በ10 ዓመታት ውስጥ 261 ጋዜጣና መጽሔቶች ከኅትመት ውጭ ሆነዋል

0
667

ከየካቲት ወር 2001 እስከ ኅዳር 2011 ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ 288 ጋዜጣና መጽሔቶች ፍቃድ ቢወስዱም 27 ብቻ ኅትመት ላይ እንዳሉ ታወቀ። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው ከ2001 ጀምሮ ባሉት ጊዜያት ውስጥ 87 ጋዜጦች እና 174 መጽሔቶች በተለያዩ ምክንያቶች ከኅትመት ውጭ ሆነዋል።
የባለሥልጣኑ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ገብረ ጊዮርጊስ አብርሃ የኅዳር ወር መረጃን መሠረት በማድረግ ‹‹ቁጥራቸው በየወሩ ልዩነት ቢያሳይም በኅዳር ወር 27 የተለያየ ይዘት ያላቸው የኅትመት ሚዲያዎች ብቻ ናቸው ገበያ ላይ የዋሉት›› ብለዋል።
አያይዘውም የተጠቀሰው አኀዝ የሚያመለክተው የብሮድካስት ባለሥልጣን ቁጥጥር በሚያደርግባቸው አዲስ አበባ እና ክልሎች ላይ የስርጭት አድማስ ያላቸውን የኅትመት ሚዲያዎች እንጂ ክልላዊ ጋዜጦችና መጽሔቶን አይጨምርም ብለዋል።
ለኅትመት መገናኛዎቹ መክሰም በባለሥልጣኑ እንደ ምክንያት የተዘረዘሩት የኅትመት ዋጋ መጨመር፣ የመረጃ እጥረት፣ የቤት ኪራይ መጨመር እና ማስታወቂያዎች በጥቂት የመገናኛ ኅትመቶች ቁጥጥር ሥር መውደቅ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ፍቃድ ወስደው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ካልገቡ ከኅትመት ውጭ ናቸው ሊባሉ እንደሚችሉ ባለሥልጣኑ ገልጸዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ እስካሁን ተመዝግበው ፈቃድ ከወሰዱ በኋላ ወደ ሥራ ያልገቡ አምስት ጋዜጦች እና ሠላሳ ሦስት መጽሔቶች ቢኖሩም አንድ ዓመት ስላልሞላቸው እንቅስቃሴ ላይ ናቸው ተብሎ እንደሚታመን ተገልጿል።
ብሮድካስት ባለስልጣን በዋናነት ምክንያት ናቸው ተብለው ለተቀመጡት ችግሮች መፍትሔ ለማምጣት እየሠራ እንደሆነ የተናገረ ሲሆን የኅትመት ዋጋ መጨመር መፍትሔ የሚያሻው ጉዳይ ስለሆነ በተደጋጋሚ ለሚመለከተው አካል ጉዳዩን ማቅረባቸውን አክለዋል። ከኅትመት ዋጋ መናር ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ በታኅሣሥ 6 ዕትሟ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከታኅሣሥ 12 ጀምሮ የ16 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉን መዘገቧ የሚታወስ ነው።
ሌላው ባለሥልጣኑ እንደችግር ያስቀመጠው የመረጃ እጥረት ሲሆን ይሄንንም ለመቅረፍ ሁሉም መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ መሥሪያ ቤቶች ተገቢውን መረጃ እንዲሰጡ የግንዛቤ መፍጠር ሥራ እንደተሠራ ጠቁመዋል።
በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ማስታወቂያዎች ለሁሉም ኅትመት መገናኛዎች በፍትሐዊነት እንዲከፋፈሉ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ተገልጿል። ከተጠቀሱት ምክንያቶች ውጪ ንግድ ፍቃድን በጊዜው አለማደስ እንዲሁም በመታገድ ምክንያት ከሥራ ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ የታወቀ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ግን ፍቃድ የመሰረዝ ሥልጣን የለውም። ባለሥልጣኑ 261 ጋዜጦችና መጽሔቶችን በተመለከተ ከኅትመት ውጪ ሆኑ እንጂ አልተሰረዙምያለ ሲሆን አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ በማሟላት ወደ ኅትመት መመለስ እንደሚችሉ አሳውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here