በአቅርቦት እጥረት ምክንያት ከስጋና ወተት የተገኘው ገቢ መቀነሱ ተገለጸ

0
472

በአቅርቦት እጥረት ምክንያት ያለፈው በጀት አመት 2012 ከስጋ እና ወተት ተዋጽኦ የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢው መቀነሱን የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ ተናገረ።

በ2012 በጀት አመት ማጠናቀቂያ የተገኘውን ገቢ የኢኒስቲቲውቱ ዋና ዳይሬክተር ኃይለ ስላሴ ወረስ እንደገለፁት ኢትዮጵያ ከሥጋና ከእንስሳት ውጤቶች ከእቅድ በታች 72 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን ነው ያመላከቱት።

በዚህም እንስሳት በማጣት ብቻ አንድ ግዙፍ ቄራ አዳማ ከተማ የሚገኝ በ2011 በጀት ዓመት ብቻ 23 ነጥብ 15 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘት የቻለ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ግን መዘጋቱን ነው ያነሱት ። አንዱ ለገቢው መቀነስም እንደ ዋና ምክንያት የሱን መዘጋትም አንስተዋል። በ2012 በጀት አመትም በመጀመርያዎቹ ሦስት ወራት 3 ነጥብ 37 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መጀመሪያ አካባቢ አስገብቶ እንደዘጋው ነው ያነሱት።
ኢንስቲቲዪቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከወጪ ንግዱ 124 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢያቅድም ማሳካት የቻለው ግን 72 ነጥብ 31 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው።

በዕቅዱ መሰረት ከበግ እና ፍየል እቅዱ 88 ነጥብ 54 ሚሊዮን የነበረው ቢሆንም የተገኘው ገቢ ግን 64 ነጥብ 85 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መሆኑን ተገልፀዋል።

የበሬ ስጋ በዕቅድ ደረጃ 17 ነጥብ 72 ሚሊዮን ዶላር ለማስገባት ታስቦ የነበረ ሲሆን ነገር ግን በበጀት ዓመቱ አፈፃፀሙ 1ነጥብ 36 ሚሊየን ዶላር ብቻ ነው የተገኘው ። ከተረፈ ምርት ለማግኘት ታስቦ የተቀመጠው በዕቅድ ደረጃ 11ነጥብ 81 ሚሊየን ዶላር ሲሆን አፈፃፀሙ 3ነጥብ 33 ሚሊየን ዶላር መውረዱ ታውቋል ። ከስጋ ውጤቶች ለማግኘት የታሰበ አጠቃላይ ዕቅዱ 118 ነጥብ 07 ሲሆን አፈፃፀሙ ደግሞ 69 ነጥብ 54 ብቻ መሆኑ ተገልፀዋል።

ማር ፣አሳ ፣ወተት ደግሞ ፤ የማር 1.32 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም ዕቅዱ አፈፃፀሙ ግን 520 ሺህ ዶላር ብቻ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል ። በተመሳሳይም የአሳ ምርት 120 ሺህ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 40 ሺህ ዶላር ብቻ ማግኘት መቻሉም ታውቋል ። ከወተት ተዋጽኦ ታቀዶ የነበረው 290 ሲሆን አፈፃፀሙ ግን 120 ሺህ ነው።

124 ነጥብ 12 ሚሊዮን ዶላር ካለፈው አመት ጋር ሲወዳደር ወደ በ24 ነጥብ 51 ሚሊየን ዶላር ገቢው እንደቀነሰም ታውቋል። ለዚህም እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ የአቅርቦት ችግር እንደሆነ ነው ።

ኢንስቲቲውቱ ዳይሬክተር ኃይለስላሴ ወረስ እንደገለጹት በዋና ወጪ ንግድ መዳረሻዎች ማለትም በሳውዲ አረቢያና በተባበሩት ዓረብ ሀገርራት በኩል ከፍተኛ የሥጋ ፍላጎት በመጋቢት እና በግንቦት ወራት የነበረ ቢሆንም ማቅረብ አለመቻሉን አስታውቀዋል ።

በቀን እስከ 100 ቶን የሚደርስ የስጋ ፍላጎት እንደነበር እና በአቅርቦት እጥረት ብሎም በኮሮና ወረርሺን ምክንያት የአየር መጓጓዝዣ አገልግሎት መዘጋት ምርቶችን ለመላክ አለመቻሉ የወጪ ንግዱ ገቢ እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል ።

በተያያዘም ዳይሬክተሩ በስፋት እንዳነሱት ከሆነ ፤ የቁም ከብት አቅርቦት ማነስ እና የህገ ወጥ የቁም ከብት ንግድ መስፋፋት ማነቆ እንደሆንባቸው አመላክተዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here