በኮንሶና በአሌ አካባቢ በተፈጠረ የጸጥታ ችግር የ21 ሰዎች ሕይወት አለፈ

0
517

በመሬት ይገባኛል ጥያቄ የተነሳ በኮንሶና በአሌ ማህበረሰብ መካከል በተፈጠረ ግጭት የ21 ሰዎች ህይወት ማለፉን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው ገለጹ።
በደቡብ ክልል በኮንሶና በአሌ ማህበረሰብ መካከል በመሬት ይገባኛል ምክንያት በተነሳው የጸጥታ ችግር የ21 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች መፈናቀላቸውንና የንበረት ውድመት መድረሱን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በተፈጠረው ግጭት ለተከሰተው የሰው ህይወት መጥፋት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል:: ከዚህ በፊት በኮንሶና አሌ ማህበረሰብ መካከል መሰል ግጭት ተከስቶ እንደማያውቅ የተናገሩት አቶ ርስቱ የግጭቱ መንስኤ የመሬት ይገባኛል እንደሆነ ገልጸዋል።
ያልተገባ ወሬ በማናፈስ በህዝቦች መካከል ጸብ በመፍጠር የግል ጥቅም ለማግኘት የሚጥሩ ግለሰቦችም ችግሩ እንዲባባስና ጉዳቱ የከፋ እንዲሆን አፍራሽ ተግባር መፈፀማቸውን ጠቁመዋል።
በተፈጠረው ችግር ከጠፋው የሰው ህወት ባሻገር በርካቶች ለአካል ጉዳትና ለመፈናቀል የተዳረጉ ሲሆን የመኖሪያ ቤቶች ቃጠሎና የንብረት ውድመት መድረሱንም አብራርተዋል።
የክልሉ መንግስት ባደረገው ጥረት አካባቢው ወደቀደመ ሠላሙ መመለሱንና የደረሰውን ጉዳት የሚያጠና ቡድን መቋቋሙን ገልፀው ለተፈናቃዮቹም የቀለብና የአልባሳት ድጋፍ ለማድረግ እተሰራ ይገኛል ብለዋል ።
ከጸጥታ ችግሩ ጋር በተያያዘ እጃቸው ያስገቡ አካላት የመለየት ስራ እየተከናወነ ሲሆን ሁለት አመራሮችን ጨምሮ ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል ።
የህዘብን ሠላም ለማናጋትና ክልሉ እንዳይረጋጋ ከጠላት ተልዕኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ አካላት በተለይ በአመራር ደረጃ ያሉ ግለሰቦች ከእንዲህ ዓይነት ችግር እጃቸውን እንዲያወጡ ለማድረግ አቅጣጫ መቀመጡንም አቶ ረስቱ አያይዘው ገልፀዋል ።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here