‹‹ዓላማዬ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሠላም መፍጠር ነው››

0
588

‹‹ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዳግም አንድ አገር ይሆናሉ የሚል ግምት ባይኖረኝም ሁለቱ አገራት ጥሩ ጎረቤታሞች የማይሆኑበት ምክንያት አይታየኝም›› ነበር ያሉት በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈው የቀድሞው የኢ.ፌ.ደ.ሪ. ፕሬዘደንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፤ የአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ከሆነችው ‹‹ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው›› ጋር አምስት ዓመታት በፊት በሰጡት ቃለ ምልልስ፡፡ የቀድሞ ፕሬዝደንት አክለውም ‹‹ተመሳሳይ ባህልን የሚጋሩት የእነኚህ አገራት ወንድም ሕዝቦች በአንድ መንግሥት ስር እንኳን ባይሆኑ ጥብቅ ጎረቤታሞች ሆነው መኖር እንዳለባቸው አምናለሁ›› ብለዋል፡፡
ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የደርግ መንግሥት በ1970ዎቹ መጀመሪያ የኤርትራ ጉዳይ በሠላማዊ መንገድ ሊፈታ ይችላል ብሎ ባቋቋመው ኮሚሽን ውስጥ ምክትል ኮሚሽር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ኮሚሽኑን ወክሎ ወደ ኤርትራ የተጓዘው ልዑክ አባልም ነበሩ፡፡ በደርግ መንግሥት የማይጨበጥ ባሕሪ እና አቋም ምክንያት የኮሚሽኑ ሥራ ውጤት እንዳላመጣ የተናገሩት ግርማ ‹‹የሕዝብ ድርጅት›› የሚል ተቋም ተቋቁሞ የነበረ ቢሆንም ከሙከራ ውጭ የተለየ ውጤት ሊያመጣ እንዳልቻለም አክለዋል፡፡
‹‹ንጉሱ ፌዴሬሽኑን ባያፈርሱት ኖሮ የኤርትራ ጉዳይ እዚህ ደረጃ አይደርስም ነበር›› ሲሉ በቁጭት የተናገሩት ግርማ በዚህ ምክንያት ብዙ ኤርትራዊያን ወደ ትጥቅ ትግል ሊገቡ እንደቻሉም አስታውሰዋል።ቃለ መጠይቁን ባደረጉበት ወቅት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሻሻል ጅምር ሒደቶች እንደነበሩ ያልደበቁት ግርማ ‹‹በቀረኝ እድሜ በሁለቱ አገራት መካከል ሠላም እንዲወርድ የተቻለኝን ጥረት ሁሉ አደርጋለሁ፤ ዓላማዬ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሠላም መፍጠር ነው›› ብለውም ነበር።
ከወራት በፊት የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ላይ ሠላም መውረዱ የግርማ ወልደ ጊዮርጊስን ሕልም ዕውን ቢያረገውም የሠላሙን ቀጣይ ፍሬ ሳያዩ እና ሳያጣጣሙ ሞት ቀድሟቸዋል። ግርማ ወልደጊዮርጊስ አርብ፣ ታኅሣሥ 5/2011 ለቅዳሜ አጥቢያ ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 10/2011 ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ዲፕሎማቶች በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል የቀብር ሥነ ስርዓታቸው መፈፀሙ ይታወሳል፡፡ የቀድሞው ፕሬዘዳት ለሥራ ባላቸው ቀናነትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ባበረከቱት አስተዋጽኦ በርካቶች ሲያደንቋቸው ይሰማል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here