ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚወስደው ይናገራሉ። በተለይም ደግሞ የጤና ተቋማት እና የጤና ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ ለሕዝብ በማይዳረሱበት ሁኔታ ይህ ወረርሽኝ በአገር ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ለመፍጠሩ የማሻማ ጉዳይ እንደሆነም ይጨምራሉ። ከዚህም ጋር ተያይዞ በአደጉት አገራት እንኳን በበቂ ሁኔታ የሕክምና አገልግሎት በወረርሽኙ ለተጠቁ ዜጎቻቸው ማዳረስ ሳይችሉ ቀርተው በርካታ ዜጎቻቸውን እያጡ እንደሆነ የሚናገሩት ሽታየ፤ ሌሎች ተዛማጅ እና ትሮፒካል በሽታዎች መገኛ ከሚባሉት አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያም ኮቪድ ከሌሎች ተጨማሪ በሽታዎች ጋር ሲደመር የገዳይነት ደረጃው እጅግ ከፍ ስለሚል ጫናውም በዛው ልክ እንደሚጨምር ያስረዳሉ

‹‹ክረምት ሲገባ በአገር ደረጃ ተያይዘው የሚመጡ ወቅትን መሰረት ያደረጉ በሽታዎች ለመኖራቸው ኹላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው። በዚህም ምክንያት መንግስት ከዚህ ቀደም ባሉት ነባራዊ ሁኔታዎችም ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ በክረምት ወቅት ለሚከሰቱ በሽታዎችም ሆነ ወረርሽኞች ቅድመ ዝግጅት ያደርጋል።ይሁን እንጂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎም ቢሆን መደረስ የሚቻለው ውስን ስፍራዎችን እና ተጠቂዎችን ስለሚሆን ቁጥሩ ቀላል የማይባ ሰው በክረምት ወቅት በበሽታዎች ተጠቅቶ እንዲያልፍ ወይም በከባድ ሁኔታ እንደሚያገግም የሚታወቅ ነው›› ሲሉ ያስረዳሉ።
ሽታየ ቀጥለውም በመንግስት ደረጃ በየዓመቱ ከፍተኛ ጫና እንደሚደረግ እና እንደ አገርም ወጪው እና ውጥረቱ ከፍ እንደሚልና ይህ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ደግሞ ጫናው በተለያዩ ዘርፎች እንደሚታይ እና ጫናውንም ለማቃለል ቀላል የማይባል ወጪ ስለሚጠይቅ እንደ አገር ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንገኛለን ሲሉ ያትታሉ።

በተመሳሳይ በብሩክ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት እና ሐኪም የሆኑት ዶክተር ብሩክ አለማየሁ ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ፤ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ኤችአይቪን ጨምሮ ከባባድ በሽታዎች በሕዝቡ ዘንድ ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ ሁሉን አቀፍ ተጽዕኖ ሲያደርሱ መቆየታቸውን ጠቅሰው ከዚህም ባለፈ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ይኸው ወረርሽ ደግሞ እንደ አገር ተደራቢ ችግር ስለሚፈጥር ጉዳዩን ከባድ ያደርገዋል ሲሉም ይናገራሉ። ከዚህም ባለፈ እንደ ዶክተር ብሩክ ሀሳብ ከተላላፊ በሽታዎች ውጪም ተላላፊ ባልሆኑ እና አስም እና መሰል የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቁ በሽታዎች ኮቪድ 19 በመጣ ጊዜ ገዳይነታቸው ስለሚጨምር ጫናውም ከፍ ይጨምራል ይላሉ።

የቀድሞው የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ሚንስትር የነበሩት ዶክተር አሚር አማን በኃላፊነት ላይ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት በአስር ዓመታ ውስጥ 62 ቢሊዮን ብር እንደምታጣ መናገራቸው የሚታወስ ነው። ከተላላፊ በሽታዎች በተጓዳኝ የኮሮና ወረርሽኝም በመንግስት እና አገር ላይ ሚያሳድረው ጫናም ይህ ነው የሚባል አይደለም። ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግስት ከኅብረተሰቡ ሀብት የማሰባሰብ እና ወረርሽኙ ከባድ ተጽዕኖ ሳያሳድር መከላከል የሚቻልበት ጉዳይን ለመፍጠር እየተሰራ እንደሚገኝም የሚታወቅ ነው። ይህ ከምጣኔ ሀብት እነጻርም በአገር እና መንግስት ላይ ትልቅ ሆነ ድቀትን ለመፍጠር ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።

