የድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ አካባቢ ሰላማዊ ሰልፍ የሚመስሉ እንቅስቃሴዎች መስተዋላቸውን ተከትሎ ‹‹ምንም ዓይነት ሰልፍ ማድረግ አይቻልም›› ሲል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ማንኛውንም ሰልፍ በምንም መልኩ የተፈቀደ አለመሆኑን እና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት አስቸኳይ ጊዜ መታወጁንና አዋጁ ማናቸውም ዓይነት ሰልፍን የሚከለክል መሆኑን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጄላን አብዲ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ጄላን አክለውም ፖሊስ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎችን በቦታው ፈጥኖ በመድረስ እየመከተ መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ሰኔ 28/2012 ከለገጣፎ እስከ አያት ባሉት የከተማዋ አካባቢዎች አዲስ ማለዳ የተደራጁ አካላት የተለያዩ ሐሳቦችን በመግለጽ ወደ አደባባይ በመውጣት ንብረት የማውደም እና ሰላማዊ እንቅስቃሴን ለማወክ የሚመስል ክስተት ታዝባለች። ይህን ተከትሎም በመዲናይቱ አዲስ አበባ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ኅብረተሰቡ ስጋት እንዳለበት እና በመደራጀት ሌሊት ሌሊት አካባቢውን እየጠበቀ መሆኑን ከትዝብቷ ተረድታለች።
ሕዝቡ እንደዚህ አይነት ሰልፎችን እና የተደራጁ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት በፍጥነት ለፖሊስ ማሳወቅ እንዳለበት የገለጹት ጄላን፣ ፖሊስ ከምንጊዜውም በላይ የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። ፖሊስ ከተማዋን ለመጠበቅ በተለያዩ ቦታዎች በተሽከርካሪ እየተንቀሳቀሱ እና በተጠንቀቅ ቆሞ እየጠበቀ መሆኑንም የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በከተማዋ ሕዝቡን ለማደናገር የተለያዩ አደናጋሪ የሐሰት ወሬዎች እንደሚሰራጩ የገለጹት ጄላን፣ እንደምሳሌነት ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ከተማው የሚገባው ውሃ ተበክሏል በማለት ሕዝቡን ስጋት ውስጥ ለመክተት የተሞከረውን የሐሰት ማሸበር ተግባር አስታውሰዋል። ሕዝቡ እንዲህ አይነት ወሬዎችን ሲሰማ ከመሸበር ይልቅ ጉዳዩን ወደ 987 እና 991 በመደወል የሆነውን ነገር አስረድቶ መረጃውን ማረጋገጥና ፖሊስ ጉዳዩን እንዲከታተለው ማሳሰብ ይገባል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገለጸዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አክለውም በከተማዋ ሕዝቡ በሐሰተኛ ወሬ እንዳይሸበር ማሳሰቢያ መሰጠቱን ጠቁመው፣ እንዲህ አይነቱን ከነባራዊ ሁኔታው የራቀ እና ሐሰተኛ ወሬ የሚያሰራጩት ሕዝቡን በሐሰት ለማሸበር ነው ብለዋል። ኃላፊው አክለውም ፖሊስ ለማንኛውም ነገር በማንኛውም ጊዜ ሕዝቡን ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም የፌዴራል ፖሊስ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር በአሁኑ ጊዜ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ጀላን አመላክተዋል።
በከተማዋ ሕዝቡን በሐሰተኛ ወሬ ለማሸበር እና ለማደናገር የሚደረጉ ሥራዎችን ሕዝቡ ለፖሊስ መጠቆም እንዳለበት የተናገሩት ጀላን፣ አክለውም ሐሰተኛ ወሬ ማሰራጨት በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንደሚያደርግ እና እያሰራጩ የሚገኙ ሰዎችም በሕግ እንደሚጠየቁ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ሰበብ በማድረግ በከተማዋ ግር ግር ለመፍጠር ሙከራ ያደረጉ እንዲሁም ችግር ለመፍጠር ጉዳዩን ያቀነባበሩ ከአንድ ሺሕ በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ኮሚሽኑ መግለጹ የሚታወስ ነው።
የኮሚሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንደሚሉት፣ በአዲሰ አበባ ችግር ለመፍጠር እና ሕዝቡን ለማሸበር የሚንቀሳቀሱ አካላትን ኮሚሽኑ በጥብቅ ክትትል በሕግ ቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑን ጠቁመዋል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ ሐሰተኛ ውዥንብሮችን የሚፈጥሩ አካላትን ኅብረተሰቡ መጠቆምና የውሸት አጀንዳዎችን ከመቀበል እንዲቆጠብ ሲሉ አሳስበዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)በተለይ ከሀጫሉ ግድያ ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ግጭት የሚፈጥሩ ሰዎችን በረብሻ ድል አታመጡም ሲሉ ሰኔ 29/2012 በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ተደምጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እንደማይሳካላቸው እና ኢትዮጵያ እንደ ሶሪያ እና ሊብያ ብትሆን የሚጠቀም ኃይል የለም ብለዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012



