የ3 ሰዎችን ሕይወት ያጠፋ ግለሰብ ላይ የ7 ወር እስራት መወሰኑ እያወዛገበ ነው

0
363

በአዳማ የሦስት ሰዎችን ሕይወት ያጠፋ ግለሰብ ላይ የሰባት ወር የእስር ቅጣት ውሳኔ መተላለፉ ሲያወዛግብ፣ በአዲስ አበባ አንድ የሴት ጫማን ያለደረሰኝ በ180 ብር የሸጠ ግለሰብ ላይ አንድ ዓመት ጽኑ እስራት መበየኑ እያነጋገረ ነው።
በአዳማ ነሐሴ 8/2010 ያለመንጃ ፈቃድ አይሱዙ መኪና እያሸከረከረ ልጃቸውን ከግንብ ጋር አጋጭቶ እንደገደለባቸው የሚናገሩት የሟች እናት “መኪናውን እንዲያሽከረክር አሳልፎ የሰጠው ሾፌር አብሮ ጋቢና ላይ ተቀምጦ ነበር” ብለዋል። ከእሳቸው ልጅ ጋር የሦስት ሰዎች ሕይወት ያጠፋው ግለሰብ በሰባት ወር እስራት እንዲቀጣ ማድረግ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
መኪናውን አሳልፎ የሰጠው ሾፌር በስድስት ዓመት ሲቀጣ አደጋውን ያደረሰው ግለሰብ በሰባት ወር እስራት መቅጣት በአገሪቱ ፍትሕ የለም የሚያስብል እንደሆነም ቅሬታ ስለማሰማታቸው የመገናኘ ብዙኃን ዘግበዋል።
ጥፋቱ ከአምስት እስከ 15 ዓመት ፅኑ እስራት ቢያስቀምጥም ሰባት ወራት እንዲቀጣ መደረጉ ተገቢነት እንደሌለው የሚጠቅሱ የሕግ ባለሙያዎችም ውሳኔውን ተቃውመዋል።
የተሰጠው ውሳኔ የፍትሕ አሰጣጥ ስርዓትን ያጎደፈ በመሆኑ ለኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ እንደተጠየቀም ተሰምቷል።
በሌላ ዜና ነሐሴ 10/2009 በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ሾላ ገበያ አንድ የሴት ጫማ በ180 ብር ሸጦ ደረሰኝ ያልቆረጠ ነጋዴ ላይ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ተኛ የወንጀል ችሎት የአንድ ዓመት ፅኑ እስራት መበየኑን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 6 ታኅሣሥ 13 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here