በተለይም ደግሞ ኮቪድ 19 ወደ ኢትዮጵያ ከገባ እና የምርመራ አቅም ውስን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጥቂት የሚባሉ ቁጥሮች ይፋ በሚሆኑበት ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ እንዲቆም የሚቀሰቅሱ እንቅስቃሴዎች እና ጥያቄዎች እንደነበሩም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በሰኔ 30/2012 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ጠቅሰው ነበር። ይሁን እንጂ እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገለጻ እንደ አገር ከባድ የሆኑ ተጽዕኖዎች ማጋጠማቸውን እና የተባለው የእንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ማቆም ግን እንደ አገር ኢትዮጵያ የምትችልበት ደረጃ ላይ እንዳልደረሰች አስረድተው፤ ሌሎች አገራትም የኢትዮጵያን ከፊል እና የተወሰኑ እንቅስቃሴዎችን በማገድ እርምጃ በመጠቀም ወረርሽኙን የመግታት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ያስረዱበት አጋጣሚ አለ።

በአገር አቀፍ ደረጃ ይህ እንቅስቃሴ እንደተባለው ተፈጻሚ ሆኖ ቢሆን ኖሮ በኮቪድ 19 ምክንያት ከሚሞተው ይልቅ በእንቅስቃሴ መገታት ምክንያት ሳይሰሩ በቤት ውስጥ እንዲቀመጡ በሚደረገው ውሳኔ ወቅት በምግብ ዕጥረት እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገለጻ ‹‹በዳቦ ዕጦት›› የሚሞተው ይበዛ እንደነበር አስቀምጠዋል።

ኮሮና ወደ አገር ውስጥ ከገባ እና አለም አቀፍም ሆነ አገር አቀፍ እንቅስቃሴዎች ከመገደባቸው ጋር ተያይዞ ቀላል የማይባል ጫና በምጣኔ ኃብቱ እና በማኅበራዊ መስተጋብሩም ላይ ለመኖሩ የማይታበል ሀቅ ነው። የምጣኔ ሀብት ምሑሩ አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ ‹‹እንደ ኢትዮጵያ ላሉ እና አብዛኛው ሕዝብ በዕለት ገቢ የሚኖር ሕዝብ ላላቸው አገራት ወረርሽኙ ከባድ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው›› ሲሉ ይጀምራሉ።

ይህንንም መሰረት አድርገው መንግሥት ይህን ጉዳይ ለማስተካከል ከፍተኛ ሆነ ውሳኔዎችን እና የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎችን ማድረጉ እንደማይቀር እና ተገቢም እንደሆነ ይጠቁማሉ። በተፈጠረው መንግስትን እና አገርን ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ከከተተው የጤና ዕክል ለመውጣት መንግስት የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ከፍተኛ እንደሆኑ እና በሌላ ተጓዳኝ ምክንያቶች ደግሞ ውጥረት ውስጥ በመግባቱ እንደ መንግስት ቅድሚያ ሚሰጣቸው ጉዳዮች ስለሚኖሩ የምጣኔ ሀብቱ ጉዳይ ትንሽ ሊዘገይ የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል ሲሉ አጥላው ለአዲስ ማለዳ ይናገራሉ።

