በአዲስ አበባ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል የ6 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

0
445

በግል የንግድ ዘርፍ ፣ በመንግስት እና በመንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መካከል የተመሰረተው ጥምረት እንዳስታወቀው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ከፍተኛ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ለሚቀጥሉት ቀጣይ ወራት የሚሰራ እና እስከ 6 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሊኖረው የሚችል `ጤናችን በእጃችን` የተሰኘው ፕሮጀክት ይፋ ተደርጓል።
ዳልበርግ ግሩፕ እና ሮሃ ግሩፕ ተነሳሽነት በመውሰድ በሀገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የወረርሽኝ የመከላከል ብሔራዊ ምላሽ ላይ ዘላቂ ተፅእኖ ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የግል እና የመንግስት ተቋማት በጋራ በማደራጀት ወደ ስራ ገብተዋል።
ፕሮጀክቱ የውሃ ፣ የሳሙና እና ሌሎች ቁሳቁሶች ላይ እጥረት የሚያጋጥማችውን እና በጣም ጥቅጥቅ ያሉ የመኖሪያ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎችን ለማገዝ ብሎም ራሳቸውን ከወረርሽኙ እንዲጠብቁ የሚያስችል ይሆናል ተብሏል።
የፕሮጀክቱ የሙከራ ጊዜ የሚያስፈልገው 1 ሚሊዮን ዶላር በሮሃ ግሩፕ በኩል የተገኘ ሲሆን ቀሪው 5 ሚሊዮን ዶላር ከለጋሽ ድርጅቶች ፣ የግሉ ዘርፍ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚሰበሰብ ይሆናል ነው የተባለው።
መንግሥት በበኩሉ በፋይናንስ ሚኒስቴር በኩል ለፕሮጀክቱ የሚመረቱ ዕቃዎች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስን ያነሳ ሲሆን ፕሮጀክቱ እስካሁን ድረስ 15 የሚሆኑ አገር በቀል በማምረቻ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ አነጋግሯል። ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ሴቭ ዘ ችልድረን በጎ አድራጊ ድርጅት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነትም ተፈራርሟል::
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት ውስጥ ብሎክን መሰረት ያደረገ የማህበረሰብ አደረጃጀት ኤጀንሲ በከተማው ውስጥ የሚገኙ 24ሺ 934 አካባቢዎችን በመለየት የሚገኙበትን ጊዜያዊ ሁኔታ መረጃ ሰብስቦ አዘጋጅቷል።
በተጨማሪም በ10 ክፍለ ከተማዎች የሚገኙ 121 ወረዳዎች ውስጥ 1ሺ 357 የተደራጁ ማእከላትን በመጠቀም የፊት ጭንብሎችን እና ሳሙናዎችን ለከፍተኛ ተጋላጭ ተብለው ለተለዩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚያከፋፍል ይሆናልም ተብሏል።
በተጨማሪም ሴቭ ዘ ችልድረን ለጥምረቱ የቴክኒክ ድጋፍ ፣ መመሪያ እና የህብረተሰቡ ተሳትፎን በተመለከተ ድጋፍ ይሰጣል።
የሚሰራጨው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፀደቁ የእጅ መታጠብ ፣ የፊት ጭንብል መልበስ እና አካላዊ ርቀት መጠበቅን የሚመለከቱ መልዕክቶችን ያካትታል ፡፡
የሰራተኞቹን እና የህብረተሰብ አካላትን ጤና እና ደህንነት ለመጠበቅ ከ260 በላይ የክፍለ ከተማና የወረዳ ቡድን አመራሮችም ስልጠና እንደተሰጣቸው ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 90 ሐምሌ 18 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here