በሠኔ ወር የቡና ምርት ከሁሉም ምርቶች ከፍተኛ ዋጋ በመሸፈን ቀዳሚ ሆነ

0
1220

የቡና ምርት ከሁሉም ምርቶች ከፍተኛ ዋጋ በመሸፈን ቀዳሚ መሆኑ ሠኔን ወር ተንተርሶ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባወጣው ሪፖርት ላይ የተመላከተ ሲሆን፣ 44 በመቶ የሚሆነው በመጠን 66 በመቶ ዋጋ በመሸፈን ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በመጠን የ6 በመቶ፣ በዋጋ 7 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተመላክቷል። ይህ የቡና ግብይት በተመሳሳይ ሁኔታ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በመጠን 5 በመቶ በዋጋ ደግሞ 33 በመቶ መጨመሩ ተገልጿል።
በተያያዘም በወሩ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ 18.037 ቶን ያልታጠበ ቡና በ1.46 ቢሊዮን ብር እና 419 ቶን ያልታጠበ ቡና በ53 ሚሊዮን ብር እና 2665 ቶን ስፔሻሊስት ቡና በ411 ሚሊዮን ብር ግብይታቸው ተፈፅሟልም ተብሏል።
ተቋሙ በሪፖርቱ ላይ እንዳመላከተው ከሆነ በ22 የግብይት ቀናት 27.332 ቶን ቡና፣ 21.943 ቶን ሰሊጥ፣ 7.846 ቶን ማሾ፣ 3.922 ቶን ቦሎቄና 1.499 ቶን አኩሪ አተር ግብይት የተፈፀመ ሲሆን፣ የምርት አቅርቦቱም ጨምሯል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪ ከቡና ባሻገር በሌሎች ምርቶችም ላይም የግብይት ሁኔታው መጨመሩ የተገለፀ ሲሆን፤ በዚሁ ጊዜ ውስጥ 21.943 ቶን ሰሊጥ በ944 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በመጠን 40 በመቶ በዋጋ 39 ከፍ ብሏል።
ከአጠቃላይ ግብይቱም 35 በመቶ መጠን 25 በመቶ ዋጋ ድርሻ የሚይዝ መሆኑን እና፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን 281 በመቶ ዋጋ 168 በመቶ ጨምሯል።
የአረንጓዴ ማሾ ግብይትም ካለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር በሦስት እጥፍ ማደግ መቻሉ የተገለፀ ሲሆን፣ 7.846 ቶን አርንጓዴ ማሾ በ228 ሚሊዮን ብር ማገበያቱ ነው የተገለፀው። ከዛም በተጨማሪ በሠኔ ወር 2668 ቶን ነጭ ቦሎቄና 1254 ቶን ቀይ ቦሎቄ እንዲሁም 1254 ቶን ቀይ ቦሎቄ በ88 ሚሊዮን ብር የተገበያየ ሲሆን፣ ካለፈው ወር በመጠን 8 በመቶ፣ በዋጋ 9 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ነው የተመላከተው።
በዚሁም ካለፈው ዓመትም ተመሳሳይ ወቅት ጋር በመጠን 127 በመቶ፣ በዋጋ ደግሞ 148 በመቶ ማደጉ ተጠቅሷል።በተያያዘም በወሩ 1499 ቶን አኩሪ አተርም በ19 ሚሊዮን ብር ግብይቱ ተፈፅሟል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያው የውጭ ንግዱን በዘላቂነት እንዲቀጥል በማሰብ እና ሌሎች ችግሮችንም ለማቃለል የዘመናዊ ግብይትት ስርአት በመተግበሩ ምክንያት በሠኔ ወር 2012 ዓመት 62.542 ቶን ምርት በ3.72 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱን ገልፀዋል።
ወደ ሁሉም የምርት ገበያው ቅርንጫፎች በዚህ ወር የገባው የምርት መጠን ከ60 ሺሕ ቶን በላይ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ቡና 46 በመቶ ድርሻ አለው። ከቀደመው የግንቦት ወር አቅርቦት ጋር ሲተያይ ወደ ምርት ገበያው የመጣው ቡናና ሰሊጥ በተመሳሳይ በ19 በመቶ ከፍ ሲል፣ በተለይ የሰሊጥ አቅርቦት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር በሦስት እጥፍ መጨመሩም የሠኔን ወር ተንተርሶ የወጣው ሪፖርት አመላክቷል።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here