የአጥላውን ሀሳብ የሚያጠናክረውም አዲስ ማለዳ ኮቪድ 19 በኢትዮጵያ ከተገኘበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ስፍዎች በመዘዋወር ለመታዘብ እንደሞከረችው ቀደም ሲል የነበሩት የንግድ እንቅስቃሴዎች በአንድ አዳር መቀዛቀዛቸው እና አንድን የንግድ ዘርፍ ተያይዞ በቀን ሰራተኝነት የተሰማሩ ሰዎችም ከባድ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ለመታዘብ ተችሏል። መንግስት በተለያዩ ዘርፎች ለተሰማሩ ሴክተሮች በርካታ የብድር እና የዕዳ መክፈያ ጊዜ በማራዘም ድጋፎች ቢያደርግም በሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ የሚገኙት ግን ሰራተኞቻቸውን በመቀነስ እና ደሞዛቸውን በመከልከል ለከፋ ጉዳት እየዳረጉ እንደሚገኙ መንግስትም በዘዚህ በኩል ትኩረት በመንፈጉ ከፍተኛ የሆነ ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ እንደ አገር ሊገባ እንደሚችልም አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ከዚህ ቀደም በተሰሩት የዜና ዕወጃዎቿ ዘርፉ ምሑራኖችን በመጥቀስ ስታስጋባ መቆየቷም የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ ከጤናው እና ከምጣኔ ሀብቱ ዘርፍ ባለፈም በፖለቲካው እና በማኅበራዊ ዘርፉም ከባድ ችግሮች በኮቪድ ምክንያት ለመከሰታቸው ሕያው ምስክር ነች። በዚህ የአገር እና የመንግስትን ውጥረት ከአንድ ወገን እያባባሰ የሚገኘው እና ኮቪድ ካመጣው ከፍተኛ ግጥምጥሞሽ ደግሞ የአገር አቀፍ ምርጫ የመካሔዱ ጉዳይ እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት መዛመት ጉዳይ ሰኔ እና ሰኞ የሆነበት ጉዳይ በመንግስት በኩል እንደሆነበት ይታያል።በተፈጠረው ወረርሽኝ እና ወረርሽኙም ወደ ኅብረተሰቡ ዘንድ በመግባቱ ምርጫ ለማካሄድ ማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ተከትሎ ከተለያዩ ወገን በስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ በመንቀፍ እና የመንግስት አካሔድ አምባገነናዊ ነው እስከማለት የተደረሰበት እና አገርንም በተጨማሪ ውጥረት ውስጥ ከከተቱ የኮሮና ውስጥ አገራዊ ጉዳዮች እንደሆኑ ለመታዘብ ተችሏል።

ይህንንም ተከትሎ አገራዊ ምርጫው በተያዘለት ቀነ ገደብ ማለትም ነሐሴ 10/2012 ካልተካሔደ አሁን ያለው መንግስት በቀጣዩ ዓመት መስከረም 30/2013 ላይ ሕጋዊነቱ በይፋ እንደሚያከትምም በቅርቡ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሔደበት የሚገኘው ጃዋር መሐመድ እና ፖለቲከኛው ልደቱ አያሌው በይፋ ሲናገሩም ተስተውሏል። ይህም አገርን በውጥረት ውስጥ ለማስገባት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እንደማያንሱም በፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አጥኚ ቡድን አባል የሆኑት ሱራፌል መኮንን ለአዲስ ማለዳ ይገልጻሉ።

ሱራፌል ሲናገሩ በኢትዮጵያ በተለይም ደግሞ ለውጥ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ውጥረቶች ቅርጻቸውን እቀያየሩ ሲገለጡ እንደነበርም ይናገራሉ። ሆኖም ይህ በሆነበት እና አንዱ ችግር ሲፈታ ሌሎች ሲጨመሩ እዚህ የደረሰው የለውጥ መንግስት አገር እያስተዳደሩ ያለበት የውዥንብር ወቅት ኮሮና ሲከሰት ደግሞ ይባሱኑ ችግሩን እንዲግል እንዳደረገው ያስረዳሉ።

በተገለጸው እና ምርጫን በሚመለከት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ሲናገሩ እንደ አደጉት አገራት ኢትዮጵያ በዚህ የወረርሽኝ ወቅት ምርጫ ማካሔድ የማትችልበትን ጉዳይም ይፋ አድርገዋል። በዚህም መሰረት ሲናገሩ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት ሕዝብን እንደ አደጉት አገራት በመታወቂያ ወይም በማኅበራዊ ደኅንነት ቁጥር የሚያውቅበት ደረጃ ላይ ባለመሆኑ ምርጫን በሌሎች አገራት እንደታየው በኢንተርኔት በመታገዝ ማካሔድ እና ከአካላዊ ንክኪ የራቀ አካሔዶችን ማድረግ አይቻልም›› ሲሉም አስረድተዋል። በመሆኑም ጠቅላይ ሚንስትሩ በተደጋጋሚ ከምርጫ ወዲህ የሚደረጉ ጉዳዮች በሚመለከትም ስልጣን መያዝ እንደማይቻል እና ከምርጫ ውጪ የሆኑ እንቅስቃሴዎችም አገር አፍራሽ እና ወንጀልም መሆናቸውን ጠቁመው አልፈዋል።

