በአማራ ክልል 1244 የሕግ ታራሚዎች በይቅርታ ተፈቱ

0
1173

በአማራ ክልል በተለያዩ ወንጀሎች ተሳትፈው በፍርድ ቤት ቅጣታቸው የተበየነባቸው እና በማረሚያ ቤት የነበሩ 1ሽሕ 244 የሕግ ታራሚዎች በይቅርታ መፈታታቸው ታውቋል።
የክልሉ አቃቤ ሕግ ህዝብ ግንኙነት ጉዳዮች ኃላፊ አለምሸት ምህረቴ እንደገለጹት የህግ ታራሚዎቹ በይቅርታ የተለቀቁት ከሐምሌ 21/2012 ጀምሮ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይቅርታ የተደረላቸውም በመደበኛው የይቅርታ አዋጅ ቁጥር 136/1998 መሰረት እና በልዩ ይቅርታ ቦርድ ጉዳያቸው ተጣርቶ የቀረቡ እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል። የዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከልም ዕድሜያቸው የገፋ፣ የጤና ችግር ያለባቸው፣ አንድ ሶስተኛውን እስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁና የባህሪ ለውጥ ያመጡ ይገኙበታል።
በይቅርታ ከተለቀቁት ውስጥ 22 ሴቶች መሆናቸውንም አመልክተዋል። በሙስና ፣ በጠለፋና አስገድዶ መድፈር ወንጀል የተፈረደባቸው በይቅርታው አለመካተታቸውን ነው ኃላፊው ያሰረዱት።
ይቅርታ የተደረገላቸው የህግ ታራሚዎች ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ የበደሉትን ህዝብ በልማት ለመካስ ጠንክረው መስራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ደግሞ የክልሉ ይቅርታ ቦርድ ጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አምባው አስረስ ናቸው። ህብረተሰቡም በጥፋታቸው የተፀፀቱና ታርመው የተለቀቁ መሆኑን ተገንዝቦ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሊደግፋቸውና ሊያግዛቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።
በክልሉ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በመጋቢት ወር 2012 መንግስት በልዩ ሁኔታ ባደረገው ይቅርታ ከ7 ሺህ የሚበልጡ የህግ ታራሚዎች እንዲለቀቁ መደረጉ ይታወሳል።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here