የዜጎች ደኅንነት
በአንድ አገር ውስጥ የመንግስት ህልውና በሚገባ የሚረጋገጠው ለዜጎቹ በሚያረጋግጠው የደኅንነት እና ሰላማዊ የአኗኗር ሒደት እንደሆነ በርካቶች ይስማሙበታል። በኢትዮጵያ ደግሞ ከጅማሬው ጀምሮ ዕክል ያልተለየው የለውጡ አመራር በርካታ ዜጎች ለደኅንነታቸው ዋስትና አጥተው በሰቀቀን እንደሚኖሩም የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል። እየተገባደደ ባለው ዓመት መጀመሪያ ወደ ምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ተንቀሳቅሳ የነበረችው አዲስ ማለዳ በአካል ለመታዘብ እንደሞከረችው ዜጎች በከፍተኛ ፍረሀት እና ‹‹ነገ ምን ይፈጠር ይሆን›› በሚል ጭንቀት ውስጥ ለመግባታቸው ሕያው ምስክር ለመሆን ችላ ነበር።

በተለይም ደግሞ የያኔው አክቲቪስት በኋላ ላይ ደግሞ ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ ‹ተከብቢያለሁ እና ድረሱልኝ›› በሚል በአንድ አዳር በርካቶችን ከጎኑ ባሰለፈበት ጥሪ ከፍተኛ የዜጎች መፈናቀል እና ጉዳት የደረሰው ድሬዳዋ እና አካባቢው እንደሆነ የሚታወስ ነው። ከኹነቱ ቀናትን አሳልፋ ድሬዳዋ እና ኹለቱን የሐረርጌ ዞኖች የተገኘችው አዲስ ማለዳ በርካታ በደኅንነት ስጋት ውስጥ የነበሩ ሶወችን በአካልም ሆነ በርቀት ለመታዘብ ችላለች።

ሱራፌል እዚህ ላይ የሚያስረዱት ነገር ቢኖር፤ ‹‹የለውጡ አመራር ተረጋግቶ እንዳይመራ እና አገር በስጋት ውስጥ ውላ በጭንቀት ውስጥ እንድታድር ምክንያት የሆነው የዜጎች የደኅንነት ችግር አንዱ ነው። ይህ ደግሞ በክልል ከተሞች እና ዞኖች ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ውስጥ ስርቆት እና ግድያዎች መበራከታቸው እና ሕዝብ ይህን ተከትሎ ለንብረቱ እና ለሕይወቱ መስጋቱ ራሱን ቻለ አገርን ወደ አንድ ወገን በመጎተት ውጥረት ውስጥ ለመክተት የሚችል ጉዳይ ነው›› ሲሉ ያስረዳሉ። ከዚህም ባለፈ በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽል ያወጣውን ሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተም ሱራፌል ሀሳባቸውን ሲገልጹ፤ በተለያዩ ምክንያቶች መንግስት ሕግን ማስከበር እና የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ ባቻለበት ሁኔታ አገርን ውጥረት ውስጥ ለሚከቱ ሕገ ወጥ ድርጊቶች በር እንደከፈተም አስታውሰዋል።

በተለያዩ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች እና መገናኛ ብዙኃን በኩል አገርን እና ሕዝብን በቅራኔ የሚሞሉ ትንታኔዎች ሲተላለፉ ማየት የተለመዱ የድርጊቶች ለመሆናቸው ሱራፌል ይስማሙበታል። ከዚህም በመነሳት አገር በተለያዩ አበይት ርዕሰ ጉዳዮች በተወጠረችበት ወቅት እነዚህ እና መሰል ቅስቀሳዎች ሲተላለፉ እና ወደ ሕዝብ ሲደርሱ ከሚመለከተው አካል በኩል የሚደረገው ግብረ መልስ መቀዛቀዙ ውጥረቱን እንዲጨምር እንዳደረገው ማሳያ እንደሆነም ሀሳባቸውን ያስተላልፋሉ።

ዜጎች ደኅንነት በሕይወት ብቻም አይደለም በተለያዩ ጊዜያት በመኖሪያ አካባቢዎች የሚደረጉ በተለይም ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለው የመሬት ወረራም ለውጥረቱ እና እንደ አገር እና እንደ ሕዝብ መተማመንን በመሸርሸር መልካም ሆነ መስተጋብር በሕዝብ መካከል እንዳይኖር የሚያደርግ ለአገር መፍረስ ትልቅ ድርሻ ያለው ጉዳይ እንደሆነም ይታወቃል። አዲስ ማለዳ በበርካታ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በመሔድም በሕገ ወጥ መንገድ ስለታጠሩ እና ወደ ሦስተኛ ወገን በሽያጭ ስለተላለፉ መሬቶች በስፋት መዘገቧ የሚታወስ ነው። በዚህ የጥንቅር እንቅስቃሴም ወቅት በርካታ ቅሬታ አቅራቢዎች የአረንጓዴ ስፍራቸው ማንነታቸው በማይታወቁ ሰዎች እንደታጠረባቸው እና ወደ ሚመለከተው አካል አቤት ለማለት በሚሔዱበትም ወቅት ተገቢ የሆነ ምላሽ ሳያገኙ እንደቀሩም ያስረዱበት ጉዳይ መኖሩን ይናገራሉ።

የዓባይ ጉዳይ
ኢትዮጵያን እንደ አገር በሦስተኛው አቅጣጫ እየጎተተ አገራዊ ውጥረቱን ከውጭ እየመራ የሚገኘው የሕዳሴው ግድብ ግንባታ አንደኛው እና ዋነኛው ነው። በወንዙ ባለቤት ኢትዮጰያ እና በትልልቅ ውሃ ባለድርሻ አካላት ሱዳን እና ግብጽ መካከልም ለረጅም ጊዜያት የነበረው ጉንጭ አልፋ ውይይት ያለ መቋጫ ማብቃቱ ራሱን የቻለ ውጥረት አጀንዳ መፍጠሪያ እንደሆነም ይጠቀሳል።
የዓባይ ጉዳይ እንደ ሱራፌል ገለጻ ከባድ የሆነ የውጥረት ምንጭ እንደሆነ እና ውጥረቱም በአገር ውስጥ ያለውን አለመግባባት እና ፖለቲካ ቅራኔን በመጠቀም የሚተገበር ስለሚሆን ደግሞ ከኹሉም የበለጠው ኢትዮጵያን የሚወጥር ጉዳይ እንደሆነም ይጠቅሳሉ። ከሦስቱ የተፋሰስ አገራት በዋናነት ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ በዕጅ አዙር በመግባት የብጥብጥ እና የውዥንብር አጀንዳዎችን በአገር ውስጥ በመፍጠር የአገር ውስጥ ውጥረቱ ጠንክሮ የአባይ ጉዳይ የኢትዮጵያ ራስ ምታ ብቻ ሆኖ ግድቡ ግንባታ ባለበት እንዲቆም የማድረግ ጉዳይ እንደሆነም ይጠቁማሉ።

ኢትዮጵያ ከዚህ ባለፈም በቅርቡ የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ እዚህም እዛም ኮሽ በማለት አገረ መንግስቱ እንዳይረጋ እና ሕዝብም አሻግሮ ያየውን የተሸለ ነገ እንዳይኖር በተለያዩ ውጥረቶች ውስጥ በመክተት በአዙሪት ውስጥ እንዲኖር የማድረግ ሒደት እንደሆነ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ይናገራሉ። ይህን እና መሰል ጉዳዮችን በሚመለከትም የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ድምጻዊውን ግድያ በተመለከተ ሐዘናቸውን ገልጸው ሲያበቁ የግድያው ሐሳብ ግን ተራ ግድያ ያልሆነ እና አገርን እና ሕዝብ ወደ ውጥረት በመክተት መረጋጋት የራቃት እና ከዕድገት ግስጋሴ የተዳከመች ደካማ አገርን መገንባት እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከሕዝቡ የዕለት ተዕለት መስተጋብሩ ባለፈም በአገር ደረጃ የበይነ መረብ ጥቃቶች ምናልባትም አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም እንዳስነበበችው በአራተኛው የውጊያ ሜዳ ግድቡን በሚመለከት ውጥንቅጡ የወጣ የመንግስት አቋም አገር እና ሕዝብ አስተባብሮ አገራዊ እና ግዙፉን ግድብ ይገነባል ተብሎ ስለማይታሰብ እንደሆነም ሀሳባቸውን ያስረግጣሉ። ይህ በይነ መረብ ጥቃቶች ታዲያ አዲስ ማለዳ ባለፉት ዕትሟ ለመጥቀስ እንደሞከረችው ውጥረቱን በእንድ አቅጣጫዎ ብቻ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ እና በርከት ባሉ እና አመቺ እና ክፍት በሆኑ አጋጣሚዎች ኹሉ በመጠቀም ውጥረቱን ማጠንከር የሚመስል ስትራቴጂ እና አካሔዶች ለመሆናቸውም ሙሑራን ይስማሙበታል። በተለይም ደግሞ ድምጻዊውን የገደሉ ሰዎች ማንነታቸው በግልጽ ባልታወቀበት በዛ ቅጽበት ሌሊቱን ሙሉ በተመረጡ ብሔሮች ላይ ተቃጣው ጥቃት ከግድያው ጀርባ ማን እንዳለ ማሳያ እንደሆነም ያስረዳሉ።

ዘጠኝ ዓመታትን በግንባታ ላይ ያሳለፈው የሕዳሴው ግድብ የውሃ ሙሊትን በሚመለከት በርካታ መረጃዎች ሲስተጋቡ እና ሲዘዋወሩ መኖራቸውን ተከትሎ በግድቡ ዙሪያም በርካታ ውጥረቶች ከቀን ወደ ቀን እየጨመሩ ለመምጣታቸውም ይታወቃል። ይህም ደግሞ በግብጽ በኩል በአገሪቱ የደኅንነት አካላት የሚዘወሩት ሚዲያዎች የሚያሰራጩት የሐሰት መረጃዎች ወደ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከእውታው ቀድመው ስለሚደርሱ በኢትዮጵያ ውስጥም ከከባድ የሆነ የስነ ልቦና ጫና እንደሚያሳድሩ በኅዳሴው ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያን በመወከል በበርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘንድ በመቅረብ የሚሟገተው መሐመድ አል አሩሲ ይናገራል።

‹‹በአገር ውስጥ ያለው ውጥረት በሚገባ በግብጽ በኩል ይፈለጋል። ምክንያቱ ደግሞ ግድቡ ዋነኛ የግንባታ ምንጭ ከኢትዮጵያ ከሕዝብ ኪስ በመሆኑ በሕዝቡ ዘንድ ተስፋ የመቁረጥ እና የግድቡ ጉዳይ በግብጽ በላይነት ስር እንዳለ ከተሰማ ግንባታው በአንድ ጊዜ ይቆማል የሚል አካሔድ ነው የሚከተሉት›› ሲል ለአዲስ ማለዳ ያስረዳል። በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ በያዘችው ቀነ ገደብ መሰረት ግድቡን በውሃ የመሙላት መርሃ ግብሩ ሐምሌ 4/2012 በመሆኑ እና ቀኑም እየደረሰ መምጣቱን ተከትሎ በአገር ውስጥ የውጥረቱ እና ውዥንብሩ መጠን ከቀን ወደ ቀን እየጠነከረ መምጣቱም በተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ ስራ ኃላፊዎች የሚነሳ ጉዳይ ነው።

የዓባይ ጉዳይ ኢትዮጵያ ጉዳይ ብቻ እንደሆነ እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን አደራዳሪ እንጂ ውሳኔ ሰጪ አካላት ሊገቡበት የማይችሉ ኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት መሆኑን የሚገልጹት መሐመድ ነገር ግን በአገር ውስጥ ተዛቡ መረጃዎች እየተሰራጩ በሕዝቡ ዘንድ ውጥረት እንዳይከሰት መንግስት በየጊዜው ወደ ሕዝብ በመቅረብ ትክክለኛ እና ጠቃሚ መረጃዎችን ቢያደርስ የሚል ሀሳብ እንዳለውም አልሸሸገም። በከፍተኛ የኢትዮጵያ ዝናባማ ወራት ሐምሌ እና ነሐሴ ውሃ ሙሊቱ እንደሚከናወን የሚታወቀው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ እንደሚባለው በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት በተደረገው መሪዎች ውይይት ወቅት ለውሃ ሙሊቱ ተቆረጠው ቀን በሳምንታት እንዳልተገፋ እና የተደረገው ውይይትም ከዚህ ጋር ሚገናኝ እንዳልሆነም ሕዝብ እንዲገነዘበው ከመንግስት በኩል ለሕዝብ ተላልፏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here